ኢሳይያስ 58:1-10
ኢሳይያስ 58:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በኀይልህ ጩኽ፤ አትቈጥብ፤ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፤ ለሕዝቤ ኀጢአታቸውን፥ ለያዕቆብ ቤትም በደላቸውን ንገር። ነገር ግን ጽድቅን እንደሚያደርግ የአምላኩንም ፍርድ እንደማይተው ሕዝብ ዕለት ዕለት ይሹኛል፤ መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ። አሁንም እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። “ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅኸንም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ ድሃውንም በጡጫ ትማታላችሁ፤ በምትጮኹበት ጊዜ ድምፃችሁ እንዲሰማ ለእኔ ትጾማላችሁን? ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለሁም፤ እንደዚችም ባለች ቀን ሰው ራሱን ቢያሳዝን፥ አንገቱንም እንደ ቀለበት ቢያቀጥን፥ ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ቢተኛም፥ ይህ ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠ አይደለም። ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለም ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን የበደልን እስራት ፍታ፤ ጠማማውን ሁሉ አቅና፤ የተጨነቀውንም ሁሉ አድን፤ የዐመፃ ደብዳቤንም ተው። ለተራበውም እንጀራህን አጥግበው፤ ድሆችን ወደ ቤትህ አስገብተህ አሳድራቸው፤ የተራቈተውንም ብታይ አልብሰው፤ ከሥጋ ዘመድህ አትሸሽግ። ያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይወጣል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይጋርድሃል። ያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ፤ እርሱም፦ እነሆኝ፥ ይልሃል። የዐመፅ እስራትን ከመካከልህ ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ማንጐራጐርንም ብትተው፥ ከምግብህም ለተራበ ብታካፍል፥ የተራበች ሰውነትንም ብታጠግብ፥ ያንጊዜ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል፤ ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል።
ኢሳይያስ 58:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“በኀይል ጩኽ፤ ምንም አታስቀር፤ ድምፅህን እንደ መለከት አሰማ፤ ለሕዝቤ ዐመፃቸውን፣ ለያዕቆብም ቤት ኀጢአታቸውን ተናገር። ዕለት በዕለት ይፈልጉኛል፤ መንገዴን ለማወቅ የሚጓጉ ይመስላሉ፤ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ፣ የአምላኩንም ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ሁሉ፣ ተገቢ የሆነ ፍትሕ ይለምኑኛል፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ እንዲቀርብ የሚወድዱም ይመስላሉ። ‘አንተ ካልተቀበልኸው፣ ስለ ምን ብለን ጾምን? አንተ ከጕዳይ ካልቈጠርኸው፣ ስለ ምን ራሳችንን አዋረድን?’ ይላሉ። “ሆኖም በጾማችሁ ቀን የልባችሁን ታደርጋላችሁ፤ ሠራተኞቻችሁንም ትበዘብዛላችሁ። ጾማችሁ በጥልና በክርክር፣ በግፍ ጡጫና በመደባደብ ይፈጸማል፤ ከእንግዲህ ዛሬ እንደምትጾሙት ጾማችሁ፣ ድምፃችሁ ወደ ላይ እንደሚሰማ ተስፋ አታድርጉ። እኔ የመረጥሁት ጾም እንዲህ ዐይነቱን ነውን? ሰውስ ራሱን የሚያዋርደው በእንዲህ ያለው ቀን ብቻ ነውን? እንደ ደንገል ራስን ዝቅ ማድረግ ነውን? ወይስ ማቅ ለብሶ በዐመድ ላይ መንከባለል ነውን? ታዲያ ጾም ብለህ የምትጠራው ይህን ነውን? እግዚአብሔርስ የሚቀበለው እንዲህ ያለውን ቀን ነውን? “እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቈተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሣው አይደለምን? ይህ ከሆነ ብርሃንህ እንደ ንጋት ጮራ ይፈነጥቃል፤ ፈውስህ ፈጥኖ ይደርሳል፤ ጽድቅህ ቀድሞህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔር ክብር ደጀን ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ትጣራለህ፤ እግዚአብሔርም ይመልስልሃል፤ ለርዳታ ትጮኻለህ፤ እርሱም፣ ‘አለሁልህ’ ይልሃል። “የጭቈና ቀንበር፣ የክፋትን ንግግርና ጣት መቀሰርን ከአንተ ብታርቅ፣ ለተራበው ብትራራለት፣ የተገፉት እንዲጠግቡ ብታደርግ፣ ብርሃንህ በጨለማ ያበራል፤ ሌሊትህም እንደ ቀትር ፀሓይ ይሆናል።
ኢሳይያስ 58:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር። ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ፥ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፥ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለሁ? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለንም? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፥ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፥ ባታንጐራጕርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል።
ኢሳይያስ 58:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ድምፅህን ሳትቈጥብ ጩኽ! ድምፅህ እንደ እምቢልታ ከፍ ይበል! ለሕዝቤ ለእስራኤል ዐመፃቸውንና ኃጢአታቸውን ንገራቸው። ሆኖም ዕለት በዕለት ይሹኛል፤ መንገዶቼንም ማወቅ ደስ ይላቸዋል፤ ጽድቅን እንደሚያዘወትሩና የእኔን የአምላካቸውን ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ከእኔ ትክክለኛውን ፍርድ ይለምናሉ፤ ወደ እኔ ወደ አምላክም በመቅረብ ይደሰታሉ።” ሕዝቡም “እነሆ እኛ እንጾማለን፤ አንተ ግን አትመለከተንም፤ የማትመለከተንስ ከሆነ ሰውነታችንን ለምን እናዋርዳለን?” ይላሉ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “እነሆ እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ የልባችሁን ፈቃድ ትፈጽማላችሁ፤ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ትጨቊናላችሁ፤ የጾማችሁ መጨረሻው ጠብና ጭቅጭቅ ስለ ሆነ ጭካኔ በተሞላበት ቡጢ ትማታላችሁ፤ እንደዚህ አድርጋችሁ የምትጾሙት ጾም ጸሎታችሁን በላይ በሰማይ እንዲሰማ አያደርገውም። እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ ሰውነታችሁን ታጐሳቊላላችሁ፤ ራሳችሁን እንደ ሸምበቆ ዝቅ ታደርጋላችሁ፤ አመድ ነስንሳችሁ፥ ማቅም አንጥፋችሁ ትተኛላችሁ? ታዲያ እናንተ ጾም የምትሉት ይህን ነውን? እኔስ በዚህ ዐይነቱ ጾም ደስ የሚለኝ ይመስላችኋልን? “እኔ የምደሰትበት ጾም የጭቈና ሰንሰለትና የፍትሕ መጓደል ቀንበር ታላሉ ዘንድ፥ ቀንበሩን ሰብራችሁ የተጨቈኑትን ነጻ ታወጡ ዘንድ አይደለምን? ምግባችሁን ከተራበ ሰው ጋር እንድትካፈሉ፥ ማደሪያ የሌለውን ድኻ በቤታችሁ እንድትቀበሉ፥ የተራቈቱትን እንድታለብሱ፥ ከቅርብ ዘመዶቻችሁም ራሳችሁን እንዳትደብቁ አይደለምን? “ይህን ብታደርጉ ብርሃናችሁ እንደ ንጋት ብርሃን ያበራል፤ ፈውሳችሁም በፍጥነት ይመጣል፤ ፈራጃችሁ በፊታችሁ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔር ክብር የኋላ ደጀን ይሆናችኋል። ከዚያ በኋላ ትጸልያላችሁ፤ እኔም ጸሎታችሁን እሰማለሁ፤ የእርዳታ ጩኸት ትጮኻላችሁ፤ እኔም አለሁ እላችኋለሁ፤ እናንተ የጭቈናን ቀንበር ብታስወግዱ፥ የጣት ጥቆማንና የተንኰልን ንግግር ብታቆሙ፥ ምግባችሁን ለተራበ ብታካፍሉ፥ የተቸገሩ ሰዎችን ፍላጎት ብታረኩ፥ ብርሃናችሁ በጨለማ ያበራል፤ ጨለማችሁም እንደ ቀትር ብርሃን ይሆናል።
ኢሳይያስ 58:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር። ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል፤ መንገዴንም ለማወቅ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝቦች እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወዳሉ። “ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ለማሰማት ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነው? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነው? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ እንዲያደርግ፥ ማቅንና አመድንም በበታቹ እንዲያነጥፍ ነው? በውኑ ይህን ጾም፥ በጌታ ዘንድ የተወደደ ቀን ብለህ ትጠራዋለህ? እኔስ የመረጥሁት ጾም፥ የበደልን እስራት እንድትፈቱ፥ የቀንበርንስ ጠፍር እንድትለቁ፥ የተገፉትን አርነት እንድታወጡ፥ ቀንበሩን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ እንድትቈርስ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ እንድታስገባ፥ የተራቈተውን ብታይ እንድታለብሰው፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የጌታም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ ጌታም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ በጣትህም መጠቆም ብትተው፥ ባታንጐራጉርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል።