ዮሐንስ 4:5-14
ዮሐንስ 4:5-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው በወይን ቦታ አቅራቢያ ወደ አለችው ሲካር ወደምትባለው የሰማርያ ከተማ ደረሰ። በዚያም የያዕቆብ የውኃ ጕድጓድ ነበረ። ጌታችን ኢየሱስም መንገድ በመሄድ ደክሞ በዚያ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበር። እነሆ፥ ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “ውኃ አጠጪኝ” አላት። ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ያቺ የሰማርያ ሴትም፥ “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን፥ እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ከእኔ ዘንድ ውኃ ልትጠጣ ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር በሥርዐት አይተባበሩም ነበርና። ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂስ አንቺ ደግሞ በለመንሺው ነበር፤ እርሱም የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር” ብሎ መለሰላት። ያቺ ሴትም እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ አንተ ትበልጣለህን? እርሱም ልጆቹም፥ ከብቶቹም ከእርሱ ጠጥተዋል።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፥ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ዳግመኛ ይጠማል። እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆንለታል እንጂ።”
ዮሐንስ 4:5-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ በሰማርያ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደ ነበረች፣ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ። በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጕድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስም ከጕዞው የተነሣ ደክሞት ስለ ነበር በውሃው ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር። አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ” አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር። ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስለማይተባበሩ ነው። ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት። ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም ከዚሁ ጕድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።”
ዮሐንስ 4:5-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም፦ ውኃ አጠጪኝ አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ስለዚህ ሳምራዊቲቱ፦ አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ፦ የእግዚአብሔርን ስጦታና፦ ወኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት። ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው። ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት።
ዮሐንስ 4:5-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደምትገኝ፥ ሲካር ተብላ ወደምትጠራ የሰማርያ ከተማ መጣ። በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስ መንገድ ከመሄድ የተነሣ ስለ ደከመው በጒድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ። በዚያን ጊዜ አንዲት የሰማርያ አገር ሴት ውሃ ልትቀዳ ወደ ጒድጓዱ መጣች፤ ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ!” አላት። በዚያን ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበር። ይህችም ሳምራዊት ሴት ኢየሱስን፦ “አንተ ከአይሁድ ወገን ሆነህ እንዴት እኔን ሳምራዊቷን ‘ውሃ አጠጪኝ!’ ብለህ ትጠይቀኛለህ?” አለችው፤ ይህን ማለትዋ፥ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስምምነት ስላልነበራቸው ነው። ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ውሃ አጠጪኝ!’ የሚልሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂው ኖሮ፥ እርሱን መለመን የሚገባሽ አንቺ ነበርሽ፤ እርሱም የሕይወትን ውሃ ይሰጥሽ ነበር” አላት። እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ጌታ ሆይ! አንተ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ፥ የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? አንተ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱና ልጆቹ፥ ከብቶቹም ከዚህ ጒድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማዋል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘለዓለም ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ፥ ለሚጠጣው ሰው ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል።”
ዮሐንስ 4:5-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትገኝ ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። አንዲት የሰማርያ ሴት ውሃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ ደቀመዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ስለዚህ ሳምራዊቲቱ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ወሃ አጠጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ ኖሮ፥ አንቺ በለመንሽው ነበር፤ የሕይወትም ውሃ በሰጠሽ ነበር፤” አላት። ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! መቅጃ የለህም፤ ጉድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውሃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል፤” አለችው። ኢየሱስም መልሶ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በእርሱ ውስጥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል እንጂ፤” አላት።