ኢሳይያስ 61:3-7
ኢሳይያስ 61:3-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ። የጥንት ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤ በቀድሞ ጊዜ የወደሙትን መልሰው ያቆማሉ፤ ከብዙ ትውልድ በፊት የወደሙትን ፍርስራሽ ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ። መጻተኞች የበግ መንጎቻችሁን ያግዳሉ፤ ባዕዳን በዕርሻችሁና በወይን ተክል ቦታችሁ ላይ ይሠሩላችኋል። እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤ የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤ በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ። ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣ ዕጥፍ ይቀበላሉ፤ በውርደታቸው ፈንታ፣ በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤ የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤ ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።
ኢሳይያስ 61:3-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምሥጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። ከጥንትም ጀምሮ ባድማ የነበሩትን ይሠራሉ ከቀድሞ የፈረሱትንም ያቆማሉ፥ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ። መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፥ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፥ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፥ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በክብራቸውም ትመካላችሁ። በእረፍታችሁ ፋንታ ሁለት እጥፍ ይሆንላችኋል፥ በውርደታችሁም ፋንታ ዕድል ፈንታችሁ ደስ ይላቸዋል፥ ስለዚህ በምድራቸው ሁለት እጥፍ ይገዛሉ፥ የዘላለምም ደስታ ይሆንላቸዋል።
ኢሳይያስ 61:3-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድም ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። ከጥንት ጀምሮ የፈረሱትን ይሠራሉ፤ ከቀድሞ ጀምሮ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደ ገና ያድሳሉ። መጻተኞችም መጥተው በጎቻችሁን ይጠብቃሉ፥ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፤ የአምላካችንም አገልጋዮች ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፤ በሀብታቸውም ትመካላችሁ። ሌላ ምድርን ይወርሳሉ፤ በራሳቸውም ዘለዓለማዊ ደስታ አላቸው።
ኢሳይያስ 61:3-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በጽዮን ለሚያለቅሱት ሰዎች በዐመድ ፈንታ የአበባ ጒንጒንን፥ በእንባቸው ምትክ የወይራ ዘይትን በኀዘን ፈንታ የደስታ ዘይትን፥ በዛለ መንፈሳቸው ፈንታ የምስጋና መጐናጸፊያን ለማስገኘት ላከኝ። እነርሱም ክብሩን እንዲገልጡ እግዚአብሔር የተከላቸው “የጽድቅ ዋርካዎች” ተብለው ይጠራሉ። እነርሱ የጥንት ፍርስራሾችን ይገነባሉ፤ ቀደም ብለው የወደሙትን እንደገና ይሠራሉ፤ በየትውልዱ የፈራረሱትን ከተሞች ያድሳሉ፤ የባዕድ አገር ሕዝቦች መንጋዎቻችሁን ያሰማራሉ፤ ምድራችሁን ያርሳሉ፤ የወይን ተክሎቻችሁንም ይንከባከባሉ። እናንተ ግን “የእግዚአብሔር ካህናትና የአምላካችን አገልጋዮች” ተብላችሁ ትጠራላችሁ። በሕዝቦች ሀብት ትደሰታላችሁ፤ በብልጽግናቸውም ትከብራላችሁ። ኀፍረታቸው እጥፍ ስለ ነበረ፤ ውርደትም የእነርሱ ዕድል ፈንታ መሆኑ ስለ ታወጀ ስለዚህ ድርሻቸው እጥፍ ይሆናል፤ ዘለዓለማዊ ደስታም ያገኛሉ።
ኢሳይያስ 61:3-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ለክብሩ የተከላቸው ጽድቃዊ የባሉጥ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች በአመድ ፋንታ አክሊልን እንዳደርግላቸው፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እንድሰጣቸው ልኮኛል። ከጥንትም ጀምሮ ባድማ የነበሩትን ይሠራሉ፥ ከቀድሞ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ይሠራሉ። መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፥ ባዕዳንም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። እናንተ ግን የጌታ ካህናት ትባላላችሁ፤ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በሀብታቸውም ትከብራላችሁ። በኀፍረታችሁ ፈንታ ሁለት እጥፍ ይሆንላችኋል፤ በውርደታችሁም ፋንታ ዕድል ፋንታችሁ ደስ ይለዋል፤ ስለዚህ የምድራቸውን ሁለት እጥፍ ይገዛሉ፥ የዘለዓለምም ደስታ ይሆንላቸዋል።