ኢሳይያስ 5:1-7
ኢሳይያስ 5:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁን የወይኔን ቦታ በተመለከተ የወዳጄን መዝሙር ለወዳጄ እዘምራለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ቦታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው። አጥር አጠርሁ፤ በዙሪያውም ቈፈርሁ፤ ድንጋዮችንም ለቅሜ አወጣሁ፤ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከልሁ፤ በመካከሉም ግንብ ሠራሁ፤ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማስሁለት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ጠበቅሁት፤ ዳሩ ግን እሾህን አፈራ። አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ። ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድን ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ጠበቅሁት፤ ነገር ግን እሾህን አፈራ። አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፤ ለብዝበዛም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፤ ለመራገጫም ይሆናል። ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይገረዝም፤ አይኰተኰትም፤ እንደ ጠፍ ቦታ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ደመናዎችን አዝዛለሁ። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፤ ተወዳጁ አዲስ ተክልም የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ያደርጋል ብየ እጠብቅ ነበር፤ እነሆም፥ ዐመፅን አደረገ፤ ጽድቅንም አይደለም፥ ጩኸትን እንጂ።
ኢሳይያስ 5:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለ ወዳጄ፣ ደግሞም ስለ ወይን ቦታው ልዘምር፤ ወዳጄ በለምለም ኰረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው። መሬቱን ቈፈረ፤ ድንጋይንም ለቅሞ አወጣ፤ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት። በመካከሉ መጠበቂያ ማማ ሠራ፤ የወይን መጭመቂያ ጕድጓድም አበጀ፤ ከዚያ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ ዐሰበ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ። “እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤ በእኔና በወይኔ ቦታ መካከል እስቲ ፍረዱ። ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር? መልካም የወይን ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቅ ለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ? እንግዲህ በወይኔ ቦታ ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤ ዐጥሩን እነቅላለሁ፤ ለጥፋት ይጋለጣል፤ ግንቡንም አፈርሳለሁ፣ መረጋገጫም ይሆናል። የማይኰተኰትና የማይታረም ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤ ኵርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤ ዝናብም እንዳይዘንብበት ደመናዎችን አዝዛለሁ።” የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የወይን ቦታው የእስራኤል ቤት ነው፤ የይሁዳ ሰዎችም የደስታው አትክልት ናቸው። ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤ ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።
ኢሳይያስ 5:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው። በዙሪያው ቆፈረ፥ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፥ ምርጥ የሆነውንም አረግ ተከለበት፥ በመካከሉም ግንብ ሠራ፥ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት፥ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ፥ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ። አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎችም ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ። ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስተማመን ስለምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ? አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፥ አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማሪያም ይሆናል፥ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል። ባድማ አደርገዋለሁ፥ አይቆረጥም፥ አይኮተኮትም፥ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፥ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ደመናዎችን አዝዛለሁ። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፥ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፥ ፍርድን ተስፋ ያደርግ ነበር፥ እነሆም፥ ደም ማፍሰስ ሆነ፥ ጽድቅንም ይተማመን ነበር፥ እነሆም፥ ጩኸት ሆነ።
ኢሳይያስ 5:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለ ወይኑ ተክል ለውዴ የፍቅር ዘፈን ልዝፈን ውዴ እጅግ ለም በሆነ ኰረብታ ላይ የወይን ተክል ነበረው። መሬቱን በመቈፈርና ድንጋዩንም ለቅሞ በማውጣት ምርጥ የሆነውን የወይን ሐረግ ተከለበት፤ በመካከሉም መጠበቂያ የሚሆን ማማ ሠራለት፤ ጒድጓድ ቆፍሮም የወይን ፍሬ መጭመቂያ አበጀለት። ከዚያን በኋላ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ ጠበቀ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ። ስለዚህም ወዳጄ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! በእኔና በወይን ተክል ቦታዬ መካከል ስላለው ነገር እስቲ ፍረዱ፤ ለመሆኑ እኔ ለእርሱ ያላደረግኹለት ነገር አለን? ከዚህስ ሌላ ላደርግለት የሚገባ ምን አለ? ታዲያ፥ መልካም ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቀው ስለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ? “እንግዲህ በወይን ቦታዬ ላይ የማደርገውን ልንገራችሁ፤ በዙሪያው ያለውን አጥር ነቃቅዬ ቅጽሩን አፈርሳለሁ፤ የምድር አራዊት እንዲበሉትና እንዲፈነጩበት አደርጋለሁ። ከዚያን በኋላ አይገረዝም፤ አይኰተኰትም፤ ስለዚህም አራሙቻ እንዲበቅልበት፥ በኲርንቺትና በእሾኽ እንዲሸፈን አደርጋለሁ፤ ዝናብም እንዳያዘንብበት ደመናን አዛለሁ።” ይህም የሠራዊት አምላክ የወይን ቦታ የተባለው የእስራኤል ሕዝብ ነው፤ እርሱም የይሁዳ ሕዝብ ደስ የሚሰኝበት ተክል ነው። መልካም ሥራ እንዲሠሩ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ በዚህ ፈንታ ነፍሰ ገዳዮች ሆኑ፤ ቅን ፍርድ ይሰጣሉ ብሎ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ እነርሱ ግን ፍርድን በማጓደላቸው የሕዝቡ ጩኸት በዛ።
ኢሳይያስ 5:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደግሞም ስለ ወይን ቦታው ልዘምር፤ ስለ ወዳጄ፤ ወዳጄ በለምለም ኮረብታ ላይ መሬቱን ቈፈረ፤ድንጋይንም ለቅሞ አወጣ፤ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት። በመካከሉ መጠበቂያ ማማ ሠራ፤ የወይን መጭመቂያ ጉድጓድም አበጀ፤ ከዚያ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ አሰበ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ። “እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤ በእኔና በወይኔ ቦታ መካከል እስቲ ፍረዱ። ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር? መልካም የወይን ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቅ ለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ? እንግዲህ በወይኔ ቦታ ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤ ዐጥሩን እነቅላለሁ፤ ለጥፋት ይጋለጣል፤ ግንቡንም አፈርሳለሁ፤ መረጋገጫም ይሆናል። የማይኰተኰትና የማይታረም ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤ ኩርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤ ዝናብም እንዳይዘንብበት ደመናዎችን አዝዛለሁ።” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የወይን ቦታ የእስራኤል ቤት ነው፤ የይሁዳ ሰዎችም የደስታው አትክልት ናቸው። ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤ ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።