ኢሳይያስ 1:21-26
ኢሳይያስ 1:21-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፍርድ መልቶባት የነበረ የታመነችይቱ የጽዮን ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፤ አሁን ግን ወንበዴዎችና ነፍሰ ገዳዮች አሉባት። ወርቅሽና ብርሽ ዛገ፥ የወይን ጠጅ አሳላፊዎችሽም በወይን ጠጅሽ ላይ ውኃን ይደባልቃሉ። አለቆችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፤ ፍርድንም ሊያጣምሙ ይፈልጋሉ፤ ለሙት ልጅ አይፈርዱም፤ የመበለቲቱንም አቤቱታ አያዳምጡም። ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ለእስራኤል ኀያላን ወዮላቸው! በጠላቶች ላይ ቍጣዬ አይበርድም፤ ጠላቶችንም እበቀላለሁ። እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ አግልሻለሁ፤ ዝገትሽንም አነጻለሁ፤ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ፤ ዐመፀኞችን አጠፋለሁ፤ ሕገ ወጦችንም ከአንቺ አስወግዳለሁ፤ ትዕቢተኞችንም አዋርዳለሁ። ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ፥ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያ ጊዜ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ፥ የታመነችም ጽዮን ርእሰ ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።
ኢሳይያስ 1:21-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት አመንዝራ እንደ ሆነች ተመልከቱ፤ ቀድሞ ፍትሕ የሞላባት፣ ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤ አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ማደሪያ ሆነች፤ ብርሽ ዝጓል፣ ምርጥ የወይን ጠጅሽ ውሃ ገባው፤ ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጕቦን ይወድዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም። ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የእስራኤል ኀያል እንዲህ ይላል፤ “ወዮ! በባላንጣዎቼ ላይ ቍጣዬን እገልጣለሁ፤ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ። እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ ዝገትሽን ፈጽሜ አጠራለሁ፤ ጕድፍሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ። ፈራጆችሽን እንደ ጥንቱ፣ አማካሪዎችሽንም እንደ ቀድሞው እመልሳለሁ፤ ከዚያም የጽድቅ መዲና፣ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።”
ኢሳይያስ 1:21-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፍርድ ሞልቶባት የነበረው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፥ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት። ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፥ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ። አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፥ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፥ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፥ ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፥ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም። ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በጠላቶቼ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፥ የሚቋቋሙኝንም እበቀላለሁ። እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፥ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፥ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አወጣለሁ፥ ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያ ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፥ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።
ኢሳይያስ 1:21-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት እንደ አመንዝራ ሆነች! ቀድሞ ፍትሕ የሰፈነባትና የጻድቃን መኖሪያ ነበረች፤ አሁን ግን በነፍስ ገዳዮች የተሞላች ሆናለች። ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ። መሪዎችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ግብረ አበሮች ሆኑ፤ እያንዳንዱ ሁልጊዜ ገጸ በረከትና ጉቦ ይቀበላል፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት አይጠብቁም፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ አይሰሙም። ስለዚህ፥ የእስራኤል ኀይል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በጠላቶቼ ላይ ኀይለኛ ቊጣዬን አውርጄ ተቃዋሚዎቼን እበቀላለሁ። በከባድ ቊጣዬ እቀጣሻለሁ፤ ከዝገትሽ አጠራሻለሁ፤ ርኲሰትሽንም በማስወገድ አነጻሻለሁ። ቀድሞ የነበሩሽን ዐይነት ገዢዎችንና አማካሪዎችን አስነሣልሻለሁ፤ ከዚህ በኋላ ‘እውነት የሚገኝባት ታማኝ ከተማ’ ተብለሽ ትጠሪአለሽ።”
ኢሳይያስ 1:21-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት አመንዝራ እንደ ሆነች ተመልከቱ! ቀድሞ ፍትሕ የሞላባት፤ ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤ አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ማደሪያ ሆነች! ብርሽ ዝጎአል፤ ምርጥ የወይን ጠጅሽ ውሃ ገባው፤ ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጉቦን ይወዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም። ስለዚህ ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ኀያል እንዲህ ይላል፤ “በባላንጣዎቼ ላይ ቁጣዬን እገልጣለሁ፤ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ። እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ ዝገትሽን ፈጽሜ አጠራለሁ፤ ጉድፍሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ። ፈራጆችሽን እንደ ጥንቱ፤ አማካሪዎችሽንም እንደ ቀድሞው እመልሳለሁ፤ ከዚያም የጽድቅ መዲና፤ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።