ዕብራውያን 9:6-14
ዕብራውያን 9:6-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሥርዐቱ፥ ዝግጅቱም እንዲህ ነበር፤ በመጀመሪያዪቱም ድንኳን በየጊዜው አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ፥ ካህናት ዘወትር ይገቡ ነበር። ወደ ሁለተኛዪቱ ክፍል ግን ሊቀ ካህናቱ ኀጢአታቸውን ለማስተስረይ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ የሚያቀርበውን ደም ይዞ፥ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻውን ይገባ ነበር። ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ነገር ግን ለሚያቀርበው ሰው ግዳጅ መፈጸም የማይቻለውን መባና መሥዋዕት ያቀርቡበት የነበረው ለዚህ ዘመን ምሳሌ ሆነ። እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም፥ ስለ ልዩ ልዩ ጥምቀትም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዐቶች ብቻ ናቸው። ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደ አልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው፥ ከፊተኛዪቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን፥ የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም። የላምና የፍየል ደም፥ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ፥ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ ነውር የሌለው ሆኖ፥ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን?
ዕብራውያን 9:6-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሁሉም በዚህ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ፣ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ዘወትር ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ይገባሉ። ነገር ግን ወደ ውስጠኛው ክፍል የሚገባው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ስለ ራሱ ኀጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኀጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ ከቶ አይገባም ነበር። የመጀመሪያዪቱ ድንኳን ቆማ እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ ሲሆን፣ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም ሊያደርጉ አልቻሉም። እነዚህ ሁሉ አዲሱ ሥርዐት እስኪመጣ ድረስ የሚደረጉ የምግብና የመጠጥ እንዲሁም የተለያዩ የመንጻት ሥርዐቶች ብቻ ናቸው። ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ፣ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ። የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ። የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኰርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!
ዕብራውያን 9:6-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም። ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?
ዕብራውያን 9:6-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሁሉ ነገር በዚህ ሁኔታ ከተዘጋጀ በኋላ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ዘወትር ይገባሉ። ወደ ሁለተኛዋ ውስጠኛ ክፍል የሚገባው ግን የካህናቱ አለቃ ብቻ ነው፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ቀን ብቻ ነው፤ እርሱም ስለ ራሱ ኃጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም። የመጀመሪያይቱ ድንኳን እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና ያልተገለጠ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዐይነት ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፤ በዚህ ዐይነት የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የአቅራቢውን ሰው ኅሊና ፈጽመው ሊያነጹት አይችሉም፤ እነዚህ ነገሮች የመታደስ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ በሥራ ላይ የዋሉ አፍአዊ ሥርዓቶች ናቸው፤ እነርሱ ስለ መብልና ስለ መጠጥ፥ ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶችም ብቻ የተደረጉ ናቸው። ነገር ግን ክርስቶስ በመምጣት ላይ ላሉት መልካም ነገሮች የካህናት አለቃ ሆኖ ተገልጦአል፤ እርሱ የገባባት ድንኳን ትልቅና ፍጹም ናት፤ ይህች ድንኳን በሰው እጅ ያልተሠራችና ከዚህ ፍጥረት ያልሆነች ናት። እርሱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አንዴ በማያዳግም ሁኔታ የራሱን ደም ይዞ ገባ እንጂ የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አልገባም፤ በዚህም ዐይነት የዘለዓለም ቤዛን አስገኘልን። የፍየሎችና የወይፈኖች ደምና ለመሥዋዕት የተቃጠለች ጊደር ዐመድ በረከሱ ሰዎች ላይ ሲረጭ ከሥጋዊ ርኲሰት አንጽቶ የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ በዘለዓለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር የሌለበት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናገለግል ኅሊናችንን ከሞተ ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!
ዕብራውያን 9:6-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ እያለ ካህናት የአምልኮ አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ደጋግመው ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፤ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ በዚህ መንገድ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ እያለች ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ሲሆን፥ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም የማያደርጉ፥ ነገር ግን ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶች የሚውሉ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ስለ ሆኑ፥ እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ ናቸው። ነገር ግን ክርስቶስ እንደ ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ ስለሚሆነው መልካም ነገር፥ በምትበልጠውና በምትሻለው፥ በእጆችም ባልተሠራች፥ እርሷም ከፍጡራን ባልሆነች ድንኳን፥ የዘለዓምን ቤዛነት አግኝቶ፥ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ፥ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም፥ በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ፥ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም እንዴት ልቆ፥ ሕያው እግዚአብሔርን ለማምለክ፥ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን!