ኢሳይያስ 49:8-12
ኢሳይያስ 49:8-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በወደድሁ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤ በድነትም ቀን እረዳሃለሁ። ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣ ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣ ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣ እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤ የተማረኩትን፣ ‘ኑ ውጡ’ በጨለማ ያሉትን፣ ‘ነጻ ሁኑ’ እንድትል አድርጌሃለሁ። “በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤ በተራቈተውም ኰረብታ ሁሉ ላይ መሰማሪያ ያገኛሉ። አይራቡም፤ አይጠሙም፤ የምድረ በዳ ትኵሳት ወይም የፀሓይ ቃጠሎ አይጐዳቸውም። የሚራራላቸው ይመራቸዋል፤ በውሃ ምንጭ ዳርም ያሰማራቸዋል። ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤ ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ። እነሆ፤ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ አንዳንዶች ከሰሜን ሌሎች ከምዕራብ፣ የቀሩት ደግሞ ከሲኒም ይመጣሉ።”
ኢሳይያስ 49:8-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በተመረጠችው ዕለት ሰምቼሃለሁ፤ ድኅነት በሚደረግበትም ቀን ረድቼሃለሁ፤ ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ፤ ምድርንም ታቀና ዘንድ፥ ውድማ የሆኑትን ርስቶች ትወርስ ዘንድ፤ የተጋዙትንም፦ ውጡ፤ በጨለማም የተቀመጡትን፦ ተገለጡ፤ ትል ዘንድ።” በመንገድም ሁሉ ላይ ይሰማራሉ፤ ማሰማሪያቸውም በጥርጊያ ጎዳና ሁሉ ላይ ይሆናል። የሚራራላቸውም ያጽናናቸዋልና፥ በውኃ ምንጮችም በኩል ይመራቸዋልና አይራቡም፤ አይጠሙም፤ የፀሐይ ትኩሳትም አይጐዳቸውም። ተራሮችንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤ ጎዳናዎችም ሁሉ መሰማርያ ይሆናሉ። እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከፋርስ ሀገር ይመጣሉ።
ኢሳይያስ 49:8-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፥ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፥ እጠብቅህማለሁ፥ ምድርንም ታቀና ዘንድ፥ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ፥ የተጋዙትንም፦ ውጡ በጨለማም የተቀመጡትን፦ ተገለጡ ትል ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። በመንገድም ላይ ይሰማራሉ፥ ማሰማርያቸውም በወና ኮረብታ ሁሉ ላይ ይሆናል። የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፥ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፥ አይጠሙም፥ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም። ተራሮቼንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፥ ጎዳኖቼም ከፍ ከፍ ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከሲኒም አገር ይመጣሉ።
ኢሳይያስ 49:8-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በመረጥኩት ሰዓት ለጸሎትህ መልስ እሰጥሃለሁ፤ በመዳንም ቀን እረዳሃለሁ፤ ምድሪቱን መልሰህ እንድታቋቋምና ውድማ የሆነውን መሬት እንድታከፋፍል ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። አንተም እስረኞችን ‘በነጻ ሂዱ!’ በጨለማ ያሉትን ‘ወደ ብርሃን ውጡ’ ትላቸዋለህ፤ በየመንገዱ ምግብ ያገኛሉ፤ ደረቅ በነበረውም ተራራ ላይ እንደ ፍየል ይሰማራሉ። መራብና መጠማትም አይደርስባቸውም፤ የሚያቃጥል ነፋስ ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም፤ ይህም የሚሆነው የሚራራላቸው እርሱ የውሃ ምንጭ ወደሚገኝበት ቦታ ስለሚመራቸው ነው። “ተራሮቼን ደልድዬ መንገድ አደርጋለሁ፤ ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ። ሕዝቦቼ ከሩቅ አገሮች ይመጣሉ፤ ከሰሜንና ከምዕራብ እንዲሁም ከሲኒም።”
ኢሳይያስ 49:8-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ጌታ እንዲህ ይላል፦ በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፥ በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፥ ምድርንም እንድታቀና፥ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች እንድታወርስ፥ የተሰሩትንም፦ ‘ውጡ’ በጨለማም የተቀመጡትን፦ ‘ተገለጡ’ እንድትል ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። በመንገድም ላይ ይሰማራሉ፥ ማሰማርያቸውም በገላጣ ኮረብታ ሁሉ ላይ ይሆናል። የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፥ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፥ አይጠሙም፥ የበረኅ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም። ተራሮቼንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፥ ጎዳኖቼም ከፍ ከፍ ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከሲኒም አገር ይመጣሉ።”