ኢሳይያስ 25:1-9
ኢሳይያስ 25:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር አምላኬ፥ ድንቅ ነገርን የዱሮ እውነተኛ ምክርን አድርገሃልና አከብርሃለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ። ከተሞችን ትቢያ አደረግህ፤ የተመሸጉ ከተሞችን፥ የኃጥኣንንም መሠረት አፈረስህ፤ ከተሞቻቸውም ለዘለዓለም አይሠሩም። ስለዚህ ድሆች ወገኖች ያከብሩሃል፤ የተገፉ ሰዎች ከተሞችም ያከብሩሃል። ለተዋረዱ ሰዎች ከተሞች ረዳት ሆነሃልና፥ በችግራቸው የተጨነቁትን በደስታ ጋረድሃቸው፤ ከክፉዎች ሰዎችም አዳንሃቸው፤ ለተጠሙት ጥላ ሆንሃቸው፤ ለተገፉትም ሕይወት ሆንሃቸው። ለእነርሱ አሳልፈህ ከሰጠኸን ከኃጥኣን ሰዎች የተነሣ በጽዮን እንደ ተጠሙ አእምሮአቸውን እንዳጡ ሰዎች ሆነናል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝቡ ሁሉ ግብዣን ያደርጋል፤ በዚህ ተራራ ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ፤ የወይን ጠጅንም ይጠጣሉ፤ ዘይትንም ይቀባሉ። በዚህም ተራራ ላይ ይህን ሁሉ ለአሕዛብ ሰጠ፤ ምክሩ ለአሕዛብ ሁሉ ናትና። ሞት ሰዎችን ዋጠ፤ በረታም፤ እንደ ገናም ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር በአፉ ተናግሮአልና። በዚያም ቀን፥ “እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፤ ያድናልም፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በመዳናችንም ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን” ይላሉ።
ኢሳይያስ 25:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ፤ አስቀድሞ የታሰበውን፣ ድንቅ ነገር፣ በፍጹም ታማኝነት አድርገሃልና። ከተማዪቱን የድንጋይ ክምር አድርገሃታል፤ የተመሸገችውንም ከተማ አፈራርሰሃታል፤ የተመሸገችው የባዕድ ከተማ ከእንግዲህ አትኖርም፤ ተመልሳም አትሠራም። ስለዚህ ብርቱ ሕዝቦች ያከብሩሃል፤ የጨካኝ አሕዛብ ከተሞችም ይፈሩሃል። ለድኻ መጠጊያ፣ በጭንቅ ጊዜ ለችግረኛ መጠለያ፣ ከማዕበል መሸሸጊያ፣ ከፀሓይ ትኵሳትም ጥላ ሆነሃል። የጨካኞች እስትንፋስ፣ ከግድግዳ ጋር እንደሚላጋ ማዕበል ነውና፤ እንደ ምድረ በዳም ትኵሳት ነው። የባዕድን ጩኸት እረጭ ታደርጋለህ፤ ትኵሳት በደመና ጥላ እንደሚበርድ፣ የጨካኞችም ዝማሬም እንዲሁ ጸጥ ይላል። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በዚህ ተራራ ላይ፣ ለሕዝብ ሁሉ ታላቅ የምግብ ግብዣ፣ የበሰለ የወይን ጠጅ ድግስ፣ ማለፊያ ጮማና ምርጥ የወይን ጠጅ ያዘጋጃል። በዚህም ተራራ ላይ፣ በሕዝብ ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፣ በመንግሥታት ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል፤ ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ውርደት ከምድር ሁሉ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሯልና። በዚያን ቀን እንዲህ ይባላል፤ “እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።”
ኢሳይያስ 25:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አቤቱ፥ አንተ አምላኬ ነህ፥ ድንቅን ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና በእውነት አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናሁ። ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፥ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፥ የኀጥኣንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፥ ከቶ አትሠራም። ስለዚህ ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፥ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች። የጨካኞችም ቍጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፥ ለድሀው መጠጊያ፥ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ፥ ከውሽንፍር መሸሸጊያ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል። እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥአንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፥ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአህዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፥ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፥ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፥ እግዚአብሔር ይህ ነው፥ ጠብቀነዋል፥ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል።
ኢሳይያስ 25:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ፤ አንተ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን አድርገሃል፤ ከጥንት ጀምሮ ያቀድከውን ሁሉ፥ ፍጹምነት ባለው አስተማማኝ ሁኔታ አከናውነሃል። ከተሞች ፈርሰው ባድማ እንዲሆኑ አድርገሃል፤ ምሽጎቻቸውንም አፈራርሰሃል፤ ጠላቶቻችን የሠሩአቸው ቤተ መንግሥቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል፤ እስከ ዘለዓለምም እንደገና አይሠሩም። የታላላቅ መንግሥታት ሕዝቦች ያከብሩሃል፤ በጨካኞች መንግሥታት ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ይፈሩሃል። ለድኾች፥ ለመጻተኞችና ለችግረኞች በችግራቸው ጊዜ መጠጊያ ሆነህላቸዋል፤ ከዐውሎ ነፋስ የሚድኑበት ተገንና ከፀሐይ ቃጠሎ የሚጠለሉበት ጥላ ሆነህላቸዋል፤ የጨካኞች ምት የክረምት ወጀብ ግድግዳን እንደሚገፋ ያለ ነው። እነርሱ በደረቅ ቦታ ላይ እንዳለ ሙቀት ሕዝብን ይጐዳሉ፤ አምላክ ሆይ! አንተ ግን የባዕዳንን ድንፋታ ዝም አሰኘህ፤ የደመና ጥላ ቃጠሎን እንደሚያበርድ የጋጠወጦችን ዘፈን ጸጥ አደረግህ። የሠራዊት አምላክ በዚህች በጽዮን ተራራ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ታላቅ ግብዣ ያዘጋጃል፤ በግብዣውም ላይ ምርጥ የወይን ጠጅና፥ የተሟላ ምግብ ይዘጋጃል። በዚህ ተራራ ላይ ሕዝቦችን ሁሉ ጋርዶ የነበረውን የሐዘን መጋረጃ ያስወግዳል። ልዑል እግዚአብሔር የሞትን ኀይል ለዘለዓለም ያጠፋል! ከሰዎችም ሁሉ ዐይን እንባን ያብሳል፤ ወገኖቹ በዓለም ሁሉ ላይ የተቀበሉትን ኀፍረት ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ራሱ ይህን ተናግሮአል። ይህም በሚፈጸምበት ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “እነሆ፥ እርሱ አምላካችን ነው፤ በእርሱ ስለ ታመንን አድኖናል፤ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ እኛም በእርሱ ታምነናል፤ እርሱ ስለ ታደገን በደስታ ተሞልተን ሐሴት እናደርጋለን!” ይላሉ።
ኢሳይያስ 25:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ ጌታ፥ አንተ አምላኬ ነህ፤ አስቀድሞ የታሰበውን፤ ድንቅ ነገር በታማኝነትና በእውነት አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናሁ። ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፥ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፥ የኀጥኣንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፤ ደግማም አትገነባም። ስለዚህ ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፥ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች። የጨካኞችም ቁጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፥ ለድሀው መጠጊያ፥ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መሸሸጊያ፥ ከውሽንፍር መጠለያ፥ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል። እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥአንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፤ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል። የሠራዊት ጌታም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ መልካምና የበሰለ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘለዓለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ ይህን ጌታ ተናግሮአል። በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ ጌታ ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን፥ ይባላል።