የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 7:1-31

ዮሐንስ 7:1-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚህ በኋ​ላም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በገ​ሊላ ይመ​ላ​ለስ ነበረ፤ ወደ ይሁዳ ምድ​ርም ሊሄድ አል​ወ​ደ​ደም፤ አይ​ሁድ ሊገ​ድ​ሉት ይሹ ነበ​ርና። የአ​ይ​ሁ​ድም የዳስ በዓ​ላ​ቸው ደርሶ ነበር። ወን​ድ​ሞ​ቹም ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን እን​ዲህ አሉት- “ደቀ መዛ​ሙ​ር​ትህ የም​ት​ሠ​ራ​ውን ሥራ​ህን እን​ዲ​ያዩ ከዚህ ወጥ​ተህ ወደ ይሁዳ ሀገር ሂድ። ሊገ​ለጥ ወድዶ ሳለ በስ​ውር አን​ዳች ነገር የሚ​ያ​ደ​ርግ ማንም የለ​ምና፤ አንተ ግን ይህን የም​ታ​ደ​ርግ ከሆነ ራስ​ህን ለዓ​ለም ግለጥ። ወን​ድ​ሞቹ ገና አላ​መ​ኑ​በ​ትም ነበ​ርና። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ጊዜዬ ገና አል​ደ​ረ​ሰም፤ የእ​ና​ንተ ጊዜ ግን ዘወ​ትር የተ​ዘ​ጋጀ ነው። ዓለም እና​ን​ተን ሊጠ​ላ​ችሁ አይ​ች​ልም፤ እኔን ግን ይጠ​ላ​ኛል፤ ሥራዉ ክፉ እንደ ሆነ እኔ እመ​ሰ​ክ​ር​በ​ታ​ለ​ሁና። እና​ን​ተም ወደ​ዚህ በዓል ውጡ፤ እኔ አሁን ወደ​ዚህ በዓል አል​ወ​ጣም፤ ጊዜዬ ገና አል​ደ​ረ​ሰ​ምና።” እር​ሱም እን​ዲህ ብሎ​አ​ቸው በገ​ሊላ ቀረ። ወን​ድ​ሞቹ ለበ​ዓል ከወጡ በኋላ፥ እር​ሱም ያን​ጊዜ በግ​ልጥ ሳይ​ሆን ተሰ​ውሮ ወጣ። አይ​ሁ​ድም፥ “ያ ወዴት ነው?” እያሉ በበ​ዓሉ ይፈ​ል​ጉት ጀመር። ሕዝ​ቡም ስለ እርሱ ብዙ አን​ጐ​ራ​ጐሩ፥ “ደግ ሰው ነው” ያሉ ነበሩ፤ ሌሎች ግን፥ “አይ​ደ​ለም፤ ሕዝ​ቡን ያስ​ታል እንጂ” አሉ። ነገር ግን፥ አይ​ሁ​ድን በመ​ፍ​ራት የእ​ር​ሱን ነገር ገልጦ የተ​ና​ገረ አል​ነ​በ​ረም። በበ​ዓሉ ቀኖች እኩ​ሌ​ታም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ወደ መቅ​ደስ ወጥቶ ያስ​ተ​ምር ጀመረ። አይ​ሁ​ድም፥ “ይህ ሳይ​ማር መጽ​ሐ​ፍን እን​ዴት ያው​ቃል?” እያሉ ትም​ህ​ር​ቱን አደ​ነቁ። ስለ​ዚ​ህም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ትም​ህ​ርቴ የላ​ከኝ ናት እንጂ የእኔ አይ​ደ​ለ​ችም። ፈቃ​ዱን ሊያ​ደ​ርግ የሚ​ወ​ድድ ግን ትም​ህ​ርቴ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ እንደ ሆነች፥ የም​ና​ገ​ረ​ውም ከራሴ እን​ዳ​ይ​ደለ እርሱ ያው​ቃል። ከራሱ የሚ​ና​ገር የራ​ሱን ክብር ይሻል፤ የላ​ከ​ውን ያከ​ብር ዘንድ የሚ​ፈ​ልግ ግን እው​ነ​ተኛ ነው፤ ሐሰ​ትም የለ​በ​ትም። ሙሴ ኦሪ​ትን ሰጥ​ቶ​አ​ችሁ የለ​ምን? ከእ​ና​ንተ አንዱ ስንኳ ኦሪ​ትን የሚ​ያ​ደ​ርግ የለም፤ እን​ግ​ዲህ ልት​ገ​ድ​ሉኝ ለምን ትሻ​ላ​ችሁ?” ሕዝ​ቡም፥ “ጋኔን አለ​ብ​ህን? ማን ሊገ​ድ​ልህ ይሻል?” ብለው መለ​ሱ​ለት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ አላ​ቸው፥ “አንድ ሥራ ሠራሁ፤ ሁላ​ች​ሁም አደ​ነ​ቃ​ችሁ። ስለ​ዚህ ሙሴ ግዝ​ረ​ትን ሰጥ​ቶ​አ​ችሁ ነበር፤ ነገር ግን ከአ​ባ​ቶች ናት እንጂ ከሙሴ አይ​ደ​ለ​ችም፤ በሰ​ን​በ​ትም ሰውን ትገ​ዝ​ሩ​ታ​ላ​ችሁ። የሙሴ ሕግ እን​ዳ​ይ​ሻር ሰው በሰ​ን​በት የሚ​ገ​ዘር ከሆነ እን​ግ​ዲያ ሰውን ሁለ​ን​ተ​ና​ውን በሰ​ን​በት ባድ​ነው ለምን ትነ​ቅ​ፉ​ኛ​ላ​ችሁ? የእ​ው​ነት ፍርድ ፍረዱ እንጂ ለሰው ፊት በማ​ድ​ላት አት​ፍ​ረዱ።” ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ሰዎ​ችም እን​ዲህ የሚሉ ነበሩ፥ “ይህ አይ​ሁድ ሊገ​ድ​ሉት የሚ​ሹት አይ​ደ​ለ​ምን? እነሆ፥ እርሱ በገ​ሀድ ይና​ገ​ራል፤ እነ​ርሱ ግን ምንም የሚ​ሉት የለም፤ ይህ በእ​ው​ነት ክር​ስ​ቶስ እንደ ሆነ ምና​ል​ባት አለ​ቆች ዐው​ቀው ይሆን? ነገር ግን ይህን ከየት እንደ ሆነ እና​ው​ቃ​ለን፤ ክር​ስ​ቶስ በሚ​መ​ጣ​በት ጊዜስ ከወ​ዴት እንደ ሆነ ማንም አያ​ው​ቅም”። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም በመ​ቅ​ደስ ሲያ​ስ​ተ​ምር ቃሉን ከፍ አድ​ርጎ እን​ዲህ አለ፥ “እኔን ታው​ቁ​ኛ​ላ​ችሁ፤ ከወ​ዴ​ትም እንደ ሆንሁ ታው​ቃ​ላ​ችሁ፤ እኔ ራሴ የመ​ጣሁ አይ​ደ​ለ​ሁም፤ ነገር ግን እና​ንተ የማ​ታ​ው​ቁት የላ​ከኝ እው​ነ​ተኛ አለ። እኔ ግን አው​ቀ​ዋ​ለሁ፤ እኔ ከእ​ርሱ ነኝና፥ እር​ሱም ልኮ​ኛ​ልና። ስለ​ዚ​ህም ሊይ​ዙት ወደው ነበር፤ ነገር ግን እጁን በእ​ርሱ ላይ ያነሣ የለም፤ ጊዜዉ ገና አል​ደ​ረ​ሰም ነበ​ርና። ከሕ​ዝ​ቡም ብዙ​ዎች አመ​ኑ​በ​ትና፥ “በውኑ ክር​ስ​ቶስ በሚ​መ​ጣ​በት ጊዜ ይህ ሰው ካደ​ረ​ገው ተአ​ም​ራት የሚ​በ​ልጥ ያደ​ር​ጋ​ልን?” አሉ።

ዮሐንስ 7:1-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፣ በዚያ የነበሩት አይሁድ ሊገድሉት ስለ ፈለጉ፣ በይሁዳ አውራጃ መዘዋወር ትቶ በገሊላ ተዘዋወረ። የአይሁድ የዳስ በዓል በተቃረበ ጊዜ ግን፣ የኢየሱስ ወንድሞች እንዲህ አሉት፤ “ደቀ መዛሙርትህም ደግሞ የምታደርገውን ታምራት እንዲያዩ፣ ከዚህ ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱን ሊገልጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ ማንም የለምና። አንተም እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ፣ ራስህን ለዓለም ግለጥ።” የገዛ ወንድሞቹ እንኳ አላመኑበትም ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ገና አልደረሰም፤ ለእናንተ ግን ማንኛውም ጊዜ ምቹ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይችልም፤ እኔ ግን፣ አድራጎቱ ክፉ መሆኑን ስለምመሰክርበት ይጠላኛል። እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ስላልደረሰ ወደ በዓሉ አልሄድም።” ይህን ብሏቸው በገሊላ ቈየ። ይሁን እንጂ፣ ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ፣ እርሱም በግልጥ ሳይሆን በስውር ወደ በዓሉ ሄደ። በበዓሉም ላይ አይሁድ፣ “ያ ሰው የት አለ?” እያሉ ይፈልጉት ነበር። ስለ እርሱ በሕዝቡ መካከል ብዙ ጕምጕምታ ነበር። አንዳንዶች፣ “ደግ ሰው ነው” አሉ። ሌሎች ግን፣ “የለም፤ ሕዝቡን የሚያስት ነው” አሉ። ይሁን እንጂ አይሁድን ከመፍራት የተነሣ ስለ እርሱ በግልጽ የተናገረ ማንም አልነበረም። በበዓሉም አጋማሽ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ጀመር። አይሁድም በመደነቅ፣ “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ሊያውቅ ቻለ?” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው። ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ፣ የእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል፤ ከራሱ የሚናገር፣ ያን የሚያደርገው ለራሱ ክብርን ስለሚሻ ነው፤ ስለ ላከው ክብር የሚሠራ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም አይገኝበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ነገር ግን አንዳችሁም ሕጉን አልጠበቃችሁም። ለምን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡም፣ “አንት ጋኔን ያደረብህ! ደግሞ አንተን ማን ሊገድል ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሥራ ብሠራ፣ ሁላችሁም ተገረማችሁ። ግዝረት የመጣው ከአባቶች እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ ሆኖም ሙሴ ግዝረትን ስለ ሰጣችሁ፣ በሰንበት እንኳ ሕፃን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሕፃን በሰንበት የሚገረዝ ከሆነ፣ የሰውን ሁለንተና በሰንበት ስለ ፈወስሁ ለምን በእኔ ላይ ትቈጣላችሁ? የሰውን ፊት በማየት መፍረድ ትታችሁ ቅን ፍርድ ፍረዱ።” በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አሉ፤ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? ይኸው እርሱ በአደባባይ ይናገራል፤ አንድም ቃል አይናገሩትም፤ ክርስቶስ ነው ብለው ባለሥልጣኖቹም ተቀብለውት ይሆን? ይህ ሰው ግን ከየት እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ እኮ ከየት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።” ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አደባባይ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “አዎን፣ እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከየት እንደ ሆንሁም ታውቃላችሁ። እኔ እዚህ ያለሁት በገዛ ራሴ አይደለም፤ ነገር ግን የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው። እናንተ አታውቁትም፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ስለሆንሁ፣ እርሱም ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።” ስለዚህ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አላሳረፈበትም፤ ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎች በእርሱ አምነው፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ሰው ከሚሠራቸው ታምራዊ ምልክቶች የበለጠ ያደርጋል?” አሉ።

ዮሐንስ 7:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር። የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። እንግዲህ ወንድሞቹ፦ “ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱ ሊገልጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ” አሉት። ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል። እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም።” ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም፦ “እርሱ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። በሕዝቡም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም፦ “ደግ ሰው ነው፤” ሌሎች ግን፦ “አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል” ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። አይሁድም፦ “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡ መለሱና፦ “ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ “አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ። ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።” እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች እንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።” እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር፦ “እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ” ብሎ ጮኸ። ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና፦ “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን?” አሉ።

ዮሐንስ 7:1-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ይዘዋወር ነበር፤ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበረ ግን በይሁዳ ሊዘዋወር አልፈለገም፤ በዚያን ጊዜ የአይሁድ የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ስለዚህ ወንድሞቹ ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ደቀ መዛሙርትህ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ፤ በግልጥ ለመታወቅ የሚፈልግ ሰው ሥራውን በስውር አያደርግም፤ አንተም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስታደርግ ራስህን ለዓለም ልትገልጥ ያስፈልጋል።” ይህንንም ያሉበት ምክንያት ወንድሞቹ እንኳ በእርሱ ስላላመኑ ነው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ጊዜ ገና አልደረሰም፤ የእናንተ ጊዜ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይችልም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን ስለምመሰክርበት እኔን ይጠላኛል። እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ እኔ ግን ጊዜዬ ገና ስላልደረሰ ወደዚህ በዓል አልሄድም።” ይህንንም ብሎ እርሱ በገሊላ ቀረ። ነገር ግን ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ እርሱ በይፋ ሳይሆን በስውር ወደ በዓሉ ሄደ። በበዓሉም ላይ “እርሱ የት ነው?” እያሉ አይሁድ ይፈልጉት ነበር። ሕዝቡም ስለ እርሱ በሹክሹክታ ይነጋገሩ ነበር፤ አንዳንዶቹ “እርሱ ደግ ሰው ነው” ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ “አይደለም፤ እርሱ ሕዝቡን ያስታል” ይሉ ነበር። ይሁን እንጂ የአይሁድን ባለ ሥልጣኖች በመፍራት ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አልተናገረም። በበዓሉም አጋማሽ ላይ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ ያስተምር ጀመር። አይሁድም፥ “ይህ ሰው ሳይማር ይህን ሁሉ እንዴት ሊያውቅ ቻለ?” እያሉ ይደነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእኔ ትምህርት ከላከኝ ከአብ የተገኘ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም። የላከኝን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልግ ቢኖር ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር የተገኘ ወይም እኔ ከራሴ የተናገርኩት መሆኑን ያውቃል። ከገዛ ራሱ የሚናገር የገዛ ራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላኪውን ክብር የሚፈልግ ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም የለበትም። ሙሴ ሕግን ሰጥቶአችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ ሕግን የሚፈጽም ማንም የለም። እናንተ ለምን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡም “አንተ ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ አንድ ሥራ ሠራሁ፤ እናንተም ሁላችሁ በዚህ ሥራ ትደነቃላችሁ። ሙሴ የግዝረትን ሥርዓት ሰጣችሁ፤ ይህም ሥርዓት የተገኘው፤ ከአባቶች ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ እናንተም እኮ በሰንበት ሰውን ትገርዛላችሁ። እንግዲህ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ እንዳይሻር በሰንበት ቀን ሰው የሚገረዝ ከሆነ ታዲያ፥ እኔ በሰንበት ቀን የሰውን ሁለንተና በመፈወሴ ስለምን ትቈጣላችሁ? ትክክለኛ ፍርድ ፍረዱ እንጂ የሰውን ፊት አይታችሁ በማዳላት አትፍረዱ።” ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በግልጥ ይናገራል፤ እነርሱም ምንም አላሉትም፤ ይህ ሰው መሲሕ መሆኑን ባለሥልጣኖች በእውነት ዐውቀው ይሆን? ሆኖም ይህ ሰው ከወዴት እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን፤ መሲሕ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ የሚያውቅ ማንም የለም።” ስለዚህ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደ መጣሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ በራሴ ሥልጣን አልመጣሁም፤ የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው፤ እናንተ ግን አታውቁትም። እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ስለ መጣሁና እርሱ ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።” በዚያን ጊዜ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም። ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎቹ በእርሱ አመኑ፤ እንዲህም አሉ፦ “መሲሕ በሚመጣበትስ ጊዜ ይህ ሰው ካደረጋቸው ተአምራት የበለጠ ያደርጋልን?”

ዮሐንስ 7:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ይመላለስ ነበር። አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበር። የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ወንድሞቹም “ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ በይፋ መታወቅ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ እራስህን ለዓለም ግለጥ፤” አሉት። ወንድሞቹም እንኳን አላመኑበትም ነበርና። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ይጠላኛል፤ ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና ነው። እናንተ ወደ በዓሉ ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል አልወጣም።” ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ፥ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም “እርሱ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። በሕዝቡም መካከል በእርሱ ምክንያት ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዶቹ “ደግ ሰው ነው፤” ሌሎች ደግሞ “አይደለም፤ ሕዝቡን ያስታል እንጂ፤” ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። አይሁድም “ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ትምህርቴስ የላከኝ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር እንደሆነ ወይንም እኔ ከራሴ የምናገር እንደሆነ ያውቃል። ከገዛ እራሱ የሚናገር የገዛ እራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፤ በእርሱም ዐመፃ የለበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚፈጽም አንድ እንኳን የለም። ልትገድሉኝ ስለምን ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡ መለሱና “ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አንድ ሥራ ፈጸምኩ፥ ሁላችሁም ትደነቃላችሁ። ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።” ከኢየሩሳሌም ሰዎችም እንዳንዶቹ እንዲህ አሉ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆ፥ በግልጥ ይናገራል፤ ነገር ግን ምንም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው ክርስቶስ እንደሆነ በእውነት አወቁን? ሆኖም ይህ ሰው ከወዴት እንደሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደሆነ ማንም አያውቅም።” እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር “እኔንም ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ፤ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ፤” ብሎ ጮኸ። ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና፥ “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ሰው ካደረጋቸው ምልክቶች የሚበልጥ ያደርጋልን?” አሉ።