ዮሐንስ 20:21-31
ዮሐንስ 20:21-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም ዳግመኛ እንዲህ አላቸው፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኋለሁ።” ይህንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢኣታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም።” ጌታችን ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ዲዲሞስ የሚሉት ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቶማስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም። ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፥ “ጌታችንን አየነው” አሉት፤ እርሱ ግን፥ “የችንካሩን ምልክት በእጁ ካላየሁ፥ ጣቴንም ወደ ተቸነከረበት ካልጨመርሁ፥ እጄንም ወደ ጎኑ ካላገባሁ አላምንም” አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላም ዳግመኛ ደቀ መዛሙርቱ በውስጡ ሳሉ፥ ቶማስም አብሮአቸው ሳለ በሩ እንደ ተዘጋ ጌታችን ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆመና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚህም በኋላ ቶማስን፥ “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆችን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” አለው። ቶማስም፥ “ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መለሰ። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ስለ አየኸኝ አመንህን? ብፁዓንስ ሳያዩ የሚያምኑ ናቸው” አለው። ጌታችን ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ብዙ ሌላ ተአምራት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ። ነገር ግን ይህ የተጻፈ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እናንተ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ የዘለዓለም ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ነው።
ዮሐንስ 20:21-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።” በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ አልነበረም። ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት። እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ። ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋራ ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው። ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው። ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፏል።
ዮሐንስ 20:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ዳግመኛ፦ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” አላቸው። ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርቱ፦ “ጌታን አይተነዋል” አሉት። እርሱ ግን፦ “የችንካሩን ምልክት በእዶቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም” አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፦ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም በኋላ ቶማስን፦ “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን” አለው። ቶማስም፦ “ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም፦ “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው ናቸው” አለው። ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።
ዮሐንስ 20:21-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንደገና “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ግን፥ ይቅር አይባልላቸውም” አላቸው። ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ በመጣ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ስለዚህ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ቶማስን “ጌታን አየነው” አሉት። እርሱ ግን “በምስማር የተወጉትን እጆቹን ካላየሁና ጣቴን በምስማር በተወጋው ውስጥ ካላገባሁ፥ እጄንም በጐኑ ቊስል ካላገባሁ አላምንም” አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም አብሮአቸው ነበር፤ በሮቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ከዚህ በኋላ ቶማስን፥ “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጐኔ ውስጥ አግባው፤ እመን እንጂ እምነተ ቢስ አትሁን” አለው። ቶማስም “ጌታዬ! አምላኬም!” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ቶማስን፥ “አንተስ ስለ አየኸኝ አመንክ፤ ሳያዩኝ የሚያምኑ ግን የተመሰገኑ ናቸው” አለው። ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ብዙ ተአምር በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንድታምኑና፥ አምናችሁም በእርሱ ስም የዘለዓለም ሕይወትን እንድታገኙ ይህ ተጽፎአል።
ዮሐንስ 20:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ዳግመኛ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ፤” አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፤” አላቸው። ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ሌሎቹም ደቀመዛሙርቱ “ጌታን አይተነዋል፤” አሉት። እርሱ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ላይ ካላየሁ፥ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ውስጥ ካላስገባሁ፥ እጄንም በጎኑ ቊስል ውስጥ ካላስገባሁ አላምንም፤” አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላም ደቀመዛሙርቱ ደግመው በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ ውስጥ አስገባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤” አለው። ቶማስም “ጌታዬና አምላኬ!” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው። ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌላ ብዙ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ መሢሕ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።