ትንቢተ ኢሳይያስ 1
1
1በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ። 2እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፥ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ። 3በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፥ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም። 4ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል። 5ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል። 6ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፥ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፥ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም። 7ምድራችሁ ባድማ ናት፥ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፥ እርሻችሁንም በፊታችሁ ሌሎች ይበሉታል፥ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች። 8የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፥ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፥ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች። 9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር። 10እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። 11የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፥ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። 12በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? 13ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፥ እጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፥ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፥ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም። 14መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፥ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሳቸውም ደክሜያለሁ። 15እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፥ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል። 16ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፥ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፥ 17ክፉ ማድረግን ተዉ፥ መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። 18ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፥ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፥ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። 19እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፥ 20እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። 21ፍርድ ሞልቶባት የነበረው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፥ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት። 22ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፥ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ። 23አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፥ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፥ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፥ ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፥ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም። 24ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በጠላቶቼ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፥ የሚቋቋሙኝንም እበቀላለሁ። 25እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፥ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፥ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አወጣለሁ፥ 26ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያ ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፥ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ። 27ጽዮን በፍርድ ከእርሷም የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ። 28በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፥ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ። 29በወደዳችኋት የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁም፥ ስለ መረጣችኋትም አትክልት እፍረት ይይዛችኋልና፥ 30ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፥ ውሃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና። 31ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፥ ሥራውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፥ አብረውም ይቃጠላሉ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 1: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ