የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 13:21-30

ዮሐንስ 13:21-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ታወከ መስክሮም፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ አመንትተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ፦ “ሰለማን እንደ ተናገረ ንገረን” አለው። እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ፦ “ጌታ ሆይ፥ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም፦ “እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ፦ “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ” አለው። ነገር ግን ከተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው ማንም አላወቀም፤ ይሁዳ ከረጢቱን የያዘ ስለ ሆነ፥ ኢየሱስ፦ ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፥ ወይም ለድሆች ምጽዋት እንዲሰጥ ያለው ለአንዳንዱ መስሎአቸው ነበርና። እርሱም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።

ዮሐንስ 13:21-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ይህ​ንም ተና​ግሮ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በልቡ አዘነ፤ መሰ​ከረ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ከእ​ና​ንተ አንዱ አሳ​ልፎ ይሰ​ጠ​ኛል።” ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ይህን ስለ ማን እንደ ተና​ገረ ተጠ​ራ​ጥ​ረው እርስ በር​ሳ​ቸው ተያዩ፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ይወ​ደው የነ​በረ ከደቀ መዛ​ሙ​ርቱ አንዱ በጌ​ታ​ችን ኢየ​ሱስ አጠ​ገብ ተቀ​ምጦ ነበር። ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም እር​ሱን ጠቀ​ሰና፥ “ይህን ስለ ማን እንደ ተና​ገረ ጠይ​ቀህ ንገ​ረን” አለው። ያም ደቀ መዝ​ሙር በጌ​ታ​ችን ኢየ​ሱስ አጠ​ገብ ቀረብ ብሎ፥ “ጌታ ሆይ፥ እርሱ ማነው?” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ይህ እኔ እን​ጀራ በወጥ አጥ​ቅሼ የም​ሰ​ጠው ነው” አለው፤ ያን ጊዜም እን​ጀራ በወጥ አጥ​ቅሶ ለስ​ም​ዖን ልጅ ለአ​ስ​ቆ​ሮ​ታ​ዊው ይሁዳ ሰጠው። እን​ጀ​ራ​ው​ንም ከተ​ቀ​በለ በኋላ ወዲ​ያ​ውኑ በይ​ሁዳ ልብ ሰይ​ጣን አደ​ረ​በት፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እን​ግ​ዲህ የም​ታ​ደ​ር​ገ​ውን ፈጥ​ነህ አድ​ርግ” አለው። አብ​ረ​ው​ትም በማ​ዕድ የተ​ቀ​መ​ጡት ስለ ምን ይህን እን​ዳ​ለው አላ​ወ​ቁም። ሙዳየ ምጽ​ዋቱ በይ​ሁዳ ዘንድ ነበ​ረና፥ ለበ​ዓል የም​ን​ሻ​ውን ወይም ለነ​ዳ​ያን የም​ን​ሰ​ጠ​ውን ግዛ ያለው የመ​ሰ​ላ​ቸው ነበሩ። ይሁ​ዳም ያን እን​ጀራ ተቀ​ብሎ ወዲ​ያ​ውኑ ወጣ፥ ሌሊ​ትም ነበር።።

ዮሐንስ 13:21-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” ሲል በግልጽ ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ “ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ጠይቀው” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ደገፍ ብሎ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህን ቍራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቍራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው። ይሁዳም ቍራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም፣ “የምታደርገውን ቶሎ አድርግ” አለው፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለምን እንዲህ እንዳለው ማንም አላወቀም ነበረ። ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበር፣ አንዳንዶቹ ለበዓሉ የሚያስፈልግ ነገር እንዲገዛ ወይም ለድኾች እንዲሰጥ ኢየሱስ የተናገረው መሰላቸው። ይሁዳም ያን ቍራሽ እንጀራ እንደ ተቀበለ ወጥቶ ሄደ፤ ሌሊትም ነበረ።

ዮሐንስ 13:21-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በመንፈሱ ተጨነቀና “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል ገልጦ ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ባለማወቃቸው እርስ በእርሳቸው ተያዩ። ኢየሱስ ይወደው የነበረው፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ጐን ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቀሰና “ስለ ማን እንደ ተናገረ እስቲ ጠይቅ” አለው። ስለዚህ እርሱ አንገቱን ወደ ኢየሱስ አስጠጋና “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “እርሱ ይህን እንጀራ በወጥ አጥቅሼ የማጐርሰው ነው” አለ። ይህንንም ብሎ እንጀራ በወጥ አጠቀሰና የአስቆሮታዊው ስምዖን ልጅ ለሆነው ለይሁዳ አጐረሰው። ይሁዳ ጉርሻውን ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ ሰይጣን ዐደረበት፤ ኢየሱስም ይሁዳን፥ “ለማድረግ ያሰብከውን ቶሎ ብለህ አድርግ!” አለው። ኢየሱስ ስለምን ይህን እንዳለ በማእድ ከተቀመጡት ማንም የገባው የለም። ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ ወይም ለድኾች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበር። ይሁዳም ጉርሻውን እንደ ተቀበለ ወዲያውኑ ወጥቶ ሄደ፤ ጊዜውም ሌሊት ነበረ።

ዮሐንስ 13:21-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ተረበሸ፤ እንዲህም ሲል መሰከረ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። ደቀመዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ ግራ ገብቶአቸው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ይወደው የነበረው አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ ስምዖን ጴጥሮስም በምልክት “ሰለ ማን እንደ ተናገረ ንገረን” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም “እኔ የእንጀራ ቁራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” ብሎ መለሰለት። ቁራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ፤” አለው። ነገር ግን ስለምን ይህን እንዳለው በማእድ ከተቀመጡት ማንም አላወቀም፤ ይሁዳ የገንዘብ ከረጢቱን ይዞ ስለ ነበር፥ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፤ ወይም ለድሆች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበርና። እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።