ዮሐንስ 3:1-31
ዮሐንስ 3:1-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው፥ “መምህር ሆይ፥ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” አለው። ኒቆዲሞስም፥ “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና። ስለዚህም ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል ስለ አልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳልና፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የሚወለድ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ኒቆዲሞስም መልሶ፥ “ይህ ሊሆን እንዴት ይቻላል?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን እንዴት ይህን አታውቅም?” አለው። እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም። በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው። ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና። ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል፤ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አላመነምና። ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጥቶአልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና። ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። እውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ አብሮአቸው ተቀመጠ። ዮሐንስም በዮርዳኖስ ማዶ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ያጠምቅ ነበር፤ በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ እየመጡ ያጠምቃቸው ነበር። ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልገባም ነበርና። ከዚህም በኋላ በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ፤ ወደ ዮሐንስም ሄደው፥ “መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ካንተ ጋር የነበረው፥ አንተም የመሰከርህለት እርሱ እነሆ፥ ያጠምቃል፤ ሁሉም ወደ እርሱ ይሄዳል” አሉት። ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለ፥ “ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው በስተቀር እርሱ ራሱ ጸጋን ገንዘብ ሊያደርግ ምንም አይችልም። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን እንድሰብክለት ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልኋችሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮች ናችሁ። ሙሽራ ያለችው ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው የሙሽራው ሚዜ ግን በሙሽራው ቃል እጅግ ደስ ይለዋል፤ የእኔ ደስታ አሁን ተፈጸመች። የእርሱ ትበዛለች፤ የእኔ ግን ታንስ ዘንድ ይገባል።” ከላይ የመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የተገኘውም ምድራዊ ነው፤ የምድሩንም ይናገራል፤ ከሰማይ የመጣው ግን ከሁሉ በላይ ነው።
ዮሐንስ 3:1-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደ ሆንህ እናውቃለን” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤ ነፋስ ወደሚወድደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።” ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወድዷልና። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም። በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር። ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር። በአንዳንድ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአንድ አይሁዳዊ መካከል ስለ መንጻት ሥርዐት ክርክር ተነሣ፤ ወደ ዮሐንስም መጥተው፣ “ረቢ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው እነሆ፤ ያጠምቃል። ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሄደ ነው” አሉት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም። ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ’ እንዳልሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። ሙሽራዪቱ የሙሽራው ነች፤ ድምፁን ለመስማት በአጠገቡ የሚቆመው ሚዜ ግን፣ የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፤ እርሱም አሁን ተፈጽሟል። እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል። “ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤
ዮሐንስ 3:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦ መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለም መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም፦ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው። ኒቆዲሞስ መልሶ፦ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው። ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥ እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና። ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ። ወደ ዮሐንስም መጥተው፦ መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት። ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው እንዳች ሊቀበል አይችልም። እናንተ፦ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን፦ ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል። ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።
ዮሐንስ 3:1-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ የአይሁድ አለቃ ነበረ። ይህ ሰው በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር እነዚህን አንተ የምታደርጋቸውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል ማንም የለም፤ ስለዚህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደ ሆንክ እናውቃለን” አለው። ኢየሱስም “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው እንደገና ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። ኒቆዲሞስም “ታዲያ፥ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማሕፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው። ስለዚህ ‘ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል’ ስላልኩህ አትደነቅ። ነፋስ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣና ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ኒቆዲሞስም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ይህን አታውቅምን? እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉትም። ምድራዊውን ነገር ስነግራችሁ የማታምኑ ከሆነ ሰማያዊውን ነገር ስነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። “ሙሴ በበረሓ እባብን ከፍ አድርጎ እንደ ሰቀለ እንዲሁም የሰው ልጅ ከፍ ብሎ ሊሰቀል ይገባዋል። ይህም የሚሆነው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለምን ሕይወት እንዲያገኝ ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለ ወደደው አንድያ ልጁን ሰጠ። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው፥ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም። “በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ ቀድሞውኑ ተፈርዶበታል። “ፍርዱም ይህ ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። ክፉ ነገር የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ ክፉ ሥራውም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። እውነት የሆነውን ነገር የሚያደርግ ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ወደ ብርሃን የሚመጣውም ያደረገው ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት መሆኑ በግልጥ እንዲታይ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ ከእነርሱ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈየ። በዚያኑ ጊዜ ዮሐንስም ብዙ ውሃ ስለ ነበረበት በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር። በዚያን ጊዜ ዮሐንስ ገና አልታሰረም ነበር። በዚያን ጊዜ በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ መንጻት ሥርዓት ክርክር ተነሣ። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ዮሐንስ ቀርበው “መምህር ሆይ፥ ያ ከዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፥ አንተ ስለ እርሱ የመሰከርክለት፥ እነሆ፥ እርሱም ያጠምቃል፤ ሰዎችም ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዳሉ” አሉት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ማንም ሰው እግዚአብሔር ካልሰጠው በቀር ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም፤ ‘ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንጂ እኔ መሲሕ አይደለሁም’ ብዬ እንደ ነገርኳችሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮቼ ናችሁ። ሙሽሪት ያለችው ሰው ሙሽራ ነው፤ የሙሽራው ሚዜ ግን ከሙሽራው አጠገብ ቆሞ ይሰማዋል፤ የእርሱንም ድምፅ በመስማት ይደሰታል፤ ስለዚህ የእኔም ደስታ ይህ ነው፤ እርሱም አሁን ፍጹም ሆኖአል። እርሱ ከፍ ከፍ ማለት ይገባዋል፤ እኔ ግን ዝቅ ዝቅ ማለት ይገባኛል።” ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነ ምድራዊ ነው፤ የምድርንም ነገር ይናገራል፤ ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።
ዮሐንስ 3:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከፈሪሳውያንም ወገን አንድ ሰው ነበረ፤ ስሙ ኒቆዲሞስ ሲሆን የአይሁድም አለቃ ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ “መምህር ሆይ! ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር መሆንህን እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በስተቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል ማንም የለምና፤” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፤” አለው። ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ኒቆዲሞስ መልሶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህንን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ የእኛንም ምስክርነት አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም የሰው ልጅ ነው። ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅም መሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ ከወዲሁ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፥ ብርሃንም ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር መከናወኑ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፤ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን፥ በዚያ ብዙ ውሃ ነበርና፥ ያጠምቅ ነበር፤ እየመጡም ይጠመቁ ነበር፤ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልወረደም ነበርና። በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከልም ስለ ማንጻት ሥርዓት ክርክር ተነሣ። ወደ ዮሐንስም መጥተው “መምህር ሆይ! በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል፤ ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ፤” አሉት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው እንዳችም ነገር ሊቀበል አይችልም። እናንተ ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ፤’ እንዳልሁ እራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ እንዲልቅ እኔ ግን እንዳንስ ያስፈልጋል።” ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው፥ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።