የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 11:1-40

መሳፍንት 11:1-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ገለ​ዓ​ዳ​ዊ​ዉም ዮፍ​ታሔ ጽኑዕ ኀያል ሰው የጋ​ለ​ሞታ ሴትም ልጅ ነበረ። ለገ​ለ​ዓ​ድም ዮፍ​ታ​ሔን ወለ​ደ​ች​ለት። የገ​ለ​ዓ​ድም ሚስት ወን​ዶች ልጆ​ችን ወለ​ደ​ች​ለት፤ ልጆ​ች​ዋም ባደጉ ጊዜ ዮፍ​ታ​ሔን፥ “የሌላ ሴት ልጅ ነህና በአ​ባ​ታ​ችን ቤት አት​ወ​ር​ስም” ብለው አስ​ወ​ጡት። ዮፍ​ታ​ሔም ከወ​ን​ድ​ሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀ​መጠ፤ ድሆች ሰዎ​ችም ተሰ​ብ​ስ​በው ዮፍ​ታ​ሔን ተከ​ተ​ሉት። ከዚ​ያም ወራት በኋላ የአ​ሞን ልጆች እስ​ራ​ኤ​ልን ተዋ​ጉ​አ​ቸው። የገ​ለ​ዓድ ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ችም ዮፍ​ታ​ሔን ከጦብ ምድር ለማ​ም​ጣት ሄዱ። ዮፍ​ታ​ሔ​ንም፥ “ና፥ ከአ​ሞን ልጆች ጋር እን​ድ​ን​ዋጋ መስ​ፍን ሁነን” አሉት። ዮፍ​ታ​ሔም የገ​ለ​ዓ​ድን ሽማ​ግ​ሌ​ዎች፥ “የጠ​ላ​ች​ሁኝ፥ ከአ​ባ​ቴም ቤት ያስ​ወ​ጣ​ች​ሁኝ እና​ንተ አይ​ደ​ላ​ች​ሁ​ምን? አሁን በተ​ጨ​ነ​ቃ​ችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣ​ችሁ?” አላ​ቸው። የገ​ለ​ዓ​ድም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ዮፍ​ታ​ሔን፥ “እን​ዲህ አይ​ደ​ለም፤ ከእኛ ጋር እን​ድ​ት​ወጣ፥ ከአ​ሞ​ንም ልጆች ጋር እን​ድ​ቷጋ፥ ስለ​ዚህ አሁን ወደ አንተ ተመ​ል​ሰን መጣን፤ በገ​ለ​ዓ​ድም ሰዎች ሁሉ ላይ አለ​ቃ​ችን ትሆ​ና​ለህ” አሉት። ዮፍ​ታ​ሔም የገ​ለ​ዓ​ድን ሽማ​ግ​ሌ​ዎች፥ “ከአ​ሞን ልጆች ጋር ለመ​ዋ​ጋት ብት​ወ​ስ​ዱኝ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእጄ አሳ​ልፎ ቢሰ​ጣ​ቸው፥ እኔ አለ​ቃ​ችሁ እሆ​ና​ለ​ሁን?” አላ​ቸው። የገ​ለ​ዓ​ድም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ዮፍ​ታ​ሔን፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በመ​ካ​ከ​ላ​ችን ምስ​ክር ይሁን፤ በር​ግጥ እንደ ቃልህ እና​ደ​ር​ጋ​ለን” አሉት። ዮፍ​ታ​ሔም ከገ​ለ​ዓድ ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ጋር ሄደ፤ ሕዝ​ቡም መስ​ፍን ይሆ​ና​ቸው ዘንድ በላ​ያ​ቸው አለቃ አድ​ር​ገው ሾሙት፤ ዮፍ​ታ​ሔም ቃሉን ሁሉ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በመ​ሴፋ ተና​ገረ። ዮፍ​ታ​ሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ፥ “ሀገ​ሬን ለመ​ው​ጋት ወደ እኔ የም​ት​መጣ አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ?” ብሎ መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ። የአ​ሞ​ንም ልጆች ንጉሥ የዮ​ፍ​ታ​ሔን መል​እ​ክ​ተ​ኞች፥ “እስ​ራ​ኤል ከግ​ብፅ በወጣ ጊዜ ከአ​ር​ኖን ጀምሮ እስከ ያቦ​ቅና እስከ ዮር​ዳ​ኖስ ድረስ ምድ​ሬን ስለ ወሰደ ነው፤ አሁ​ንም በሰ​ላም መል​ሱ​ልኝ” ብሎ መለ​ሰ​ላ​ቸው። ዮፍ​ታ​ሔም የላ​ካ​ቸው ወደ ዮፍ​ታሔ ተመ​ለሱ፤ ዮፍ​ታ​ሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን እንደ ገና ላከ፤ እን​ዲ​ህም አለው፦ ዮፍ​ታሔ እን​ዲህ ይላል፥ “እስ​ራ​ኤል ከግ​ብፅ በወጡ ጊዜ የሞ​ዓ​ብን ምድር፥ የአ​ሞ​ን​ንም ልጆች ምድር አል​ወ​ሰ​ዱም፤ ነገር ግን እስ​ራ​ኤል በም​ድረ በዳ እስከ ኤር​ትራ ባሕር ሄዱ፤ ወደ ቃዴ​ስም ደረሱ፤ እስ​ራ​ኤል ወደ ኤዶ​ም​ያስ ንጉሥ፦ ‘በም​ድ​ርህ እን​ዳ​ልፍ፥ እባ​ክህ፥ ፍቀ​ድ​ልኝ’ ብሎ መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ የኤ​ዶ​ም​ያ​ስም ንጉሥ እንቢ አለ። እን​ዲ​ሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ ላከ፤ እር​ሱም እንቢ አለ። እስ​ራ​ኤ​ልም በቃ​ዴስ ተቀ​መጠ። በም​ድረ በዳም በኩል አለፈ፤ የኤ​ዶ​ም​ያ​ስ​ንና የሞ​ዓ​ብ​ንም ምድር ዞሩ፤ ከሞ​ዓብ ምድ​ርም በም​ሥ​ራቅ በኩል መጡ፤ በአ​ር​ኖ​ንም ማዶ ሰፈሩ፤ አር​ኖ​ንም የሞ​ዓብ ድን​በር ነበ​ረና ወደ ሞዓብ ድን​በር አል​ገ​ቡም። እስ​ራ​ኤ​ልም ወደ አሞ​ራ​ዊው ወደ ሐሴ​ቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ እስ​ራ​ኤ​ልም፦ ‘በም​ድ​ርህ በኩል ወደ ስፍ​ራ​ችን፥ እባ​ክህ፥ አሳ​ል​ፈን’ አለው። ሴዎ​ንም እስ​ራ​ኤል በድ​ን​በሩ እን​ዲ​ያ​ልፍ እንቢ አለ፤ ነገር ግን ሴዎን ሕዝ​ቡን ሁሉ ሰበ​ሰበ፤ በኢ​ያ​ሴ​ርም ሰፈረ፤ ከእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ጋር ተዋጋ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሴዎ​ን​ንና ሕዝ​ቡን ሁሉ በእ​ስ​ራ​ኤል እጅ አሳ​ልፎ ሰጠ፤ ገደ​ሉ​አ​ቸ​ውም፤ እስ​ራ​ኤ​ልም በዚያ ምድር ተቀ​ም​ጠው የነ​በ​ሩ​ትን የአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያ​ንን ምድር ሁሉ ወረሱ። ከአ​ር​ኖ​ንም እስከ ያቦቅ ድረስ፥ ከም​ድረ በዳ​ውም እስከ ዮር​ዳ​ኖስ ድረስ የአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያ​ንን አው​ራጃ ሁሉ ወረሱ። አሁ​ንም የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከሕ​ዝቡ ከእ​ስ​ራ​ኤል ፊት አሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያ​ንን አስ​ወ​ገደ፤ አን​ተም በተ​ራህ ትወ​ር​ሳ​ለ​ህን? አም​ላ​ክህ ኮሞስ የሚ​ሰ​ጥ​ህን የም​ት​ወ​ርስ አይ​ደ​ለ​ህ​ምን? እኛም አም​ላ​ካ​ችን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከፊ​ታ​ችን ያስ​ወ​ጣ​ቸ​ውን የእ​ነ​ር​ሱን ምድር የም​ን​ወ​ርስ አይ​ደ​ለ​ን​ምን? ወይስ ዛሬ ከሞ​ዓብ ንጉሥ ከሴ​ፎር ልጅ ከባ​ላቅ አንተ ትሻ​ላ​ለ​ህን? ወይስ እርሱ ከእ​ስ​ራ​ኤል ጋር ተጣ​ላን? ወይስ ተዋ​ጋ​ውን? እስ​ራ​ኤ​ልም በሐ​ሴ​ቦ​ንና በመ​ን​ደ​ሮ​ችዋ፥ በአ​ሮ​ዔ​ርና በመ​ን​ደ​ሮ​ችዋ፥ በአ​ር​ኖ​ንም አቅ​ራ​ቢያ ባሉት ከተ​ሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀ​ምጦ በነ​በረ ጊዜ፥ በዚያ ዘመን ስለ ምን አላ​ዳ​ን​ሃ​ቸ​ውም ነበር? እኔ አል​በ​ደ​ል​ሁ​ህም፤ አንተ ግን ከእኔ ጋር ትዋጋ ዘንድ ክፉ አታ​ድ​ር​ግ​ብኝ፤ ፈራጁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በእ​ስ​ራ​ኤል ልጆ​ችና በአ​ሞን ልጆች መካ​ከል ዛሬ ይፍ​ረድ።” ነገር ግን ዮፍ​ታሔ የላ​ከ​በ​ትን ቃል የአ​ሞን ልጆች ንጉሥ አል​ሰ​ማም፤ እን​ቢም አላ​ቸው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መን​ፈስ በዮ​ፍ​ታሔ ላይ መጣ፤ እር​ሱም የም​ናሴ ዕጣ ከም​ት​ሆን ከገ​ለ​ዓድ ምድ​ርና ከገ​ለ​ዓድ መሴፋ፥ ወደ አሞን ልጆች ማዶ ተሻ​ገረ። ዮፍ​ታ​ሔም፥ “በእ​ው​ነት የአ​ሞ​ንን ልጆች በእጄ አሳ​ል​ፈህ ብት​ሰ​ጠኝ፥ ከአ​ሞን ልጆች ዘንድ በደ​ኅና በተ​መ​ለ​ስሁ ጊዜ፥ ከቤቴ ደጅ ወጥቶ የሚ​ቀ​በ​ለ​ኝን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሥ​ዋ​ዕት አደ​ር​ገ​ዋ​ለሁ” ብሎ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስእ​ለት ተሳለ። ዮፍ​ታ​ሔም ሊዋ​ጋ​ቸው ወደ አሞን ልጆች ተሻ​ገረ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእጁ አሳ​ልፎ ሰጣ​ቸው። ከአ​ሮ​ዔ​ርም እስከ ሚኒ​ትና እስከ አቤ​ል​ክ​ራ​ሚም ድረስ ሃያ ከተ​ሞ​ችን በታ​ላቅ ሰልፍ አጠ​ፋ​ቸው። የአ​ሞ​ንም ልጆች በእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ፊት ተዋ​ረዱ። ዮፍ​ታ​ሔም ወደ መሴፋ ወደ ቤቱ ተመ​ለሰ፤ እነ​ሆም፥ ልጁ ከበሮ ይዛ እየ​ዘ​ፈ​ነች ልት​ቀ​በ​ለው ወጣች፤ ለእ​ር​ሱም የሚ​ወ​ድ​ዳት አን​ዲት ብቻ ነበ​ረች። ከእ​ር​ስ​ዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አል​ነ​በ​ረ​ውም። እር​ስ​ዋ​ንም ባየ ጊዜ ልብ​ሱን ቀድዶ፥ “ወዮ​ልኝ ልጄ ሆይ! ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አፌን ከፍ​ቻ​ለ​ሁና፥ ከዚ​ያ​ውም እመ​ለስ ዘንድ አል​ች​ል​ምና አሰ​ና​ከ​ል​ሽኝ፤ አስ​ጨ​ነ​ቅ​ሽ​ኝም” አላት። እር​ስ​ዋም፥ “አባቴ ሆይ፥ አፍ​ህን ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከከ​ፈ​ትህ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጠ​ላ​ቶ​ችህ በአ​ሞን ልጆች ላይ ተበ​ቅ​ሎ​ል​ሃ​ልና በአ​ፍህ እንደ ተና​ገ​ርህ አድ​ር​ግ​ብኝ” አለ​ችው። አባ​ቷ​ንም፥ “ይህ ነገር ይደ​ረ​ግ​ልኝ፤ ከዚህ ሄጄ በተ​ራ​ሮች ላይ እን​ድ​ወ​ጣና እን​ድ​ወ​ርድ፥ ከባ​ል​ን​ጀ​ሮቼም ጋር ለድ​ን​ግ​ል​ናዬ እን​ዳ​ለ​ቅስ ሁለት ወር አሰ​ና​ብ​ተኝ” አለ​ችው። እር​ሱም፥ “ሂጂ” አለ። ሁለት ወርም አሰ​ና​በ​ታት፤ ከባ​ል​ን​ጀ​ሮ​ች​ዋም ጋር ሄደች፤ በተ​ራ​ሮ​ችም ላይ ለድ​ን​ግ​ል​ናዋ አለ​ቀ​ሰች። ሁለት ወርም ከተ​ፈ​ጸመ በኋላ ወደ አባቷ ተመ​ለ​ሰች፤ ዮፍ​ታ​ሔም የተ​ሳ​ለ​ውን ስእ​ለት አደ​ረገ፤ እር​ስ​ዋም ወንድ አላ​ወ​ቀ​ችም ነበር። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሴቶች ልጆች ለገ​ለ​ዓ​ዳ​ዊዉ ለዮ​ፍ​ታሔ ልጅ በዓ​መት አራት ቀን ያለ​ቅ​ሱ​ላት ዘንድ በዓ​መት በዓ​መት ይሄዱ ነበር። ይህ​ችም በእ​ስ​ራ​ኤል ዘንድ ሥር​ዐት ሆነች።

መሳፍንት 11:1-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ኀያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች። እንደዚሁም የገለዓድ ሚስት ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፣ “ከሌላ ሴት ስለ ተወለድህ ከቤተ ሰባችን ምንም ዐይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት። ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፣ የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ። እነርሱም፣ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት። ዮፍታሔም፣ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳድዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው። የገለዓድ አለቆችም፣ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት። ዮፍታሔም፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው። የገለዓድ አለቆችም፣ “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ ያልኸውንም በርግጥ እናደርጋለን” አሉት። ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደገመው። ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፣ “ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ። የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፣ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው። ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደ ገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም። እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ በምድረ በዳ አድርጎ ወደ ቀይ ባሕር ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄደ። እስራኤልም ወደ ኤዶም ንጉሥ፣ ‘በአገርህ እንዳልፍ እባክህ ፍቀድልኝ’ በማለት መልእክተኞችን ላከበት፤ የኤዶም ንጉሥ ግን አልሰማውም። ለሞዓብ ንጉሥም እንደዚሁ ላከበት፤ እርሱም አልተቀበለውም፤ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ። “ቀጥሎም የኤዶምንና የሞዓብን ምድር በመዞር፣ በምድረ በዳው ተጕዞ ከሞዓብ በስተ ምሥራቅ በኩል በማለፍ ከአርኖን ማዶ ሰፈረ፤ የሞዓብም ድንበር አርኖን ስለ ነበር ወደ ሞዓብ ክልል አልገባም። “ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፣ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው። ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሰራዊቱንም ሰብስቦ በያሃድ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። “ከዚያም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ አሸነፏቸውም። እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤ ከአርኖን እስከ ያቦቅ፣ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ወረሱ። “እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳድዶ ካስወጣቸው፣ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ? አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ ነው፤ እኛም እንደዚሁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን እንወርሳለን። አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋር ተጣልቷልን? ወይስ ተዋግቷልን? እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮቿ፣ በአሮዔርና በመንደሮቿ፣ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያን ጊዜ ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር? እኔ አልበደልሁህም፤ አንተ ግን በእኔ ላይ ዘምተህ በድለኸኛል፤ እንግዲህማ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ።” የአሞን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከውን መልእክት ከምንም አልቈጠረውም። ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ። ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው። ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣ አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ እግዚአብሔርም እርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባ፣ ከዚያም ዐልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ። ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ። እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም። ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፣ “ወይኔ ልጄ ጕድ አደረግሽኝ! ጭንቅም ላይ ጣልሽኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁና” ብሎ በሐዘን ጮኸ። እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለእግዚአብሔር ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን እግዚአብሔር ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ። ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።” እርሱም፣ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋር ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ። ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች፤ እርሱም የተሳለውን አደረገ፤ ድንግልም ነበረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ በእስራኤል ልማድ ሆኖ፣ የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ሐዘን ያደርጉላታል።

መሳፍንት 11:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ጽኑዕ ኃያል ሰው የጋለሞታ ሴትም ልጅ ነበረ። ገለዓድም ዮፍታሔን ወለደ። የገለዓድም ሚስት ወንዶች ልጆችን ወለደችለት፥ ልጆችዋም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፦ የልዩ ሴት ልጅ ነህና በአባታችን ቤት አትወርስም ብለው አሳደዱት። ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀመጠ፥ ምናምንቴዎችም ሰዎች ተሰብስበው ዮፍታሔን ተከተሉት። ከዚያም ወራት በኋላ የአሞን ልጆች ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ነበር። የአሞንም ልጆች ከእስራኤል ጋር በተዋጉ ጊዜ የገለዓድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር ለማምጣት ሄዱ። ዮፍታሔንም፦ ና፥ ከአሞን ልጆች ጋር እንድንዋጋ አለቃችን ሁን አሉት። ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች፦ የጠላችሁኝ ከአባቴም ቤት ያሳደዳችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? አሁን በተጨነቃችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው። የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን፦ ከእኛ ጋር እንድትወጣ፥ ከአሞንም ልጆች ጋር እንድትዋጋ፥ ስለዚህ አሁን ወደ አንተ ተመልሰን መጣን፥ በገለዓድም ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃችን ትሆናለህ አሉት። ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች፦ ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው፥ እኔ አለቃችሁ እሆናለሁን? አላቸው። የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን፦ እግዚአብሔር በመካከላችን ምስክር ይሁን፥ በእርግጥ እንደ ቃልህ እናደርጋለን አሉት። ዮፍታሔም ከገለዓድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፥ ሕዝቡም በላያቸው ራስና አለቃ አደረጉት፥ ዮፍታሔም ቃሉን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በምጽጳ ተናገረ። ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ፦ አገሬን ለመውጋት ወደ እኔ የምትመጣ አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ብሎ መልክተኞችን ላከ። የአሞንም ልጆች ንጉሥ የዮፍታሔን መልክተኞች፦ እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ምድሬን ስለ ወሰደ ነው፥ አሁንም በሰላም መልሱልኝ ብሎ መለሰላቸው። ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ መልክተኞችን እንደ ገና ላከ፥ እንዲህም አለው፦ ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል የሞዓብን ምድር የአሞንንም ልጆች ምድር አልወሰደም፥ ነገር ግን ከግብፅ በወጣ ጊዜ፥ እስራኤልም በምድረ በዳ በኩል ወደ ኤርትራ ባሕር በሄደ ጊዜ፥ ወደ ቃዴስም በደረሰ ጊዜ፥ እስራኤል ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ፦ በምድርህ እንዳልፍ፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ ብሎ መልክተኞችን ላከ፥ የኤዶምያስም ንጉሥ አልሰማም። እንዲሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ ላከ፥ እርሱም አልፈቀደም። እስራኤልም በቃዴስ ተቀመጠ። በምድረ በዳም በኩል ሄዱ፥ የኤዶምያስንና የሞዓብንም ምድር ዞሩ፥ ከሞዓብ ምድርም በምሥራቅ በኩል መጡ በአርኖንም ማዶ ሰፈሩ፥ አርኖንም የሞዓብ ድንበር ነበረና የሞዓብን ድንበር አላለፉም። እስራኤልም ወደ አሞራዊው ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልክተኞችን ላከ፥ እስራኤልም፦ በምድርህ በኩል ወደ ስፍራችን፥ እባክህ፥ አሳልፈን አለው። ሴዎንም እስራኤል በድንበሩ እንዲያልፍ አላመነውም ነበር፥ ነገር ግን ሴዎን ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ በያሀጽም ሰፈረ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ መቱአቸውም፥ እስራኤልም በዚያ ምድር ተቀምጠው የነበሩትን የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሰ። ከአርኖንም እስከ ያቦቅ ድረስ ከምድረ በዳውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሱ። የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሞራውያንን አስወገደ፥ አንተም ምድሩን ትወርሳለህን? አምላክህ ካሞሽ የሚሰጥህን አትወርስምን? እኛም አምላካችን እግዚአብሔር ከፊታችን ያስወጣቸውን የእነርሱን ምድር እንወርሳለን። ወይስ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ አንተ ትሻላለህን? በውኑ እርሱ እስራኤልን ከቶ ተጣላውን? ወይስ ተዋጋውን? እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረ ጊዜ፥ በዚያ ዘመን ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር? እኔ አልበደልሁህም፥ አንተ ግን ከእኔ ጋር እየተዋጋህ በድለኸኛል፥ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆችና በአሞን ልጆች መካከል ዛሬ ይፍረድ። ነገር ግን ዮፍታሔ የላከበትን ቃል የአሞን ልጆች ንጉሥ አልሰማም። የእግዚአብሔርም መንፈስ በዮፍታሔ ላይ መጣ፥ እርሱም ገለዓድንና ምናሴን አለፈ፥ በገለዓድም ያለውን ምጽጳን አለፈ፥ ከምጽጳም ወደ አሞን ልጆች አለፈ። ዮፍታሔም፦ በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አቀርበዋለሁ ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ። ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች አለፈ፥ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው። ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሀያ ከተሞችን በታላቅ አገዳደል መታቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ። ዮፍታሄም ወደ ቤቱ ወደ ምጽጳ መጣ፥ እነሆም ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትገናኘው ወጣች፥ ለእርሱም አንዲት ብቻ ነበረች፥ ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም። እርስዋንም ባየ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ፦ አወይ ልጄ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር አፌን ከፍቻለሁና፥ ከዚያውም እመለስ ዘንድ አልችልምና በጣም አዋረድሽኝ አስጨነቅሽኝም አላት። እርስዋም፦ አባቴ ሆይ፥ አፍህን ለእግዚአብሔር ከከፈትህ፥ እግዚአብሔር በጠላቶችህ በአሞን ልጆች ላይ ተበቅሎልሃልና በአፍህ እንደ ተናገርህ አድርግብኝ አለችው። አባትዋንም፦ ይህ ነገር ይደረግልኝ፥ ከዚህ ሄጄ በተራሮች ላይ እንድወጣና እንድወርድ፥ ከባልንጀሮቼም ጋር ለድንግልናዬ እንዳለቅስ ሁለት ወር አሰናብተኝ አለችው። እርሱም፦ ሂጂ አለ። ሁለት ወርም አሰናበታት፥ ከባልንጀሮችዋም ጋር ሄደች፥ በተራሮችም ላይ ለድንግልናዋ አለቀሰች። ሁለትም ወር ከተፈጸመ በኋላ ወደ አባትዋ ተመለሰች፥ እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት፥ እርስዋም ወንድ አላወቀችም ነበር። የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።

መሳፍንት 11:1-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ከአንዲት ጋለሞታ ሴት የተወለደ ጀግና ወታደር ነበር፤ አባቱም ገለዓድ ይባል ነበር። የእርሱ አባት ገለዓድ ቀደም ብሎ ያገባት ሚስቱ የወለደችለት ሌሎች ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ወንድማቸውን ዮፍታሔን “አንተ ከሌላ ሴት የተወለድክ ስለ ሆንክ ከአባታችን ርስት ምንም ነገር መውረስ አይገባህም” ብለው ከቤት እንዲባረር አደረጉት። ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ሸሽቶ ጦብ ተብላ በምትጠራ ምድር ኖረ፤ እዚያ ጥቂት ወሮበሎች ተሰብስበው ተከተሉት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዐሞናውያን በእስራኤላውያን ላይ ዘመቱ። ይህም በሆነ ጊዜ የገለዓድ መሪዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር መልሰው ለማምጣት ሄዱ። ዮፍታሔንም፦ “ዐሞናውያንን መውጋት እንችል ዘንድ መጥተህ መሪያችን ሁን” አሉት። ዮፍታሔ ግን “እኔን ጠልታችሁ ከአባቴ ቤት ያባረራችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ወደ እኔ መምጣታችሁ ስለምንድነው?” አላቸው። እነርሱም ዮፍታሔን “አሁን እኛ ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከእኛ ጋር ዘምተህ ዐሞናውያንን እንድትወጋልንና የገለዓድ ሕዝብ ሁሉ መሪ እንድትሆን እንፈልጋለን” አሉት። ዮፍታሔም የገልዓድን ሽማግሌዎች፦ “እንግዲህ ወደ ቤት ከመለሳችሁኝ በኋላ እግዚአብሔር በዐሞናውያን ላይ ድልን በሚያጐናጽፈኝ ጊዜ እኔ የእናንተ መሪ እሆናለሁ” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ አንተ እንዳልከው እናደርጋለን” ብለው መለሱለት፤ ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ መሪዎች ጋር ሄደ። ሕዝቡም ገዢአቸውና መሪያቸው አደረጉት፤ ዮፍታሔም በምጽጳ በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ጉዳይ መስማማቱን ገለጠ። ከዚህ በኋላ ዮፍታሔ ወደ ዐሞን ንጉሥ መልእክተኞችን ልኮ “ከእኛ ጋር የተጣላህበት ምክንያት ምንድን ነው? አገራችንንስ የወረርከው ለምንድነው?” ብለው እንዲጠይቁት አደረገ። የዐሞንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች መልስ ሲሰጥ “እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ ከአርኖን ወንዝ እስከ ያቦቅ ወንዝ ያለውን ምድሬንና የዮርዳኖስንም ወንዝ ወሰዱብኝ፤ አሁን ግን በሰላም መመለስ ይኖርባችኋል” አላቸው። ዮፍታሔ እንደገና መልእክተኞችን ወደ ዐሞን ንጉሥ ላከ፤ እንዲህ በማለትም መልስ ሰጠው፤ “እስራኤላውያን የሞአብንም ሆነ የዐሞንን ምድር አልወሰዱም፤ እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ በበረሓው አቋርጠው ወደ ቀይ ባሕር ደረሱ፤ ከዚያም ወደ ቃዴስ አለፉ፤ ከዚያ በኋላ በምድሩ አልፈው እንዲሄዱ ይፈቅድላቸው ዘንድ ወደ ኤዶም ንጉሥ መልእክተኞች ላኩ፤ ነገር ግን የኤዶም ንጉሥ አልፈቀደላቸውም፤ የሞአብንም ንጉሥ እንዲሁ ጠየቁ፤ እርሱም ቢሆን በምድሩ አልፈው እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም፤ ስለዚህ እስራኤላውያን በቃዴስ ቈዩ፤ በረሓውንም በማቋረጥ ጒዞ ቀጥለው የኤዶምንና የሞአብን ምድር በመዞር ከሞአብ በስተምሥራቅና ከአርኖን ወንዝ ባሻገር ወዳለው ስፍራ መጥተው ሰፈሩ፤ ነገር ግን የሞአብ ወሰን ስለ ነበር የአርኖንን ወንዝ አልተሻገሩም፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን በሐሴቦን ሆኖ ወደሚገዛው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሲሖን መልእክተኞች ልከው በአገሩ በኩል አልፈው ወደ አገራቸው እንዲሄዱ አስጠየቁት፤ ሲሖን ግን እስራኤላውያን አልፈው እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም፤ እንዲያውም መላ ሠራዊቱን ሰብስቦ በያሐጽ በመስፈር ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እስራኤላውያን በሠራዊቱ ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረገ። በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን በዚያ አገር ይኖሩ የነበሩትን የአሞራውያንን ግዛት በሙሉ ወስደው የራሳቸው ርስት አደረጉት፤ በደቡብ ከአርኖን ወንዝ አንሥቶ በሰሜን እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ፥ እንዲሁም በምሥራቅ ከበረሓው አንሥቶ በምዕራብ እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ መላውን የአሞራውያን ግዛት ያዙ፤ ስለዚህ ለሕዝቡ ለእስራኤላውያን ሲል አሞራውያንን አባሮ ያስወጣ ራሱ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ፥ አንተ መልሰህ ልትወስድ ታስባለህን? አንተ አምላክህ ከሞሽ የሰጠህን ይዘህ ዐርፈህ አትቀመጥምን? እኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ ወርሰን እንኖራለን። ለመሆኑ አንተ የሞአብ ንጉሥ ከነበረው ከጺጶር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? እርሱ እንኳ እስራኤልን ከቶ አልተቋቋመም፤ እኛንም ይወጋ ዘንድ ወደ ጦርነት ለመውጣት አልደፈረም። ስለዚህ ሦስት መቶ ዓመት ሙሉ እስራኤል ሐሴቦንና መንደሮችዋን ዓሮዔርንና መንደሮችዋን፥ እንዲሁም በአርኖን ወንዝ ዳርቻ ያሉትን ከተሞች በሙሉ ወርሰው ኖረዋል፤ ታዲያ በነዚህ ዘመናት ሁሉ ስለምን መልሳችሁ አልወሰዳችኋቸውም ነበር? እኔ በበኩሌ ምንም አልበደልኩም፤ በእኔ ላይ ጦርነት በመክፈት ልትበድለኝ የተነሣሣህ አንተ ነህ፤ እንግዲህ ፈራጅ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ ዛሬ በእስራኤላውያንና በዐሞናውያን መካከል ውሳኔ ይሰጣል።” የዐሞን ንጉሥ ግን የዮፍታሔን መልእክት ከቁም ነገር አልቈጠረውም። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ዮፍታሔም በገለዓድና በምናሴ ግዛቶች መካከል አቋርጦ ሄደ፤ በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ምጽጳ አለፈ፤ ከዚያም ወደ ዐሞን ጒዞውን ቀጠለ። ለእግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “በዐሞናውያን ላይ ድልን ብታቀዳጀኝ ድል አድርጌ ከዘመቻ ወደ ቤቴ በደኅና ስመለስ ከቤት ወጥቶ ሊቀበለኝ የሚመጣው ለአንተ ይሆናል፤ እርሱንም ለአንተ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ከዚህም በኋላ ዮፍታሔ ዐሞናውያንን ለመውጋት ወንዙን ተሻግሮ ሄደ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድልን አጐናጸፈው። ከዓሮዔር ጀምሮ በሚኒት ዙሪያ እስካለው ስፍራ በአጠቃላይ ኻያ ከተሞችን፥ እንዲሁም እስከ አቤል ከራሚም ድረስ ያሉትን ሁሉ ደመሰሳቸው፤ በዚህም ዐይነት ዐሞናውያን በእስራኤላውያን ፊት ተዋረዱ። ዮፍታሔ በምጽጳ ወዳለው ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ሴት ልጁ አታሞ ይዛ እየጨፈረች ልትቀበለው ወጣች፤ ያለ እርስዋም ሌላ ወንድ ወይም ሴት ልጅ አልነበረውም። ባያትም ጊዜ በሐዘን ልብሱን በመቅደድ “ወዮ ልጄ! ልቤን በሐዘን ሰበርሽው! ለታላቅ ጭንቀትም ዳረግሽኝ፤ ለእግዚአብሔር ቃል ገብቼአለሁና ስለቴን ልመልሰውም አልችልም፤” አለ። እርስዋም “አባቴ ሆይ! ለእግዚአብሔር ቃል ገብተህ ከሆነስ፥ እግዚአብሔር ጠላቶችህን ዐሞናውያንን ስለ ተበቀለልህ በእኔ ላይ ልታደርግ ለእግዚአብሔር ቃል የገባኸውን ፈጽም!” አለችው። ነገር ግን አባትዋን እንዲህ ስትል ጠየቀችው፤ “ይህን አንድ ነገር ፍቀድልኝ፤ እንግዲህ አግብቼ ልጅ መውለድ ስለማልችል ከጓደኞቼ ጋር በተራራው ላይ ተዘዋውሬ ለድንግልናዬ እንዳለቅስ የሁለት ወር ጊዜ ፍቀድልኝ።” እርሱም እንድትሄድ ፈቅዶ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርስዋና ጓደኞችዋም ወደ ተራራዎች ወጡ፤ ከዚያም ባል አግብታ ልጆች የማትወልድ በመሆንዋ አለቀሱላት። ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባትዋ ቤት ተመልሳ መጣች፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃል የገባውን ስለት ፈጸመባት፤ እርስዋም ወንድ ያላወቀች ድንግል ነበረች። ከዚያም ጊዜ አንሥቶ፥ የእስራኤላውያን ወጣት ሴቶች ልጆች በየዓመቱ ለአራት ቀን ያኽል ከቤታቸው ርቀው እየሄዱ ለገለዓዳዊው ለዮፍታሔ ሴት ልጅ ማዘናቸውና ማልቀሳቸው የተለመደ ሆነ።

መሳፍንት 11:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ኃያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች። የገለዓድ ሚስትም ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፥ “ከሌላ ሴት ስለተወለድህ ከቤተሰባችን ምንም ዓይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት። ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፥ የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ። እነርሱም፥ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት። ዮፍታሔም፥ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው። የገለዓድ አለቆችም፥ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት። ዮፍታሔም፥ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና ጌታ በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በእርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው። የገለዓድ አለቆችም፥ “ጌታ ምስክራችን ነው፤ ያልከውንም በእርግጥ እናደርጋለን” አሉት። ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በጌታ ፊት ደገመው። ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፥ “ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ። የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፥ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው። ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም። እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በምድረ በዳ አድርጎ ወደ ቀይ ባሕር ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄደ። እስራኤልም ወደ ኤዶም ንጉሥ፥ ‘በአገርህ እንዳልፍ እባክህ ፍቀድልኝ’ በማለት መልእክተኞችን ላከበት፤ የኤዶም ንጉሥ ግን አልሰማውም። ለሞዓብ ንጉሥም እንደዚሁ ላከበት፤ እርሱም አልተቀበለውም፤ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ። “ቀጥሎም የኤዶምንና የሞዓብን ምድር በመዞር፥ በምድረ በዳው ተጉዞ ከሞዓብ በስተ ምሥራቅ በኩል በማለፍ ከአርኖን ማዶ ሰፈረ፤ የሞዓብም ድንበር አርኖን ስለ ነበር ወደ ሞዓብ ክልል አልገባም። “ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፥ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው። ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሠራዊቱንም ሰብስቦ በያሃጽ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። “ከዚያም የእስራኤል አምላክ ጌታ ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤” አሸነፏቸውም፤ እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤ ከአርኖን እስከ ያቦቅ፥ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ወረሱ። “እንግዲህ የእስራኤል አምላክ ጌታ አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳዶ ካስወጣቸው፥ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ? አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ አይደለምን? እኛስ እንደዚሁ አምላካችን ጌታ የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን ልንወርስ አይገባንምን? አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋር ተጣልቶአልን? ወይስ ተዋግቶአልን? እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያን ጊዜ ስለምን አልወሰዳችኋቸውም? እኔ አልበደልሁህም፤ አንተ ግን በእኔ ላይ ዘምተህ በድለኸኛል፤ እንግዲህማ ፈራጅ የሆነው ጌታ በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ።” የአሞን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከውን መልእክት ከምንም አልቈጠረውም። ከዚያም የጌታ መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ፤ ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው። ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለጌታ ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለጌታ ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ ጌታ እነርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባቢ ከዚያም አልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ። ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም። ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፥ “ወይኔ ልጄ ጉድ አደረግሽኝ ጭንቅም ላይ ጣልሺኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለጌታ ተስያለሁና” ብሎ በኀዘን ጮኸ። እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለጌታ ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን ጌታ ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ። ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።” እርሱም፥ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋር ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ። ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች፤ እርሱም የተሳለውን አደረገ፤ ድንግልም ነበረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ በእስራኤል ልማድ ሆኖ፥ የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ኀዘን ያደርጉላታል።