ዕብራውያን 9:16-28

ዕብራውያን 9:16-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኑዛዜ ያለ እን​ደ​ሆነ የተ​ና​ዛዡ ሰው ሞት ይመጣ ዘንድ ግድ ነው። የሙ​አች ሰው ኑዛዜ የጸ​ናች ናት፤ ተና​ዛዡ በሕ​ይ​ወት ባለ​በት ጊዜ አት​ጠ​ቅ​ም​ምና። ስለ​ዚ​ህም ፊተ​ኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አል​ከ​በ​ረም። ሙሴ የኦ​ሪ​ትን ትእ​ዛዝ ሁሉ ለመ​ላው ሕዝብ ከነ​ገረ በኋላ፥ የላ​ምና የፍ​የል ደም ከውኃ ጋር ቀላ​ቅሎ፥ ቀይ የበግ ጠጕ​ርና የስ​ሚዛ ቅጠል ነክሮ መጽ​ሐፈ ኦሪ​ቱ​ንና ሕዝ​ቡን ሁሉ ይረጭ ነበር። “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያዘ​ዛ​ችሁ የኪ​ዳኑ ደም ይህ ነው” ይላ​ቸው ነበር። ድን​ኳ​ኑ​ንና የመ​ገ​ል​ገ​ያ​ውን ዕቃ ሁሉ በደሙ ይረጭ ነበር። ደግ​ሞም በቀ​ረ​በው ሁሉ እን​ዲህ ያደ​ርግ ነበር፥ በኦ​ሪት ሕግ ሁሉ በደም ይነጻ ነበር፤ ደም ሳይ​ረጭ ግን አይ​ሰ​ረ​ይም ነበር። በሰ​ማይ ባለው አም​ሳል የተ​ሠ​ራው ይህ ሥራ፥ በዚህ ደም የሚ​ነጻ ከሆነ፥ ይህ ሰማ​ያዊ መሥ​ዋ​ዕ​ትስ ከዚህ ይበ​ል​ጣል። ክር​ስ​ቶስ በእጅ ወደ ተሠ​ራች የእ​ው​ነ​ተ​ኛ​ይቱ ምሳሌ ወደ​ም​ት​ሆን ቅድ​ስት አል​ገ​ባ​ምና፥ ነገር ግን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ፥ ወደ እር​ስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህ​ናቱ ያደ​ር​ገው እንደ ነበረ፥ በያ​መ​ቱም ደም ይዞ ወደ ቅድ​ስት ይገባ እንደ ነበረ ዘወ​ትር ራሱን የሚ​ሠዋ አይ​ደ​ለም። ይህስ ባይ​ሆን ዓለም ከተ​ፈ​ጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ በሞተ ነበር፤ አሁን ግን በዓ​ለም ፍጻሜ፥ ራሱን በመ​ሠ​ዋት ኀጢ​አ​ትን ይሽ​ራት ዘንድ አንድ ጊዜ ተገ​ለጠ። ለሰው አንድ ጊዜ ሞት፥ ከዚ​ያም በኋላ ፍርድ እን​ደ​ሚ​ጠ​ብ​ቀው፥ እን​ዲሁ ክር​ስ​ቶ​ስም የብ​ዙ​ዎ​ችን ኀጢ​አት ያስ​ተ​ሰ​ርይ ዘንድ ራሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፤ በኋላ ግን ያድ​ና​ቸው ዘንድ ተስፋ ለሚ​ያ​ደ​ር​ጉት ያለ ኀጢ​አት ይገ​ለ​ጥ​ላ​ቸ​ዋል።

ዕብራውያን 9:16-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኑዛዜ በሚኖርበት ጊዜ የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ግድ ነው፤ ምክንያቱም ኑዛዜው የሚጸናው ሰውየው ሲሞት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ተናዛዡ በሕይወት እስካለ ድረስ ኑዛዜው ዋጋ አይኖረውም። ስለዚህ የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አልነበረም። ሙሴ እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፣ ከቀይ የበግ ጠጕርና ከሂሶጵ ጋራ ወስዶ፣ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ እንዲህም አለ፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” እንዲሁም ድንኳኒቱንና ማገልገያ ዕቃውን ሁሉ በደም ረጨው። በርግጥ ከጥቂት ነገሮች በቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዝዛል፤ ደም ሳይፈስስ ስርየት የለምና። እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት በእነዚህ ነገሮች ሊነጹ ግድ ነበር፤ በሰማይ ያሉት ነገሮች ግን ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ። ክርስቶስ የእውነተኛዪቱ ድንኳን ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደ ተሠራችው መቅደስ አልገባም፤ ነገር ግን አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት ወደ እርሷ፣ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናት የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ፣ ክርስቶስ ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሰማይ አልገባም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጧል። ሰው አንድ ጊዜ ሊሞት ከዚያም በኋላ በፍርድ ፊት ሊቆም ተወስኖበታል። ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኗል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።

ዕብራውያን 9:16-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፤ ሰው ሲሞት ኑዛዜው ይጸናልና፥ ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን ከቶ አይጠቅምም። ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልተመረቀም። ሙሴም ትእዛዛትን ሁሉ እንደ ሕጉ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ፥ የጥጆችንና የፍየሎችን ደም ከውኃና ከቀይ የበግ ጠጕር ከሂሶጵም ጋር ይዞ፦ እግዚአብሔር ያዘዘላችሁ የኪዳን ደም ይህ ነው ብሎ በመጽሐፉና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ረጨው። እንዲሁም በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጨ። እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም። እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።

ዕብራውያን 9:16-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኑዛዜ ሲኖር የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ የኑዛዜ ቃል የሚጸናው ተናዛዡ ከሞተ በኋላ ነው፤ ተናዛዡ በሕይወት ካለ ግን የኑዛዜው ቃል ዋጋ አይኖረውም። በዚህ ምክንያት የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አይደለም። በመጀመሪያ ሙሴ የሕጉን ትእዛዞች ለሕዝቡ ሁሉ ነገረ፤ ከዚህ በኋላ የወይፈኖችንና የፍየሎችን ደም ከውሃ ጋር አድርጎ የሕጉን መጽሐፍና ሕዝቡን ሁሉ በሂሶጵና በቀይ የበግ ጠጒር ረጨ፤ የረጨውም “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የቃል ኪዳን ደም ይህ ነው” ብሎ ነው። እንዲሁም በድንኳኒቱና በመገልገያ ዕቃ ሁሉ ላይ ደምን ረጨ። በእርግጥም በሙሴ ሕግ መሠረት ከጥቂት ነገር በቀር ሁሉም ነገር በደም ይነጻል፤ ደም ካልፈሰሰም የኃጢአት ስርየት አይገኝም። እንግዲህ እነዚህ የሰማያዊ ነገሮች ምሳሌ የሆኑት ሁሉ በዚህ ዐይነት ሥርዓት መንጻት ያስፈልጋቸው ነበር፤ ከሰማይ የሆኑት ነገሮች ግን ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት መንጻት ያስፈልጋቸዋል። ክርስቶስ የእውነተኛይቱ “መቅደስ” ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደተሠራችው ቅድስተ ቅዱሳን አልገባም፤ እርሱ አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት ወደ ሰማይ ገባ። የአይሁድ የካህናት አለቃ የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር፤ ክርስቶስ ግን ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አልገባም። እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ኃጢአትን ለማስወገድ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ አንዴ በማያዳግም ሁኔታ ተገልጦአል። ለሰው አንድ ጊዜ መሞት ተመድቦለታል፤ ከሞት በኋላም ፍርድ አለበት። እንዲሁም ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ለማስወገድ አንድ ጊዜ ተሠውቶአል፤ ደግሞም ኃጢአትን ለመሸከም ሳይሆን እርሱን የሚጠባበቁትን ለማዳን ሁለተኛ ጊዜ ይገለጣል።

ዕብራውያን 9:16-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኑዛዜ ካለ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፥ ሰው ሲሞት ኑዛዜው ይጸናል። ተናዛዡ በሕይወት ካለ ግን ከቶ አይጠቅምም። ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳን ያለ ደም አልተመረቀም። እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ በሙሴ ለሕዝቡ ከተነገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፥ ከቀይ የበግ ጠጒርና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ፥ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” አላቸው። በተመሳሳይ በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጭቷል። እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፤ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም። እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት እነዚህ ነገሮች በዚህ ሥርዓት ሊነጹ ግድ ነበር፤ ነገር ግን ሰማያዊ ነገሮች ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ለመታየት ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት ደጋግሞ እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ ለመሞት ከዚያም ለፍርድ መቅረብ ተመድቦባቸዋል። እንዲሁም ክርስቶስ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ተሰውቷል። ለሁለተኛ ጊዜ ሲታይ ሊያድናቸው ለሚጠባበቁት ኃጢአትን ለመሸከም ሳይሆን መዳንን ለማምጣት ነው።