የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 5:1-7

ትንቢተ ኢሳይያስ 5:1-7 አማ05

ስለ ወይኑ ተክል ለውዴ የፍቅር ዘፈን ልዝፈን ውዴ እጅግ ለም በሆነ ኰረብታ ላይ የወይን ተክል ነበረው። መሬቱን በመቈፈርና ድንጋዩንም ለቅሞ በማውጣት ምርጥ የሆነውን የወይን ሐረግ ተከለበት፤ በመካከሉም መጠበቂያ የሚሆን ማማ ሠራለት፤ ጒድጓድ ቆፍሮም የወይን ፍሬ መጭመቂያ አበጀለት። ከዚያን በኋላ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ ጠበቀ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ። ስለዚህም ወዳጄ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! በእኔና በወይን ተክል ቦታዬ መካከል ስላለው ነገር እስቲ ፍረዱ፤ ለመሆኑ እኔ ለእርሱ ያላደረግኹለት ነገር አለን? ከዚህስ ሌላ ላደርግለት የሚገባ ምን አለ? ታዲያ፥ መልካም ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቀው ስለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ? “እንግዲህ በወይን ቦታዬ ላይ የማደርገውን ልንገራችሁ፤ በዙሪያው ያለውን አጥር ነቃቅዬ ቅጽሩን አፈርሳለሁ፤ የምድር አራዊት እንዲበሉትና እንዲፈነጩበት አደርጋለሁ። ከዚያን በኋላ አይገረዝም፤ አይኰተኰትም፤ ስለዚህም አራሙቻ እንዲበቅልበት፥ በኲርንቺትና በእሾኽ እንዲሸፈን አደርጋለሁ፤ ዝናብም እንዳያዘንብበት ደመናን አዛለሁ።” ይህም የሠራዊት አምላክ የወይን ቦታ የተባለው የእስራኤል ሕዝብ ነው፤ እርሱም የይሁዳ ሕዝብ ደስ የሚሰኝበት ተክል ነው። መልካም ሥራ እንዲሠሩ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ በዚህ ፈንታ ነፍሰ ገዳዮች ሆኑ፤ ቅን ፍርድ ይሰጣሉ ብሎ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ እነርሱ ግን ፍርድን በማጓደላቸው የሕዝቡ ጩኸት በዛ።