ኢሳይያስ 55:1-13
ኢሳይያስ 55:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ሂዱ፤ ገንዘብም የሌላችሁ ሂዱና ግዙ፤ ብሉ፤ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ጠጡ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፤ በረከትንም ብሉ፤ ሰውነታችሁም በበረከት ደስ ይበለው። ስሙኝ፤ ጎዳናዬን ተከተሉ፤ አድምጡኝም፤ ሰውነታችሁም በበረከት ትኖራለች፤ የታመነችዪቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘለዓለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን አደረግሁት። እነሆ፥ የማያውቁህ ሕዝብ ይጠሩሃል፤ የእስራኤል ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ በአንተ ይማጠናሉ። እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን፥ በደለኛም ዐሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ፤ እርሱም ይምረዋል፤ እርሱ ብዙ በደላችሁን ይተውላችኋልና። ዐሳቤ እንደ ዐሳባችሁ፥ መንገዴም እንደ መንገዳችሁ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር። ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ፥ ዐሳቤም ከዐሳባችሁ የራቀ ነው። ብዙ ዝናምና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርን ለሚዘራ፥ እህልንም ለምግብ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ነው፤ የምሻውን እስኪያደርግ ድረስ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም፤ መንገዴንና ትእዛዜን አከናውናለሁ። እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሐሤትም ትማራላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በደስታ ሊቀበሏችሁ ይዘላሉ፤ የሜዳም ዛፎች ሁሉ በቅርንጫፎቻቸው ያጨበጭባሉ። በእሾህም ፋንታ ጥድ፥ በኵርንችትም ፋንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ የእግዚአብሔርም ስም ለዘለዓለም በማይጠፋ ምልክት ይመሰገናል።
ኢሳይያስ 55:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም! ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘባችሁን እንጀራ ባልሆነ ነገር ላይ ለምን ታጠፋላችሁ? በማያጠግብስ ነገር ላይ ለምን ጕልበታችሁን ትጨርሳላችሁ? ስሙ፤ እኔን ስሙኝ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤ ነፍሳችሁም በጥሩ ምግብ ትደሰታለች። ጆሯችሁን ከፍታችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤ ነፍሳችሁም እንድትኖር አድምጡኝ። ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣ ከእናንተም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ። እነሆ፤ እርሱን ለሕዝቦች ምስክር፣ መሪ፣ የጦር አዝማችም አድርጌዋለሁ። እነሆ፤ የማታውቃቸውን መንግሥታት ትጠራለህ፤ የማያወቁህ መንግሥታት በፍጥነት ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣ በክብሩ ከፍ ከፍ አድርጎሃል።” እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት። ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና። “ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣ መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለምና” ይላል እግዚአብሔር። “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው። ዝናምና በረዶ ከሰማይ ወርዶ፣ ምድርን በማራስ፣ እንድታበቅልና እንድታፈራ ለዘሪው ዘር፣ ለበላተኛም እንጀራ እንድትሰጥ ሳያደርግ፣ ወደ ላይ እንደማይመለስ ሁሉ፣ ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል። በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኰረብቶች፣ በፊታችሁ በእልልታ ይዘምራሉ፤ የሜዳ ዛፎች ሁሉ፣ ያጨበጭባሉ። በእሾኽ ፈንታ የጥድ ዛፍ፣ በኵርንችት ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል። ይህም የእግዚአብሔር መታሰቢያ፣ ሊጠፋ የማይችል፣ የዘላለም ምልክት ይሆናል።”
ኢሳይያስ 55:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፥ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፥ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፥ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘላለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ። እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣሉ። እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፥ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፥ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፥ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፥ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። በእሾህም ፈንታ ጥድ በኵርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፥ ለእግዚአብሔርም መታሰቢያና ለዘላለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።
ኢሳይያስ 55:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሃው ኑ! የምትገዙበት ገንዘብ የሌላችሁ ኑና ገዝታችሁ ብሉ! ኑና ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ ወተትና የወይን ጠጅን ግዙ። ለማይጠቅም ምግብ ገንዘባችሁን ለምን ታወጣላችሁ? ለማያጠግብ ነገር ጒልበታችሁን ለምን ታባክናላችሁ? አሁንም በጥንቃቄ አድምጡኝና መልካም የሆነውን ምግብ ብሉ፤ በምርጥ ምግብም ራሳችሁን አስደስቱ። “ጆሮአችሁን አዘንብላችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ቃሌን አድምጡ፤ ዳዊትን እንደ ወደድኩት እናንተን በታማኝነት ለመውደድ ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን እገባለሁ። እነሆ እርሱን ለሕዝቦች ምስክር፥ መሪና አለቃ አድርጌዋለሁ። እኔ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክህ ስላከበርኩህ እነሆ፥ የማታውቃቸውን ሕዝቦች ትጠራለህ፤ የማያውቁህም ሕዝቦች ወደ አንተ ይፈጥናሉ።” በሚገኝበት ጊዜ እግዚአብሔርን ፈልጉት፤ በሚቀርብበትም ጊዜ ጥሩት። ክፉዎች አካሄዳቸውን፥ ኃጢአተኞች ክፉ ሐሳባቸውን ይተዉ፤ ምሕረቱ ብዙ ስለ ሆነ ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፥ መንገዴም እንደ መንገዳችሁ አይደለም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ መንገዴ ከመንገዳችሁ፥ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እጅግ ከፍ ያለ ነው። “ዝናብና ደቃቅ በረዶ ከሰማይ ወርደው ምድርን በማርካት ፍሬ እንድታፈራ እንደሚያደርጓትና ለዘሪው ዘርን፥ ለበላተኛውም ምግብን ሳይሰጡ ወደ ሰማይ እንደማይመለሱ፥ ከእኔ አንደበት የሚወጣውም ቃል እንደዚሁ ነው። እርሱ የላክሁትን ጉዳይ ሳያከናውንና ተልእኮውን ሳይፈጽም ወደ እኔ አይመለስም። “እናንተም ከባቢሎን በደስታ ወጥታችሁ፥ በሰላም ወደ ሀገራችሁ እንድትመለሱ ትደረጋላችሁ፤ ተራራዎችና ኰረብቶች በፊታችሁ በመዘመር ይፈነድቃሉ፤ የሜዳ ዛፎችም በእጆቻቸው ያጨበጭባሉ። በእሾኽ ፈንታ ዝግባ በኲርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያና ለዘለዓለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።”
ኢሳይያስ 55:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። እንጀራ ላልሆነ ነገር ገንዘብን ለምን ታባክናላችሁ፥ የድካማችሁንም ዋጋ በማያጠግብ ነገር ለምን ትለውጣላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ሰውነታችሁ በሕይወት እንድትኖር ስሙኝ፥ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘለዓለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ። እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ ጌታ የማያውቅህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣል። ጌታ በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ ጌታም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፤ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል ጌታ። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ እንድታበቅልና እንድታፈራም እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ፥ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል፤ የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልል ይላሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። በእሾህም ፈንታ ጥድ፥ በኩርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ ለጌታም መታሰቢያና ለዘለዓለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።