ዮሐንስ 10:11-18
ዮሐንስ 10:11-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም መጥቶ በጎችን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፤ ስለ በጎችም አያዝንም፤ ምንደኛ ነውና። ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ የእኔ የሆኑትን መንጋዎችን አውቃለሁ፤ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል። አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤ ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎችም አሉኝ፤ እነርሱንም ወደዚህ አመጣቸው ዘንድ ይገባኛል፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ ለአንድ እረኛም አንድ መንጋ ይሆናሉ። ስለዚህም፤ አብ ይወድደኛል፥ እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና። ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፤ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፤ ይህንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።”
ዮሐንስ 10:11-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሏቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም። የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ጕረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወድደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ መልሼ ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።”
ዮሐንስ 10:11-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንድሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አኖራለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ። ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።”
ዮሐንስ 10:11-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ቅጥረኛ እንጂ እውነተኛ ያልሆነ እረኛ ግን ተኲላ ሲመጣ በሚያይበት ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኲላውም በጎቹን ነጥቆ ይበታትናቸዋል። እረኛው የሚሸሸውም ቅጥረኛ ስለ ሆነና ለበጎቹም ስለማያስብ ነው። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ እኔ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ በጎቼም እኔን ያውቁኛል። እኔ እነርሱን የማውቃቸው አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ዐይነት ነው፤ እኔ ስለ በጎቼ ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ ይሆናል። “እንደገና መልሼ እወስዳት ዘንድ ሕይወቴን የምሰጥ ስለ ሆንኩ አብ እኔን ይወደኛል። ሕይወቴን በፈቃዴ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም፤ ሕይወቴን ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።”
ዮሐንስ 10:11-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑት ተቀጣሪው ግን፥ ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል። ተቀጣሪ ስለሆነ፥ ለበጎቹም ስለማይገደው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የእራሴም በጎች ያውቁኛል። አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ማምጣት ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለመውሰድ ነፍሴን አሳልፌ ስለምሰጥ አብ ይወደኛል። እኔ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመውሰድም ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።”