ኢሳይያስ 30:15-22

ኢሳይያስ 30:15-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የእ​ስ​ራ​ኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላ​ልና፥ “ብት​ጸ​ጸ​ትና ብታ​ለ​ቅስ ትድ​ና​ለህ፤ የት እን​ዳ​ለ​ህም ታው​ቃ​ለህ፤ በከ​ንቱ ታም​ነ​ሃ​ልና፤ ኀይ​ላ​ች​ሁም ከንቱ ይሆ​ናል፤ እና​ንተ ግን መስ​ማ​ትን እንቢ አላ​ችሁ፤ ነገር ግን፥ በፈ​ረስ ላይ ተቀ​ም​ጠን እን​ሸ​ሻ​ለን እንጂ እን​ዲህ አይ​ሆ​ንም አላ​ችሁ፤ ስለ​ዚ​ህም ትሸ​ሻ​ላ​ችሁ፤ ደግ​ሞም በፈ​ጣን ፈረስ ላይ እን​ቀ​መ​ጣ​ለን አላ​ችሁ፤ ስለ​ዚ​ህም የሚ​ያ​ሳ​ድ​ዱ​አ​ችሁ ፈጣ​ኖች ይሆ​ናሉ። ከአ​ንድ ሰው ዛቻ የተ​ነሣ ሺህ ሰዎች ይሸ​ሻሉ፤ እና​ን​ተም በተ​ራራ ራስ ላይ እን​ዳለ ምሰሶ፥ በኮ​ረ​ብ​ታም ላይ እን​ዳለ ምል​ክት ሆና​ችሁ እስ​ክ​ት​ቀሩ ድረስ፥ ከአ​ም​ስት ሰዎች ዛቻ የተ​ነሣ ብዙ​ዎች ይሸ​ሻሉ።” አም​ላ​ካ​ችን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፈራጅ ነውና ስለ​ዚህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይራ​ራ​ላ​ችሁ ዘንድ ይታ​ገ​ሣል፤ ይም​ራ​ች​ሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፤ እር​ሱን በመ​ተ​ማ​መን የሚ​ጠ​ባ​በቁ ሁሉ ብፁ​ዓን ናቸው። ቅዱስ ሕዝብ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ውስጥ በጽ​ዮን ይኖ​ራል፤ ልቅ​ሶን አል​ቅሺ፤ ይቅር በለ​ኝም በዪ፤ ልቅ​ሶ​ሽን ባየ ጊዜ ይቅር ይል​ሻል፤ ሰም​ቶ​ሻ​ልና። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የጭ​ን​ቀ​ትን እን​ጀ​ራና የመ​ከ​ራን ውኃ ይሰ​ጥ​ሃል። የሚ​ያ​ሳ​ስ​ቱ​ህም እን​ግ​ዲህ ወደ አንተ አይ​ቀ​ር​ቡም፤ ዐይ​ኖ​ችህ ግን የሚ​ያ​ሳ​ስ​ቱ​ህን ያያሉ፤ ወደ ቀኝም ቢሆን ወደ ግራም ቢሆን በኋ​ላህ በዚህ መን​ገድ እን​ሂድ የሚ​ሉና የሚ​ሳ​ሳቱ ሰዎ​ችን ድምፅ ጆሮ​ዎ​ችህ ይሰ​ማሉ። በብ​ርም ወደ ተለ​በጡ፥ በወ​ር​ቅም ወደ አጌጡ ወደ ጣዖ​ታቱ እን​ሂድ የሚሉ ናቸው፤ ያን​ጊዜ እንደ ትቢያ የደ​ቀቁ ይሆ​ናሉ፤ እንደ ውኃም ይደ​ፈ​ር​ሳሉ፤ በእ​ነ​ር​ሱም ጥራ​ጊ​ዎ​ችን ይጥ​ሉ​ባ​ቸ​ዋል።

ኢሳይያስ 30:15-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤ እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤ ደግሞም ‘አይሆንም፣ በፈረስ እንሸሻለን’ አላችሁ፤ ስለዚህ ትሸሻላችሁ! ደግሞም፣ ‘በፈጣን ፈረስ እናመልጣለን’ አላችሁ፤ ስለዚህ አሳዳጆቻችሁም ፈጣን ይሆናሉ። በተራራ ዐናት ላይ እንደ ተተከለ ሰንደቅ ዐላማ፣ በኰረብታም ላይ እንደ ቆመ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ በአንድ ሰው ዛቻ፣ ሺሕ ሰው ይሸሻል፤ በዐምስት ሰው፣ ሁላችሁ ትሸሻላችሁ።” እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት ብፁዓን ናቸው! በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም። ለርዳታ ወደ እርሱ ስትጮኹ እንዴት ምሕረት አያደርግላችሁ! ጩኸትህን እንደ ሰማም ፈጥኖ ይመልስልሃል። ጌታ የጭንቀት እንጀራና የመከራ ውሃ ቢሰጥህም፣ አስተማሪህ ከእንግዲህ አይሰወርብህም፤ ዐይኖችህም አስተማሪህን ያያሉ። ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ “መንገዱ ይህ ነው፤ በርሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል። ከዚያም በብር የተለበጡትን ጣዖቶችህንና በወርቅ የተለበዱ ምስሎችህን ታዋርዳለህ፤ “ከዚህ ወግዱ!” ብለህም እንደ መርገም ጨርቅ ትጥላቸዋለህ።

ኢሳይያስ 30:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፥ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፥ እናንተም እምቢ አላችሁ፥ ነገር ግን፦ በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፥ ደግሞም፦ በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ። ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፥ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ። እግዚአብሔርም የፍርድ አምላክ ነውና ስለዚህ እግዚአብሔር ይራራላችሁ ዘንድ ይታገሣል፥ ይምራችሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፥ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅስም፥ በጩኸትም ድምፅ ይራራልሃል፥ በሰማህም ጊዜ ይመልስልሃል። ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፥ ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ። በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፥ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ፦ ወግዱ ትላቸውማለህ።

ኢሳይያስ 30:15-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በመመለስና በማረፍ ደኅንነትን ታገኛላችሁ፤ ጸጥ በማለትና በመታመን ኀይል ታገኛላችሁ፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ። በዚህ ፈንታ በፈጣን ፈረሶች ላይ ተቀምጣችሁ ከጠላቶቻችሁ እጅ ለማምለጥ ታቅዳላችሁ፤ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ‘ፈረሶቻችን እጅግ ፈጣኖች ናቸው’ ትሉ ይሆናል፤ ነገር ግን አሳዳጆቻችሁ ከእናንተ የፈጠኑ ይሆናሉ። ከጠላት ወታደር የአንድ ሰው ዛቻ ከእናንተ ሺህ ሰዎችን እንዲሸሹ ያደርጋል፤ እናንተን በሙሉ አምስት የጠላት ወታደሮች በተራራ ላይ እንዳለ የሰንደቅ ዓላማ ምሰሶና በኰረብታ ላይ ያለን ምልክት ጥቂቶቻችሁ ብቻ እስክትቀሩ ድረስ ያባርሩአችኋል። ይህም ሁሉ ሆኖ እግዚአብሔር ምሕረት ሊያደርግላችሁ ተዘጋጅቶአል፤ እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ስለ ሆነ ሊራራላችሁ ወዶአል፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር የሚታመኑ ሁሉ የተባረኩ ናቸው።” እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም፤ እግዚአብሔር ርኅሩኅ ስለ ሆነ የእርሱን ርዳታ በመፈለግ በምትጮኹበት ጊዜ ሰምቶ መልስ ይሰጣችኋል። በብዙ መከራ ውስጥ እንድታልፉ እግዚአብሔር ይፈቅድ ይሆናል፤ ነገር ግን እርሱ ራሱ ከእናንተ ጋር በመገኘት ያስተምራችኋል፤ ዳግመኛም እርሱን በመፈለግ አትደክሙም። ከመንገድ ወጥታችሁ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ብትባዝኑ ከበስተኋላችሁ “ትክክለኛው መንገድ ይህ ነው! በዚህ ሂድ” የሚለውን ድምፅ ትሰማላችሁ። በብርና በወርቅ የተለበጡትን ጣዖቶቻችሁንም “ከእኛ ወዲያ ራቁ!” ብላችሁ በመጮኽ እንደ ረከሰ ነገር አሽቀንጥራችሁ ትጥሉአቸዋላችሁ።

ኢሳይያስ 30:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ ኃይላችሁ በጸጥታና በመታመን ይሆናል፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ፥ ነገር ግን፦ “በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም” አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም፦ “በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን” አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዷችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ። ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፤ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ። ጌታም የፍርድ አምላክ ነው፤ ስለ ሆነም ጌታ ይራራላችኋልና ይታገሣል፤ ሊምራችሁም ከፍ ከፍ ይላል፤ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖር ሕዝብ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅስም፤ በጩኸትም ድምፅ ይራራልሃል፥ በሰማህም ጊዜ ይመልስልሃል። ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፤ ዐይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ “መንገዷ ይህች ናት በእርሷም ሂድ” የሚለውን ቃል ይሰማሉ። በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን፥ በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፤ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ፦ “ከእኔ ራቁ!” ትላቸዋለህ።