ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። በማግስቱም ጠዋት በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ተመልሶ መጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ተቀምጦ ያስተምር ነበር። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ስታመነዝር የተያዘች ሴት አመጡና በሕዝቡ መካከል አቆሙአት። ኢየሱስንም እንዲህ አሉት፦ “መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተይዛለች፤ እንዲህ ዐይነትዋ ሴት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ሙሴ በሕጋችን አዞናል፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?” ይህንንም ያሉት በእርሱ ላይ የክስ ምክንያት እንዲያገኙ ሊፈትኑት ፈልገው ነበር፤ ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በመሬት ላይ ይጽፍ ጀመር። ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ ቀና አለና፥ “ከእናንተ መካከል ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ በእርስዋ ላይ ይጣል!” አላቸው። ከዚህም በኋላ እንደገና ጐንበስ ብሎ በመሬት ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ከሽማግሌዎች ጀምሮ ሁሉም አንድ በአንድ ከዚያ ሄዱ፤ ስለዚህ ኢየሱስ በመካከል ቆማ ከነበረችው ሴት ጋር ብቻውን ቀረ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ቀና ብሎ፥ “አንቺ ሴት ከሳሾችሽ የት አሉ? የፈረደብሽ ማንም የለምን?” አላት። እርስዋም “ጌታ ሆይ! ማንም የለም” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ዳግመኛ ኃጢአት አትሥሪ” አላት። እንደገናም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል፤ በጨለማም አይመላለስም” ሲል ተናገራቸው። ፈሪሳውያን “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ምንም እንኳ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁ፥ ወዴትም እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም። እናንተ በሥጋዊ አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም ላይ አልፈርድም። ብፈርድም እንኳ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነና እኔ ብቻዬን ስለማልፈርድ ፍርዴ እውነት ነው፤ የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። ስለዚህ እኔ ስለ ራሴ እመሰክራለሁ፤ የላከኝ አብም ስለ እኔ ይመሰክራል።” በዚያን ጊዜ እነርሱ “አባትህ የት አለ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም “እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ ይህን ቃል የተናገረው በቤተ መቅደስ በገንዘብ መቀበያ ሣጥን አጠገብ ሆኖ ሲያስተምር ነው። ታዲያ፥ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።
የዮሐንስ ወንጌል 8 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 8:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos