ዮሐንስ 6:26-65
ዮሐንስ 6:26-65 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስለ አያችሁ አይደለም። የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘለዓለም ሕይወት ለሚኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚጠፋው መብል አይደለም፤ ይህን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንሠራ ዘንድ ምን እናድርግ?” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ ነው፤” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፥ “የምትሠራውን አይተን በአንተ እናምን ዘንድ ምን ተአምራት ታደርጋለህ? አባቶቻችንስ ‘ሊበሉ እንጀራ ከሰማይ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ በምድረ በዳ መና በሉ። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ያን እንጀራ ከሰማይ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ከሰማይ የእውነት እንጀራን ሰጥቶአችኋል እንጂ። የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ፤ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።” እነርሱም፥ “አቤቱ ከዚያ እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም ለዘለዓለም አይጠማም። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ አያችሁኝ፤ አላመናችሁብኝምም። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም። ከሰማይ የወረድሁ የላከኝን ፈቃድ እንጂ፥ ፈቃዴን ላደርግ አይደለምና። የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድስ እንኳ ቢሆን እንዳይጠፋ ነው፤ ነገር ግን እኔ በኋለኛዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ። የአባቴ ፈቃዱ ይህ ነው፤ ወልድን አይቶ የሚያምንበት ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ።” አይሁድም ስለ እርሱ አንጐራጐሩ፤ “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ብሎአቸዋልና። “እኛ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል?” አሉ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ መምጣትን የሚችል የለም፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ። ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ በነቢያት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአባቴ የሰማ ሁሉ ተምሮ ወደ እኔ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር አብን ያየው ማንም የለም፤ እርሱም አብን አየው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁስ በምድረ በዳ መና በሉ፥ ሞቱም። ከእርሱ የበላ ሁሉ እንዳይሞት ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው።” “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ይህ እንጀራ ሥጋዬ ነው።” አይሁድም፥ “ይህ እንበላ ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛዪቱ ቀን አነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ነውና፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። የላከኝ አብ ሕያው እንደ ሆነ፥ እኔም ስለ አብ ሕያው ነኝ፤ ሥጋዬንም የሚበላ እርሱ ደግሞ ስለ እኔ ሕያው ሆኖ ይኖራል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ በልተውት እንደሞቱበት ያለ መና አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል።” በቅፍርናሆምም በምኵራብ ሲያስተምራቸው ይህን ተናገረ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ ይህን ሰምተው፥ “ይህ ነገር የሚያስጨንቅ ነው፤ ማንስ ሊሰማው ይችላል?” አሉ። ጌታችን ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ አንጐራጐሩ በልቡ ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ያሰናክላችኋልን? እንግዲህ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲያርግ ብታዩት እንዴት ይሆን? ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ግን አንዳች አይጠቅምም፤ ይህም እኔ የምነግራችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ ውስጥ የማያምኑ አሉ፤” ጌታችን ኢየሱስ ከጥንት ጀምሮ የማያምኑበት እነማን እንደ ሆኑ፥ የሚያሲዘውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና። እንዲህም አላቸው፥ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ከአብ ካልተሰጠው በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚቻለው የለም።”
ዮሐንስ 6:26-65 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በእርሱ ላይ ዐትሟልና።” እነርሱም፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” አሉት። ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል መለሰላቸው። ስለዚህ እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ “አይተን እንድናምንህ ምን ታምራዊ ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራን ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ ግን አባቴ ነው፤ የእግዚአብሔር እንጀራ እርሱ ከሰማይ የሚወርድ፣ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።” እነርሱም፣ “ጌታ፣ እንግዲያውስ ይህን እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም። ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ፣ አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፤ የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳይጠፋብኝ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣ ነው። የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጕረመርሙበት ጀመር። ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’ ” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፏል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። ነገር ግን ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የሚወርድ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።” አይሁድም፣ “እንበላ ዘንድ ይህ ሰው ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤ ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፤ ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።” ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኵራብ እያስተማረ ሳለ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?” አሉ። ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ማጕረምረማቸውን ኢየሱስ በገዛ ራሱ ተረድቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ዕንቅፋት ይሆንባችኋልን? ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው? መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው፤ ይሁን እንጂ ከእናንተ የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ይህም፣ ኢየሱስ እነማን እንዳላመኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ቀድሞውኑ ያውቅ ስለ ነበር ነው። ቀጥሎም፣ “ ‘ከአብ ካልተሰጠው በቀር፣ ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም’ ያልኋችሁ ለዚህ ነው” አለ።
ዮሐንስ 6:26-65 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። እንግዲህ፦ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው። እንግዲህ፦ እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት። ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው። ስለዚህ፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፥ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳልጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው። ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። እንግዲህ አይሁድ፦ ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና፦ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ፦ ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሁሉም ከእግዚአብሔ የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። እንግዲህ አይሁድ፦ ይህ ሰው ሥጋውን ልበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ። ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ፦ ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ። ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው፦ ይህ ያስናክላችኋላን? እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲመጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል? ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይተቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውንም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና። ደግሞ፦ ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ።
ዮሐንስ 6:26-65 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቅስ እግዚአብሔር አብ የማረጋገጫ ማኅተም ስለ አተመው የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ፥ የዘለዓለም ሕይወት ለሚሆነው ምግብ ሥሩ።” ሰዎቹም “ታዲያ፥ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ ይገባናል?” አሉት። ኢየሱስም “የእግዚአብሔር ሥራማ እግዚአብሔር በላከው ማመን ነው” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “እኛ አይተን በአንተ እንድናምን ምን ተአምር ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ‘እንዲበሉ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ አባቶቻችን በበረሓ መና በልተዋል።” በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ የወረደውን እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድና ለዓለም ሕይወትን የሚሰጥ ነው።” ስለዚህ ሰዎቹ “ጌታ ሆይ! ይህን ዐይነት እንጀራ ዘወትር ስጠን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ፈጽሞ አይራብም፤ በእኔ የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም፤ እናንተ ግን አይታችሁኛል፤ ግን በእኔ አላመናችሁም እላችኋለሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ፈጽሞ ወደ ውጪ አላባርረውም። እኔ ከሰማይ የወረድኩት የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ አይደለም። የላከኝ ፈቃድ፥ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳላጠፋ በመጨረሻው ቀን ከሞት እንዳስነሣቸው ነው። አዎ! የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያይና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ።” ስለዚህ ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ አይሁድ በእርሱ ላይ አጒረመረሙ፤ እንዲህም አሉ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለምን? ታዲያ፥ አሁን እርሱ እንዴት ‘ከሰማይ ወረድኩ’ ይላል?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ የላከኝ አብ የሳበው ካልሆነ በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል ማንም የለም፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም በመጨረሻ ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ። በነቢያት መጻሕፍት ‘ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ ስለዚህ ከአብ ሰምቶ የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። ይህም ማለት አብን ያየው ሰው አለ ማለት አይደለም፤ አብን ያየው ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣው እርሱ ብቻ ነው። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ (በእኔ) የሚያምን ሰው የዘለዓለም ሕይወት አለው። እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ፤ አባቶቻችሁ በበረሓ መና በሉ፤ ነገር ግን ሞቱ፤ ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ ይህን እንጀራ የሚበላ በፍጹም አይሞትም። ከሰማይ የወረደው ሕይወትን የሚሰጥ እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ሁሉ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን እኔ የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” በዚህ ጊዜ አይሁድ “ይህ ሰው ሥጋውን እንድንበላ እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላና ደሜንም የሚጠጣ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል፥ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው። ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝና እኔም በእርሱ ሕያው እንደ ሆንኩ እንዲሁም ሥጋዬን የሚበላ ሁሉ በእኔ ሕያው ይሆናል። እንግዲህ ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ እርሱም አባቶቻችሁ እንደ በሉት ዐይነት አይደለም፤ ያን እንጀራ የበሉ ሞተዋል፤ ይህን እንጀራ የሚበሉ ግን ዘለዓለም ይኖራሉ።” ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም በምኲራብ በሚያስተምርበት ጊዜ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ “ይህ አነጋገር ከባድ ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል?” አሉ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንዳጒረመረሙ በመንፈሱ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ነገር ያሰናክላችኋልን? የሰው ልጅ ወደነበረበት ተመልሶ ሲወጣ ስታዩ ምን ልትሉ ነው? ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሰው ኀይል ግን ለምንም አይጠቅምም፤ እኔ ለእናንተ የተናገርኩት ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዳንዶች የማያምኑ አሉ፤” ኢየሱስ ይህን የተናገረው ከመጀመሪያ አንሥቶ የማያምኑ እነማን እንደ ነበሩና አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። ቀጥሎም ኢየሱስ “ከአብ የተፈቀደለት ካልሆነ በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል የለም ያልኳችሁ ስለዚህ ነው” አለ።
ዮሐንስ 6:26-65 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን የለዘለዓለም ሕይወት ለሚሆነው መብል ሥሩ፤ ይህም የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ነው፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” እንግዲህ “የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን እናድርግ?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔር ሥራ ይህ ነው፤ ይህም እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው፤” አላቸው። እንዲህም አሉት፦ “ታዲያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ዓይነት ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ፤” አሉት። ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና፤” አላቸው። ስለዚህ “ጌታ ሆይ! ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም በፍጹም አይጠማም። ነገር ግን እንዳያችሁኝ፥ እንዳላመናችሁም ነገርኳችሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላስወጣውም፤ ፈቃዴን ለማድረግ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድም እንኳን እንዳላጠፋ፥ ይልቁንም በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው ነው። የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፤ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” አይሁድም “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ፤” በማለቱ ማንጐራጐር ጀመሩ፤ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱን እናውቃቸው የለምን? ታዲያ ‘ከሰማይ ወርጃለሁ’ እንዴት ይላል?” አሉ። ኢየሱስም መለሰ፥ አላቸውም፦ “እርስ በእርሳችሁ አታንጐራጉሩ። የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤’ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ እንዲበላ፥ እናም እንዳይሞት ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው። እኔ ከሰማይ የወረደው ሕያው እንጀራ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” አይሁድም “ይህ ሰው ሥጋውን እንድንበላ እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በእራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ፥ እኔም በአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚመገበኝ ደግሞ በእኔ ሕያው ይሆናል። ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ በልተው ነገር ግን እንደሞቱበት ዓይነት አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል።” በቅፍርናሆም፥ በምኵራብ ሲያስተምር ነበር ይህን ያለው። ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በሰሙ ጊዜ “ይህ ንግግር ከባድ ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። ኢየሱስ ግን ደቀመዛሙርቱ በዚህ ምክንያት እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህ ያስናክላችኋልን? ታዲያ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ሊሆን ነው? ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋስ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።” ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ፥ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደሆነ ከመጀመሪያው ያውቅ ነበርና። እንዲህም አለ፦ “ስለዚህ አልኋችሁ፤ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ ያልኋችሁ በዚህ ምክንያት ነው።”