ኢሳይያስ 41:10-20
ኢሳይያስ 41:10-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፤ እረዳህማለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቃወሙህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ይዋረዱማል፤ እንዳልነበሩም ይሆናሉ፤ ጠላቶችህም ይጠፋሉ። የሚያሠቃዩህንም ሰዎች ትሻቸዋለህ፤ አታገኛቸውምም፤ እንዳልነበሩ ይሆናሉና፤ የሚዋጋህም የለም። ቀኝ እጅህን የያዝሁህ፥ እንዲህም የምልህ እኔ አምላክህ ነኝና። ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቍጥር ጥቂት የነበርህ እስራኤል ሆይ፥ እኔ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ፤ ኮረብቶችንም ታደቅቃቸዋለህ እንደ ገለባም ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስም ይጠርጋቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በእስራኤል ቅዱስ ደስ ይልሃል። ድሆችና ምስኪኖች ውኃ ይሻሉ፤ አያገኙምም፤ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፤ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በተራሮች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የተጠማችውንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን፥ ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ይህን ሁሉ እንደ ሠራ፥ የእስራኤልም ቅዱስ ይህን እንደ አሳየ ያውቁ ዘንድ፥ ያስተውሉም ዘንድ፥ ይረዱም ዘንድ፥ ያምኑም ዘንድ ነው።
ኢሳይያስ 41:10-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ። “እነሆ፤ የተቈጡህ ሁሉ፣ እጅግ ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም፤ የሚቋቋሙህ፣ እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም። ጠላቶችህን ብትፈልጋቸው እንኳ፣ አታገኛቸውም፤ የሚዋጉህም፣ እንዳልነበሩ ይሆናሉ። እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና አትፍራ ይልሃል፤ እረዳሃለሁ። አንተ ትል ያዕቆብ፣ ታናሽ እስራኤል ሆይ፤ ‘አትፍራ እኔ እረዳሃለሁ’ ” ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቤዥህ የእስራኤል ቅዱስ ነው። “እነሆ፣ አዲስ የተሳለና ባለጥርስ ማሄጃ አደርግሃለሁ፤ ተራሮችን ታሄዳለህ፤ ታደቅቃቸዋለህ፤ ኰረብቶችንም ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስ ጠርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል። አንተ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእስራኤል ቅዱስ ሞገስ ታገኛለህ። “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤ ጕረሯቸው በውሃ ጥም ደርቋል። ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤ እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም። በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣ በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮችን አፈልቃለሁ። ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣ የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ፣ ዝግባን፣ ግራርን፣ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤ በበረሓ፣ ጥድን፣ አስታንና ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ። ስለዚህ ሰዎች ያያሉ፤ ያውቃሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣ የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠረው፣ በአንድነት ይገነዘባሉ፤ ያስተውላሉም።
ኢሳይያስ 41:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፥ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዱማል፥ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፉማል። የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፦ አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና። አንተ ትል ያዕቆብ የእስራኤልም ሰዎች ሆይ፥ አትፍሩ፥ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፥ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፥ ንፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፥ አንተም በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ። ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፥ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፥ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። የእግዚዘብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራች፥ የእስራኤልም ቅዱስ እንደ ፈጠረው ያዩ ዘንድ ያውቁም ዘንድ ያስቡም ዘንድ በአንድነትም ያስተውሉ ዘንድ፥ በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፥ በበረሃውም ጥዱንና አስታውን ወይራውንም በአንድነት አኖራለሁ።
ኢሳይያስ 41:10-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ! እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ! እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ። በአንተ ላይ የተቈጡ ሁሉ ተሸንፈው ያፍራሉ፤ አንተንም ለመጒዳት የሚነሡ ጠፍተው እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ጠላቶችህን ትፈልጋቸዋለህ፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ በአንተ ላይ ጦርነት አስነሥተው የነበሩትም ፈጽሞ እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ‘አይዞህ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ቀኝ እጅህን ይዤ እረዳሃለሁ’ እያልኩ የማበረታታህ፥ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ ትል ደካማ የሆንክ እስራኤል ሆይ! እኔ ስለምረዳህ አትፍራ፤ የምታደግህ የእስራኤል ቅዱስ እኔ ነኝ። እነሆ፥ እኔ እንደ ስለታም፥ አዲስና፥ ጥርስ እንዳለው የመውቂያ መሣሪያ አደርግሃለሁ፤ ተራራዎችንም በማበራየት ታደቃቸዋለህ፤ ኰረብቶችንም ዳምጠህ እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ወደ ሰማይ ትበትናቸዋለህ፤ ነፋስም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእኔ በእስራኤል ቅዱስም ትመካለህ። “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ አያገኙም፤ ጒሮሮአቸው ከጥማት የተነሣ ሲደርቅ፥ እኔ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እሰማለሁ፤ እኔም የእስራኤል አምላክ ከቶ አልተዋቸውም። በደረቁ ኰረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ በሸለቆዎችም ውስጥ የውሃ ምንጮች ያልፋሉ፤ በረሓዎችንም የኲሬ ውሃ መከማቻ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ፤ ደረቁም ምድር የምንጭ ውሃ መፍሰሻ ይሆናል። የሊባኖስ ዛፎችን፥ የግራር እንጨቶችን፥ ባርሰነቱንና የወይራ ዛፎችን በበረሓ አበቅላለሁ፤ በምድረ በዳ ዝግባ፥ አስታና ጥድ፥ ወይራ የሞላበት ደን አበቅላለሁ። ይህን የማደርገው የእኔ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገና እኔም የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠርኩት ሁሉም አይተው ያውቁ ዘንድ፥ አስተውለውም ይረዱ ዘንድ ነው።”
ኢሳይያስ 41:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳሀለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዳሉም፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፋሉም። የሚጣሉህንም ትፈልጋቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ ጌታ ነኝ፦ “አትፍራ፥ እረዳሃለሁ” ብዬ ቀኝህን የያዝኩ። አንተ ትል ያዕቆብ፥ ታናሽ እስራኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ እረዳሃለሁ፥ ይላል ጌታ፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፥ ንፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በጌታ ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ። ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ ማከማቻ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ፤ ዝግባን፤ ግራርን፤ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤ በበረሃ፤ ጥድን፤ አስታንና ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ። ስለዚህ የጌታ እጅ ይህን እንዳደረገ፥ የእስራኤል ቅዱስ እንደፈጠረው፥ ሰዎች እንዲያዩና እንዲያውቁ፥ በአንድነት እንዲገነዘቡ፤ እንዲያስተውሉም።