የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 4:5-14

የዮሐንስ ወንጌል 4:5-14 መቅካእኤ

ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትገኝ ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። አንዲት የሰማርያ ሴት ውሃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ ደቀመዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ስለዚህ ሳምራዊቲቱ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ወሃ አጠጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ ኖሮ፥ አንቺ በለመንሽው ነበር፤ የሕይወትም ውሃ በሰጠሽ ነበር፤” አላት። ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! መቅጃ የለህም፤ ጉድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውሃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል፤” አለችው። ኢየሱስም መልሶ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በእርሱ ውስጥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል እንጂ፤” አላት።