የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 8

8
1የኤፍሬም ሰዎች፦ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም? አሉት። ጽኑ ጥልም ተጣሉት። 2እርሱም፦ እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዝር ወይን መከር አይሻልምን? 3እግዚአብሔር የምድያምን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፥ እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል? አላቸው። ይህን በተናገረ ጊዜ ቍጣቸው በረደ።
4ጌዴዎንም ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ ደርሶ ተሻገረ፥ ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር። 5የሱኮትንም ሰዎች፦ የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ሳሳድድ፥ ደክመዋልና እኔን ለተከተሉ ሕዝብ እንጀራ፥ እባካችሁ፥ ስጡ አላቸው። 6የሱኮትም አለቆች፦ እኛ ለሠራዊትህ እንጀራ እንድንሰጥ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? አሉ። 7ጌዴዎንም፦ እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ ሲሰጠኝ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኩርንችት ሥጋችሁን እገርፋለሁ አለ። 8ከዚያም ወደ ጵኒኤል ወጣ፥ ለጵኒኤልም ሰዎች እንዲሁ አላቸው፥ የጵንኤልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት። 9እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች ደግሞ፦ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ ብሎ ተናገራቸው።
10ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር በቀርቀር ነበሩ፥ ሰይፍ የሚመዝዙ መቶ ሀያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና ከምሥራቅ ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ አሥራ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ። 11ጌዴዎንም የድንኳን ተቀማጮች ባሉበት መንገድ በኖባህና በዮግብሃ በምሥራቅ በኩል ወጣ፥ ሠራዊቱም ተዘልሎ ነበርና ሠራዊቱን መታ። 12ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፥ እርሱም አሳደዳቸው፥ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዘ፥ ሠራዊቱንም ሁሉ አስደነገጠ።
13የኢዮአስ ልጅም ጌዴዎን ከሔሬስ ዳገት ከሰልፍ ተመለሰ። 14ከሱኮትም ሰዎች አንድ ብላቴና ይዞ ጠየቀው፥ እርሱም የሱኮትን አለቆችና ሽማግሌዎች ሰባ ሰባት ሰዎች ጻፈለት። 15ወደ ሱኮትም ሰዎች መጥቶ፦ ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? ብላችሁ የተላገዳችሁብኝ፥ ዛብሄልና ስልማና እነሆ፥ አለ። 16የከተማይቱንም ሽማግሌዎች ያዘ፥ የምድረ በዳንም እሾህና ኵርንችት ወስዶ የሱኮትን ሰዎች ገረፋቸው። 17የጵኒኤልንም ግንብ አፈረሰ፥ የከተማይቱንም ሰዎች ገደላቸው።
18ዛብሄልና ስልማናን፦ በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ? አላቸው። እነርሱም፦ እንደ አንተ ያሉ ነበሩ፥ አንተንም ይመስሉ ነበር፥ መልካቸውም እንደ ንጉሥ ልጆች መልክ ነበረ ብለው መለሱለት። 19እርሱም፦ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፥ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ አልገድላችሁም ነበር አለ። 20በኩሩንም ዬቴርን፦ ተነሥተህ ግደላቸው አለው፥ ብላቴናው ግን ገና ብላቴና ነበረና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። 21ዛብሄልና ስልማናም፦ የሰው ኃይሉ እንደ ሰውነቱ ነውና አንተ ተነሥተህ ውደቅብን አሉት። ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደለ፥ በግመሎቻቸውም አንገት የነበሩትን ሥሉሴዎች ማረከ።
22የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን፦ ከምድያም እጅ አድነኸናልና አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም ደግሞ ግዙን አሉት። 23ጌዴዎንም፦ እኔ አልገዛችሁም፥ ልጄም አይገዛችሁም፥ እግዚአብሔር ይገዛችኋል አላቸው። 24እስማኤላውያንም ስለ ነበሩ የወርቅ ጉትቻ ነበራቸውና ጌዴዎን፦ ሁላችሁ ከምርኮአችሁ ጉትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ አላቸው። 25እነርሱም፦ ፈቅደን እንሰጥሃለን ብለው መለሱለት። መጎናጸፊያም አነጠፉ፥ ሰውም ሁሉ የምርኮውን ጉትቻ በዚያ ላይ ጣለ። 26የለመነውም የወርቅ ጉትቻ ሚዛኑ፥ ከአምባሩ፥ ከድሪውም፥ የምድያምም ነገሥታት ከለበሱት ከቀዩ ቀሚስ፥ በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ሥሉሴዎች ሌላ፥ ሺህ ሰባት መቶ ሰቅለ ወርቅ ነበረ። 27ጌዴዎንም ኤፉድ አድርጎ አሠራው፥ በከተማውም በዖፍራ አኖረው፥ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎት አመነዘረበት፥ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ። 28ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረደ፥ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፥ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች።
29የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። 30ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከወገቡ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት። 31በሴኬምም የነበረችው ቁባቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፥ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። 32የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፥ በአቢዔዝራውያንም ከተማ በዖፍራ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ።
33እንዲህም ሆነ፥ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ በኣሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፥ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ። 34የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፥ 35እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ለጌዴዎን ለይሩበኣል ቤት ወረታ አላደረጉም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ