ሆሴዕ 2:9-15
ሆሴዕ 2:9-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ እህሌን በጊዜው፥ ወይኔንም በወራቱ እወስዳለሁ፤ ኀፍረቷንም እንዳትሸፍን ልብሴንና መጎናጸፊያዬን እገፍፋታለሁ። አሁንም በወዳጆችዋ ፊት ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ ሥርዐቶችዋንም ሁሉ አስቀራለሁ። እርስዋም፥ “ወዳጆች የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው” ያለችውን ሁሉ ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ምስክርም ይሆኑ ዘንድ አኖራቸዋለሁ፤ የምድረ በዳም አራዊትና የሰማይ ወፎች፥ የምድር ተንቀሳቃሾችም ይበሉታል። እኔን ረስታ ወዳጆችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም የሠዋችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እነሆ አቅበዘብዛታለሁ፤ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፤ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የተገኘውን ገንዘብዋን እሰጣታለሁ፤ ምክርዋንም በአኮር ሸለቆ እገልጣለሁ፤ እንደ ሕፃንነትዋ ወራት፥ ከግብፅም እንደ ወጣችበት ቀን ትዘምራለች።
ሆሴዕ 2:9-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ስለዚህ እህሌን በመከር ጊዜ፣ አዲሱም የወይን ጠጅ በደረሰ ጊዜ እወስዳለሁ፤ ዕርቃኗንም እንዳትሸፍንበት፣ ሱፍና የሐር ልብሴን መልሼ እወስድባታለሁ። አሁንም በውሽሞቿ ፊት፣ ነውሯን እገልጣለሁ፤ ከእጄም የሚያድናት የለም። የደስታ በዓሎቿን ሁሉ፣ የዓመት በዓሎቿንና፣ የወር መባቻዎቿን ሰንበቶቿንና የተመረጡ በዓሎቿን ሁሉ አስቀራለሁ። ከውሽሞቼ የተቀበልሁት ዋጋ ነው የምትለውን የወይን ተክሎቿንና የበለስ ዛፎቿን አጠፋለሁ፤ ጫካ አደርገዋለሁ፤ የዱር አራዊትም ይበሉታል። ለበኣል አማልክት ዕጣን ስላጠነችባቸው ቀናት እቀጣታለሁ፤ በጌጣጌጥና በቀለበቶች ራሷን አስጊጣለች፤ ውሽሞቿንም ተከትላ ሄዳለች፤ እኔን ግን ረስታለች” ይላል እግዚአብሔር። “ስለዚህ እነሆ፤ አባብላታለሁ፤ ወደ ምድረ በዳም እወስዳታለሁ፤ በፍቅር ቃል አነጋግራታለሁ። በዚያም የወይን ተክሏን እመልስላታለሁ፤ የአኮርንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ። በዚያም ከግብፅ እንደ ወጣችበት ቀን፣ እንደ ልጅነቷም ጊዜ ትዘምራለች።
ሆሴዕ 2:9-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፥ ትፈልጋቸውማለች፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፥ እርስዋም፦ ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ ትላለች። እርስዋም እህልንና ወይንን ጠጅ ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም የተሠራውን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። ስለዚህ እህሌን በጊዜዋ ወይን ጠጄንም በወረትዋ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም እንዳትሸፍን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። አሁንም ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፥ ከእጄም ማንም አያድናትም። ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችን ሁሉ አስቀራለሁ። እርስዋም፦ ውሽሞቼ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፥ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። እኔን ረስታ ውሽሞችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም ያጠነችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
ሆሴዕ 2:9-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እህሉን በመከር ጊዜ ወይኑንም በወቅቱ እወስድባታለሁ፤ ራቁትነትዋን የምትሸፍንባቸውን የሱፍና የተልባ እግር ልብሶቼንም እወስድባታለሁ። በፍቅረኞችዋም ፊት እርቃንዋን አስቀራታለሁ፤ ከእጄም የሚያድናት የለም። የምትደሰትባቸውን በዓላትዋን ሁሉ ሰንበትዋን፥ ዓመታዊና ወርኀዊ በዓላትዋን እሽራለሁ፤ የተለዩ በዓላትዋንም ሁሉ እንዳታከብር አደርጋታለሁ። ከፍቅረኛዎችዋም ያገኘቻቸውን የወይን ተክሎችና የበለስ ዛፎች እነቃቅላለሁ፤ የወይንና የፍራፍሬ እርሻዎችዋን ወደ ጫካነት እለውጣለሁ፤ የዱር አራዊትም ይበሉአቸዋል። “በዓል” ለሚባለው ጣዖት ለማጠንና ጌጣጌጥዋን አድርጋ ፍቅረኛዎችዋን በመከተል እኔን በመተዋ እቀጣታለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እንደገና ወደ በረሓ እወስዳታለሁ፤ እዚያም በፍቅር ቃል አባብዬ እማርካታለሁ። የቀድሞውን የወይን ተክል እመልስላታለሁ፤ የመከራንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ፤ እዚያም ከግብጽ ስትወጣ በወጣትነትዋ ወራት በነበራት ሁኔታ በደስታ ትዘምራለች።
ሆሴዕ 2:9-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለችም፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርሷም፦ ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና፥ ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ፥ ትላለች። እርሷም እህልንና ወይን ጠጅን ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም ያደረጉትን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደሆንኩ አላወቀችም። ስለዚህ እህሌን በጊዜው፥ ወይን ጠጄንም በወቅቱ ፈጽሞ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም መሸፈኛ የነበረውን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። እንዲሁም አሁን ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችዋን ሁሉ አስቀራለሁ። እርሷም፦ “ውሽሞቼ ለእኔ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው” ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። በበኣሊም የበዓል ቀኖች ዕጣን ለእነርሱ በማጠንዋና ራስዋን በጉትቾችዋና በጌጥዋ በማስጌጥ ውሽሞችዋን ተከትላ እኔን በመርሳትዋ እቀጣታለሁ፥ ይላል ጌታ።