ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስለ አያችሁ አይደለም። የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘለዓለም ሕይወት ለሚኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚጠፋው መብል አይደለም፤ ይህን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንሠራ ዘንድ ምን እናድርግ?” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ ነው፤” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፥ “የምትሠራውን አይተን በአንተ እናምን ዘንድ ምን ተአምራት ታደርጋለህ? አባቶቻችንስ ‘ሊበሉ እንጀራ ከሰማይ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ በምድረ በዳ መና በሉ። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ያን እንጀራ ከሰማይ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ከሰማይ የእውነት እንጀራን ሰጥቶአችኋል እንጂ። የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ፤ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።” እነርሱም፥ “አቤቱ ከዚያ እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም ለዘለዓለም አይጠማም። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ አያችሁኝ፤ አላመናችሁብኝምም። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም። ከሰማይ የወረድሁ የላከኝን ፈቃድ እንጂ፥ ፈቃዴን ላደርግ አይደለምና። የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድስ እንኳ ቢሆን እንዳይጠፋ ነው፤ ነገር ግን እኔ በኋለኛዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ። የአባቴ ፈቃዱ ይህ ነው፤ ወልድን አይቶ የሚያምንበት ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ።” አይሁድም ስለ እርሱ አንጐራጐሩ፤ “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ብሎአቸዋልና። “እኛ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል?” አሉ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ መምጣትን የሚችል የለም፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ። ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ በነቢያት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአባቴ የሰማ ሁሉ ተምሮ ወደ እኔ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር አብን ያየው ማንም የለም፤ እርሱም አብን አየው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁስ በምድረ በዳ መና በሉ፥ ሞቱም። ከእርሱ የበላ ሁሉ እንዳይሞት ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው።” “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ይህ እንጀራ ሥጋዬ ነው።” አይሁድም፥ “ይህ እንበላ ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛዪቱ ቀን አነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ነውና፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። የላከኝ አብ ሕያው እንደ ሆነ፥ እኔም ስለ አብ ሕያው ነኝ፤ ሥጋዬንም የሚበላ እርሱ ደግሞ ስለ እኔ ሕያው ሆኖ ይኖራል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ በልተውት እንደሞቱበት ያለ መና አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል።” በቅፍርናሆምም በምኵራብ ሲያስተምራቸው ይህን ተናገረ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ ይህን ሰምተው፥ “ይህ ነገር የሚያስጨንቅ ነው፤ ማንስ ሊሰማው ይችላል?” አሉ። ጌታችን ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ አንጐራጐሩ በልቡ ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ያሰናክላችኋልን? እንግዲህ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲያርግ ብታዩት እንዴት ይሆን? ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ግን አንዳች አይጠቅምም፤ ይህም እኔ የምነግራችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ ውስጥ የማያምኑ አሉ፤” ጌታችን ኢየሱስ ከጥንት ጀምሮ የማያምኑበት እነማን እንደ ሆኑ፥ የሚያሲዘውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና። እንዲህም አላቸው፥ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ከአብ ካልተሰጠው በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚቻለው የለም።”
የዮሐንስ ወንጌል 6 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 6
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 6:26-65
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos