ዮሐንስ 2:6-11
ዮሐንስ 2:6-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያም እንደ አይሁድ ልማድ የሚያነጹባቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም እስከ ላይ ሞሉአቸው። “አሁንም ቅዱና ወስዳችሁ ለአሳዳሪው ስጡት” አላቸው፤ ወስደውም ሰጡት። አሳዳሪውም ያን የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ ቀምሶ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣም አላወቀም፤ የቀዱት አሳላፊዎች ግን የወይን ጠጅ የሆነውን ያን ውኃ ያውቁ ነበር። ውኃዉን የሞሉ እነርሱ ነበሩና። አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ፥ “ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያጠጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስካሁን አቈየህ” አለው። ጌታችን ኢየሱስም በቃና ዘገሊላ ያደረገው የተአምራት መጀመሪያ ይህ ነው፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት።
ዮሐንስ 2:6-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአይሁድ የመንጻት ሥርዐት መሠረት፣ ከሰባ ዐምስት እስከ አንድ መቶ ዐሥራ ዐምስት ሊትር የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት ጋኖች በዚያ ነበሩ። ኢየሱስ አገልጋዮቹን፣ “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” አላቸው፤ እነርሱም፣ ጋኖቹን እስከ አፋቸው ሞሏቸው። እርሱም፣ “ከላዩ ቀድታችሁ ለድግሱ ኀላፊ ስጡት” አላቸው። እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ። የድግሱ ኀላፊም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። እርሱም ሙሽራውን ለብቻው ጠርቶ፣ “ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” አለው። ኢየሱስም ይህን የታምራዊ ምልክቶቹ መጀመሪያ በገሊላ አውራጃ በቃና ከተማ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በርሱ አመኑ።
ዮሐንስ 2:6-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም፦ ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፦ ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።
ዮሐንስ 2:6-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አይሁድ የመንጻት ሥርዓት ስለ ነበራቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ነበሩ፤ እያንዳንዱ ጋን ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ውሃ ለመያዝ ይችል ነበር። ኢየሱስ አገልጋዮቹን “ጋኖቹን ውሃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እነርሱም እስከ አፋቸው ሞሉአቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አገልጋዮቹን፦ “በሉ አሁን ቀድታችሁ ለግብዣው ኀላፊ ስጡት” አላቸው፤ እነርሱም ወስደው ሰጡት። የግብዣው ኀላፊ ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ፥ ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ ስለዚህ የግብዣው ኀላፊ፥ ሙሽራውን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ ተጋባዦቹ ከጠጡ በኋላ መናኛውን ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈየህ።” ኢየሱስ ይህን የተአምራት ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን ተአምር በገሊላ ምድር በቃና ከተማ አደረገ፤ በዚህም ዐይነት ክብሩን ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።
ዮሐንስ 2:6-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም “ጋኖቹን ውሃ ሙሉአቸው፤” አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት፤” አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደመጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል፤” አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።