ኢሳይያስ 35:5-10
ኢሳይያስ 35:5-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዐይኖቻቸው ይገለጣሉ፤ የደንቆሮዎችም ጆሮዎች ይሰማሉ። በዚያን ጊዜ አንካሳዎች እንደ ሚዳቋ ይዘልላሉ፤ የዲዳዎችም ምላስ ርቱዕ ይሆናል፤ በምድረ በዳ ውኃ፥ በተጠማ መሬትም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፥ የተጠማች ምድርም የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ የዎፎች መኖሪያም ሸንበቆና ደንገል ይሆንበታል። በዚያም ንጹሕ መንገድ ይሆናል፤ እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ በዚያም ንጹሓን ያልሆኑ አያልፉበትም፤ ርኩስ መንገድም በዚያ አይኖርም፤ የተበተኑትም በእርሱ ይሄዳሉ፤ አይሳሳቱምም። አንበሳ አይኖርበትም፤ ክፉ አውሬም አይወጣበትም፤ በዚያም አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ። በእግዚአብሔር የተሰበሰቡም ይመለሳሉ፤ በደስታም ተመልሰው ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘለዓለም ደስታም በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታንም ያገኛሉ፤ መከራ፥ ኀዘንና ትካዜም ይጠፋሉ።
ኢሳይያስ 35:5-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። ዐንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል፤ ውሃ ከበረሓ ይወጣል፤ ምንጮችም ከምድረ በዳ ይፈልቃሉ። ንዳዳማው ምድር ኵሬ ይሆናል፤ የተጠማው መሬት ውሃ ያመነጫል። ቀበሮዎች በተኙባቸው ጕድጓዶች፣ ሣር፣ ሸንበቆና ደንገል ይበቅልበታል። በዚያ አውራ ጐዳና ይሆናል፤ “የተቀደሰ መንገድ” ተብሎ ይጠራል። የረከሱ አይሄዱበትም፤ በመንገዱ ላይ ላሉት ብቻ ይሆናል፤ ገራገሮችም ከመንገዱ አይስቱም። አንበሳ አይኖርበትም፤ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፤ እነዚህማ በዚያ ስፍራ አይገኙም፤ የዳኑት ብቻ በዚያ ይሄዳሉ፤ እግዚአብሔር የዋጃቸው ይመለሳሉ። እየዘመሩ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን እንደ አክሊል ይቀዳጁታል፤ ፍሥሓና ሐሤት ያገኛሉ፤ ሐዘንና ትካዜ ከዚያ ይሸሻሉ።
ኢሳይያስ 35:5-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን የገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፥ የድዳም ምላስ ይዘምራል፥ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኵሬ፥ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፥ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆው ደንገልም ይሆንበታል። በዚያም ጎዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፥ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፥ ለንጹሐን ግን ይሆናል፥ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ ከዚያም አይገኙም፥ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፥ እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፥ የዘላላም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፥ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።
ኢሳይያስ 35:5-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ ዕውሮች ያያሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ አንካሶች እንደ ሚዳቋ ይዘላሉ፤ መናገር የማይችሉ ድዳዎች ይዘምራሉ፤ በበረሓ ውስጥ የጅረት ውሃ ይፈስሳል። የሚያቃጥለው አሸዋ ኩሬ ይሆናል፤ ደረቁም ምድር በምንጭ ውሃ ይረሰርሳል፤ የቀበሮዎች መፈንጫ የነበረው ስፍራ ለምለም ሣርና ቄጠማ የሚበቅልበት ይሆናል። በዚያ “ቅዱስ ጐዳና” የሚባል መንገድ ይኖራል፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ሰዎች ይሆናል፤ ንጹሕ ያልሆነ ሰው በዚያ መንገድ አይሄድም፤ ሞኞችም ሊሄዱበት አይችሉም። አንበሶችም ሆነ ነጣቂ አውሬዎች በዚያ አይገኙም፤ በዚያ መንገድ የሚመላለሱ እግዚአብሔር የታደጋቸው ወገኖች ብቻ ይሆናሉ። እግዚአብሔር የታደጋቸው ሰዎች ተመልሰው ይመጣሉ፤ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘወትር የደስታን ዘውድ ይቀዳጃሉ፤ ተድላና ደስታንም ያገኛሉ፤ ማዘንና መቃተት ከእነርሱ ይርቃል።
ኢሳይያስ 35:5-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዐይን ይበራል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ምንጭ ይፈልቃልና አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳም ምላስ ይዘምራል። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፥ የተጠማች መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ለምለም፥ ሸምበቆው ደንገል ይበቅልበታል። በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፥ እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐን ያልሆኑ አያልፉበትም፥ የእርሱ የሆኑ ሕዝቦች ግን ያልፉበታል፤ ተጓዦች ሆኑ፥ ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ እነዚህ ከዚያ አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤ ጌታም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፥ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላላም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።