ኢሳይያስ 1:1-6
ኢሳይያስ 1:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም፥ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና፥ “ሰማይ ስማ፤ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ፤ አሳደግሁም፤ እነርሱም ዐመፁብኝ። በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጥ ዐወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቁኝም፤ ሕዝቤም አላስተዋሉኝም።” ኀጢአተኛ ወገንና ዐመፅ የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ በደለኞች ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ተዋችሁት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጣችሁት። እንግዲህ በበደል ላይ በደል እየጨመራችሁ ለምን ትቀሠፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕማም፥ ልብም ሁሉ ለኀዘን ሆኖአል። ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፤ አልተጠገነምም፤ በዘይትም አልለዘበም።
ኢሳይያስ 1:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፣ በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን፣ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ፤ ሰማያት ሆይ፤ ስሙ! ምድር ሆይ፤ አድምጪ! እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናግሯልና፤ “ልጆች ወለድሁ፣ አሳደግኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐመፁብኝ። በሬ ጌታውን፣ አህያ የባለቤቱን ጋጥ ያውቃል፤ እስራኤል ግን አላወቀም፤ ሕዝቤም አላስተዋለም።” እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፣ በደል የሞላበት ወገን፣ የክፉ አድራጊ ዘር፣ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃልለዋል፤ ጀርባቸውንም በእርሱ ላይ አዙረዋል። ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ? ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ? ራሳችሁ በሙሉ ታምሟል፤ ልባችሁ ሁሉ ታውኳል። ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጕራችሁ ጤና የላችሁም፤ ቍስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤ አልታጠበም፤ አልታሰረም፤ በዘይትም አልለዘበም።
ኢሳይያስ 1:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ። እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፥ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ። በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፥ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም። ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል። ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል። ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፥ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፥ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም።
ኢሳይያስ 1:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዖዝያን፥ ኢዮአታም፥ አካዝና ሕዝቅያስ የይሁዳ ነገሥታት ሆነው በነገሡባቸው ዘመናት የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰማያት ሆይ! ስሙ፤ ምድርም አድምጪ፤ ተንከባክቤ ያሳደግኋቸው ልጆች ዐመፀኞች ሆኑብኝ፤ በሬ ባለቤቱን ያውቃል፤ አህያም የጌታውን ጋጥ ያውቃል፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ምንም አያውቅም፤ ሕዝቤም አያስተውልም።” እናንተ ኃጢአተኞች በደልን የተሸከማችሁ ወገኖች! የክፉ አድራጊዎችም ትውልድ! ሕይወታችሁ የተበላሸ፥ እግዚአብሔርን የተዋችሁና የእስራኤልን ቅዱስ የናቃችሁ በእርሱም ላይ ጀርባችሁን ያዞራችሁ ናችሁ። በዐመፅ ላይ ዐመፅ ጨምራችሁ እንደገና መቀጣት የምትፈልጉት ለምንድን ነው? ራሳችሁ ለሕመም፥ ልባችሁም ሁሉ ለድካም የተጋለጠ ሆኖአል። ከዚህም የተነሣ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጠጒር ድረስ ጤናማ የሆነ የአካል ክፍል የላችሁም፤ ቊስልና እባጭ መግልም የሞላበት ሆኖአል፤ ይህም ቊስላችሁ አልፈረጠም፤ አልታሰረም፤ ወይም በዘይት አለሰለሰም።
ኢሳይያስ 1:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፤ በኢዮአታም፤ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን፤ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ። ሰማያት ሆይ፤ ስሙ! ምድር ሆይ፤ አድምጪ! ጌታ እንዲህ ተናግሮአልና፤ “ልጆች ወለድሁ፤ አሳደግኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐመጹብኝ። በሬ ጌታውን፤ አህያ የባለቤቱን ጋጥ ያውቃል፤ እስራኤል ግን አላወቀም፤ ሕዝቤም አላስተዋለም።” እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፤ በደል የሞላበት ወገን፤ የክፉ አድራጊ ዘር፤ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ! ጌታን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤ ጀርባቸውንም በእርሱ ላይ አዙረዋል። ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ? ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ? ራሳችሁ በሙሉ ታሞአል፤ ልባችሁ ሁሉ ታውኮአል። ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጉራችሁ ጤና የላችሁም፤ ቁስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤ አልታጠበም፤ አልታሰረም፤ በዘይትም አልለዘበም።