ኢሳይያስ 6:1-10
ኢሳይያስ 6:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ ምስጋናውም ቤቱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም በዙሪያው ቆመው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለቱ ክንፎቻቸው ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለቱም ክንፎቻቸው እግሮቻቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለቱም ክንፎቻቸው ይበርሩ ነበር። አንዱም ለአንዱ፥ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች” እያለ ይጮኽ ነበር። የመድረኩም መሠረት ከጩኸታቸው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፤ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። እኔም፥ “ከንፈሮች የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸው በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዐይኖች የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ!” አልሁ። ከሱራፌል አንዱ ወደ እኔ ተላከ፤ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና፥ “እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፤ ኀጢአትህም ተሰረየልህ” አለኝ። የጌታንም ድምፅ፥ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል?” ሲል ሰማሁ? እኔም፥ “እነሆኝ፥ ጌታዬ፥ እኔን ላከኝ” አልሁ። እርሱም፥ “ሂድ፤ ይህን ሕዝብ፦ መስማትን ትሰማላችሁ፥ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ፥ አትመለከቱምም” በላቸው አለኝ። እነዚህ ሕዝቦች በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ ልባቸውን አደንድነዋልና፥ ጆሮአቸውንም ደፍነዋልና፥ ዐይኖቻቸውንም ጨፍነዋልና።
ኢሳይያስ 6:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለና በከበረ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፍ ነበራቸው። በሁለት ክንፍ ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለት ክንፍ እግራቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበርሩ ነበር። እርስ በርሳቸው በመቀባበልም፣ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በክብሩ ተሞልታለች” ይሉ ነበር። ከድምፃቸው ጩኸት የተነሣ የመድረኩ መሠረት ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ። እኔም፣ “ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ነኝ፤ የምኖረውም ከንፈሮቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል ነው፤ ዐይኖቼም ንጉሡን፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አይተዋልና ጠፍቻለሁ፣ ወዮልኝ!” አልሁ። ከዚያም ከሱራፌል አንዱ፣ ከመሠዊያው ላይ የእሳት ፍም በጕጠት ወስዶ፣ ወደ እኔ እየበረረ መጣ። አፌንም በእሳቱ ነክቶ፣ “እነሆ፤ ይህ ከንፈሮችህን ነክቷል፤ በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኀጢአትህም ተሰርዮልሃል” አለኝ። ከዚያም የጌታ ድምፅ፣ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ሲል ሰማሁት። እኔም፣ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ!” አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ “ ‘መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም’ ብለህ ንገራቸው። የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤ ጆሯቸውን ድፈን፤ ዐይኖቻቸውንም ክደን፤ ይህ ካልሆነማ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው በመመለስ ይፈወሳሉ።”
ኢሳይያስ 6:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ንጉሡ ዖዝያም በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፥ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ፦ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮህ ነበር። የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። እኔም፦ ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን ስላዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ። ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና፦ እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፥ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ። የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። እርሱም፦ ሂድ፥ ይህን ሕዝብ፦ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፥ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።
ኢሳይያስ 6:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን አየሁት፤ እርሱም ከፍ ባለና ልዕልና ባለው ዙፋን ላይ ተቀምጦ መጐናጸፊያውም ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌል ተብለው የሚጠሩ መላእክትም በዙሪያው ነበሩ፤ እያንዳንዱ መልአክ ስድስት ክንፍ አለው፤ በሁለቱ ክንፎቹ ፊቱን ይሸፍናል፤ በሁለቱ ክንፎቹ እግሮቹን ሸፍኖ በሁለት ክንፎቹ ይበር ነበር፤ አንዱ መልአክ ከሌላው ጋር በመቀባበል፥ “የሠራዊት አምላክ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ነው! ክብሩም በዓለም ሁሉ የተሞላ ነው!” ይሉ ነበር። ከድምፃቸው ጩኸት የተነሣ የቤተ መቅደሱ መድረክ እስከ ሥር መሠረቱ ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ። እኔም “እነሆ አንደበቶቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል የምኖር፥ አንደበቴም የረከሰብኝ ሰው ነኝ፤ ንጉሡን የሠራዊት አምላክን በዐይኖቼ አይቼአለሁና መጥፋቴ ስለ ሆነ ወዮልኝ!” አልኩ። ከነዚያም መላእክት አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፤ ከመሠዊያው የወሰደው የእሳት ፍም የያዘበት ጒጠት በእጁ ነበር። በእሳቱም ፍም ከንፈሮቼን ነክቶ “እነሆ ይህ የእሳት ፍም ከንፈሮችህን ስለ ነካ በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኃጢአትህም ይቅር ተብሎልሃል” አለኝ። ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር “ማንን እልካለሁ? መልእክተኛ የሚሆንልንስ ማን ነው?” ሲል ሰማሁት፤ እኔም “እነሆ እኔ እሄዳለሁ! እኔን ላከኝ!” አልኩ። እርሱም “እንግዲያውስ ወደዚህ ሕዝብ ሂድና ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ ነገር ግን ልብ አታደርጉም’ በላቸው” አለኝ። ቀጥሎም “እንዳያዩ፥ እንዳይሰሙና እንዳያስተውሉ በዓይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ ተመልሰው እንዳይፈወሱ ይህን ሕዝብ ልቡ የደነደነ፥ ጆሮው የተደፈነ፥ ዐይኑም የተጨፈነ እንዲሆን አድርግ” አለኝ።
ኢሳይያስ 6:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለና በከበረ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፍ ነበራቸው። በሁለት ክንፍ ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለት ክንፍ እግራቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበሩ ነበር፤ እርስ በርሳቸው በመቀባበልም “ቅዱስ፤ ቅዱስ፤ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በክብሩ ተሞልታለች” ይሉ ነበር። ከድምፃቸው ጩኸት የተነሣ የመድረኩ መሠረት ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ። እኔም፤ “ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ነኝ፤ የምኖረውም ከንፈሮቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል ነው፤ ዐይኖቼም ንጉሡን፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አይቷልና ጠፍቻለሁ፤ ወዮልኝ!” አልሁ። ከዚያም ከሱራፌል አንዱ፤ ከመሠዊያው ላይ የእሳት ፍም በጉጠት ወስዶ፤ ወደ እኔ እየበረረ መጣ። አፌንም በእሳቱ ነክቶ፤ “እነሆ፤ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኃጢአትህም ተሰርዮልሃል” አለኝ። ከዚያም የጌታ ድምፅ፤ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ሲል ሰማሁት። እኔም፤ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ ‘መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም’ ብለህ ንገራቸው። የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤ ጆሮአቸውን ድፈን፤ ዐይኖቻቸውንም ክደን፤ ይህ ካልሆነማ፤ በዐይናቸው አይተው፤ በጆሮአቸው ሰምተው፤ በልባቸውም አስተውለው በመመለስ ይፈወሳሉ።”