መሳፍንት 8:27-35
መሳፍንት 8:27-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌዴዎንም ምስል አድርጎ ሠራው፤ በከተማውም በኤፍራታ አኖረው፤ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎ አመነዘረበት፤ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ። ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፤ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች። የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከአብራኩ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት። በሴኬምም የነበረችው ዕቅብቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ በአብያዜራውያንም ከተማ በኤፍራታ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። እንዲህም ሆነ፤ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፤ በዓሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፤ በዓሊምም አምላክ ይሆናቸው ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገቡ። የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፤ እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ይሩበኣል ለተባለው ለጌዴዎን ቤት ወረታ አላደረጉም።
መሳፍንት 8:27-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፣ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ። ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች። የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ። ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ በሴኬም የምትኖረው ቁባቱም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ አለው። የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአቢዔዝራውያን ምድር ባለችው በዖፍራ፣ በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። ጌዴዎን ሞቶ ብዙም ሳይቈይ እስራኤላውያን የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፤ በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ የታደጋቸውን እግዚአብሔር አምላካቸውን አላሰቡትም። እንዲሁም ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተ ሰቡ ውለታ መላሽ ሆነው አልተገኙም።
መሳፍንት 8:27-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጌዴዎንም ኤፉድ አድርጎ አሠራው፥ በከተማውም በዖፍራ አኖረው፥ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎት አመነዘረበት፥ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ። ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረደ፥ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፥ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች። የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከወገቡ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት። በሴኬምም የነበረችው ቁባቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፥ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፥ በአቢዔዝራውያንም ከተማ በዖፍራ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። እንዲህም ሆነ፥ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ በኣሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፥ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ። የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፥ እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ለጌዴዎን ለይሩበኣል ቤት ወረታ አላደረጉም።
መሳፍንት 8:27-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጌዴዎንም ከዚያ ወርቅ ጣዖት ሠርቶ በትውልድ ከተማው በዖፍራ አኖረው፤ እስራኤላውያንም በሙሉ ከእግዚአብሔር ተለይተው ያንን ማምለክ ጀመሩ፤ ለጌዴዎንና ለቤተሰቡ ሁሉ መሰናከያ ወጥመድ ሆነ። በዚህ ዐይነት ምድያም በእስራኤላውያን ተሸነፈች፤ ዳግመኛም ለእስራኤላውያን የምታሰጋ አልሆነችም፤ ጌዴዎን እስከ ሞተም ድረስ በምድሪቱ ላይ አርባ ዓመት ሙሉ ሰላም ሆነ። የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን ወደ ተወለደበት ቦታ ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሴኬም የምትኖርም ቊባት ነበረችው፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአባቱም በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ፤ ይህም መቃብር የአቢዔዜር ጐሣ ከተማ በነበረችው በዖፍራ ይገኛል። ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንደገና ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት አጓድለው በዓሊም የተባሉትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ ለባዓልበሪትም ሰገዱ። የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው ሁሉ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ረሱ። ለእስራኤል ያደረገውን መልካም ነገር ሁሉ ካለማስታወሳቸው የተነሣ ለጌዴዎን ቤተሰብ ባለ ውለታዎች ሆነው አልተገኙም።
መሳፍንት 8:27-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፥ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ። ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች። የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ በሴኬም የምትኖረው ቁባቱም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ አለው። የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአቢዔዝራውያን ምድር ባለችው በዖፍራ፥ በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። ጌዴዎን ሞቶ ብዙም ሳይቈይ እስራኤላውያን የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፤ በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ የታደጋቸውን ጌታ አምላካቸውን አላሰቡትም። እንዲሁም ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተ ሰቡ ውለታ መላሽ ሆነው አልተገኙም።