ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር። የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። እንግዲህ ወንድሞቹ፦ “ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱ ሊገልጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ” አሉት። ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል። እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም።” ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም፦ “እርሱ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። በሕዝቡም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም፦ “ደግ ሰው ነው፤” ሌሎች ግን፦ “አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል” ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። አይሁድም፦ “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡ መለሱና፦ “ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ “አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ። ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።” እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች እንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።” እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር፦ “እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ” ብሎ ጮኸ። ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና፦ “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን?” አሉ።
የዮሐንስ ወንጌል 7 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 7:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos