የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዕብራውያን 9:1-10

ዕብራውያን 9:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ፊተ​ኛ​ይ​ቱም ደግሞ የአ​ገ​ል​ግ​ሎት ሥር​ዐ​ትና የዚህ ዓለም የሆ​ነው መቅ​ደስ ነበ​ራት። የመ​ጀ​መ​ሪ​ያ​ዪ​ቱም ድን​ኳን ተዘ​ጋ​ጅታ ነበ​ርና፥ በእ​ር​ስ​ዋም ቅድ​ስት በም​ት​ባ​ለው ውስጥ መቅ​ረ​ዙና ጠረ​ጴ​ዛው፥ የመ​ሥ​ዋ​ዕ​ቱም ኅብ​ስት ነበ​ረ​ባት። ከሁ​ለ​ተ​ኛው መጋ​ረጃ በስ​ተ​ኋላ የነ​በ​ረ​ች​ውን የው​ስ​ጠ​ኛ​ዪ​ቱን ድን​ኳን ግን ቅድ​ስተ ቅዱ​ሳን ይሉ​አት ነበር። በው​ስ​ጥ​ዋም የወ​ርቅ ማዕ​ጠ​ን​ትና ሁለ​ን​ተ​ና​ዋን በወ​ርቅ የለ​በ​ጡ​አት፥ የኪ​ዳን ታቦት፥ መና ያለ​ባት የወ​ርቅ መሶ​ብና የለ​መ​ለ​መ​ችው የአ​ሮን በትር፥ የኪ​ዳ​ኑም ጽላት ነበ​ሩ​ባት። በላ​ይ​ዋም ማስ​ተ​ስ​ረ​ያ​ውን የሚ​ጋ​ርዱ የክ​ብር ኪሩ​ቤል ነበሩ፤ ነገር ግን በየ​መ​ልኩ እና​ገ​ረው ዘንድ ዛሬ ጊዜው አይ​ደ​ለም። ሥር​ዐቱ፥ ዝግ​ጅ​ቱም እን​ዲህ ነበር፤ በመ​ጀ​መ​ሪ​ያ​ዪ​ቱም ድን​ኳን በየ​ጊ​ዜው አገ​ል​ግ​ሎ​ታ​ቸ​ውን ይፈ​ጽሙ ዘንድ፥ ካህ​ናት ዘወ​ትር ይገቡ ነበር። ወደ ሁለ​ተ​ኛ​ዪቱ ክፍል ግን ሊቀ ካህ​ናቱ ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ውን ለማ​ስ​ተ​ስ​ረይ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ የሚ​ያ​ቀ​ር​በ​ውን ደም ይዞ፥ በየ​ዓ​መቱ አንድ ጊዜ ብቻ​ውን ይገባ ነበር። ፊተ​ኛ​ይ​ቱም ድን​ኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድ​ስት የሚ​ወ​ስ​ደው መን​ገድ ገና እን​ዳ​ል​ተ​ገ​ለጠ መን​ፈስ ቅዱስ ያሳ​ያል። ነገር ግን ለሚ​ያ​ቀ​ር​በው ሰው ግዳጅ መፈ​ጸም የማ​ይ​ቻ​ለ​ውን መባና መሥ​ዋ​ዕት ያቀ​ር​ቡ​በት የነ​በ​ረው ለዚህ ዘመን ምሳሌ ሆነ። እነ​ዚ​ህም እስከ መታ​ደስ ዘመን ድረስ የተ​ደ​ረጉ፥ ስለ ምግ​ብና ስለ መጠ​ጥም፥ ስለ ልዩ ልዩ ጥም​ቀ​ትም የሚ​ሆኑ የሥጋ ሥር​ዐ​ቶች ብቻ ናቸው።

ዕብራውያን 9:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የመጀመሪያው ኪዳን የአምልኮ ሥርዐትና ምድራዊ መቅደስ ነበረው። ድንኳን ተተክሎ ነበር፤ በመጀመሪያው ክፍል መቅረዙ፣ ጠረጴዛውና የመሥዋዕቱ ኅብስት ነበረበት፤ ይህም ስፍራ ቅድስት ይባላል። ከሁለተኛው መጋረጃ በስተ ኋላ ቅድስተ ቅዱሳን የተባለ ክፍል ነበር፤ በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንትና በወርቅ የተለበጠው የኪዳኑ ታቦት ነበሩ፤ ይህም ታቦት መና ያለበትን የወርቅ መሶብ፣ የለመለመችውን የአሮንን በትርና ኪዳኑ የተጻፈበትን ጽላት ይዟል። በታቦቱም ላይ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ አሁን ግን ስለ እነዚህ ነገሮች በዝርዝር መናገር አንችልም። ሁሉም በዚህ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ፣ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ዘወትር ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ይገባሉ። ነገር ግን ወደ ውስጠኛው ክፍል የሚገባው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ስለ ራሱ ኀጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኀጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ ከቶ አይገባም ነበር። የመጀመሪያዪቱ ድንኳን ቆማ እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ ሲሆን፣ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም ሊያደርጉ አልቻሉም። እነዚህ ሁሉ አዲሱ ሥርዐት እስኪመጣ ድረስ የሚደረጉ የምግብና የመጠጥ እንዲሁም የተለያዩ የመንጻት ሥርዐቶች ብቻ ናቸው።

ዕብራውያን 9:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ስርዓትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት። የመጀመሪያይቱ ድንኳን ተዘጋጅታ ነበርና፥ በእርስዋም ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙና ጠረጴዛው የመስዋዕቱም ኅብስት ነበረባት፤ ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፥ በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበረ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት፤ በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ፥ በላይዋም ማስተስሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ስለ እነዚህም ስለ እያንዳንዳቸው ልንናገር አሁን አንችልም። ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም።

ዕብራውያን 9:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የመጀመሪያው ኪዳን የአምልኮ አገልግሎት ሥርዓትና ምድራዊ መቅደስ ነበረው፤ ሁለት ክፍሎች ያሉአት ድንኳን ተዘጋጅታ ነበር። መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት የነበረባት መጀመሪያይቱ ክፍል “ቅድስት” ትባል ነበር። ከሁለተኛው መጋረጃ በስተኋላ የምትገኘው ውስጠኛዋ ክፍል “ቅድስተ ቅዱሳን” ትባል ነበር። በዚህችኛዋ ክፍል ውስጥ የወርቅ ማዕጠንትና በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት ነበሩባት፤ ከዚህችም የኪዳን ታቦት ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብ፥ ለምልማ የነበረችው የአሮን በትር፥ ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባት ጽላት ነበሩ። በታቦትዋም ላይ ያለውን የኃጢአት ማስተስረያ መክደኛ በክንፋቸው የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ነገር ግን ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሁን በዝርዝር መናገር አንችልም። ሁሉ ነገር በዚህ ሁኔታ ከተዘጋጀ በኋላ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ዘወትር ይገባሉ። ወደ ሁለተኛዋ ውስጠኛ ክፍል የሚገባው ግን የካህናቱ አለቃ ብቻ ነው፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ቀን ብቻ ነው፤ እርሱም ስለ ራሱ ኃጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም። የመጀመሪያይቱ ድንኳን እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና ያልተገለጠ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዐይነት ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፤ በዚህ ዐይነት የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የአቅራቢውን ሰው ኅሊና ፈጽመው ሊያነጹት አይችሉም፤ እነዚህ ነገሮች የመታደስ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ በሥራ ላይ የዋሉ አፍአዊ ሥርዓቶች ናቸው፤ እነርሱ ስለ መብልና ስለ መጠጥ፥ ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶችም ብቻ የተደረጉ ናቸው።

ዕብራውያን 9:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የመጀመሪያው ኪዳን የአገልግሎት ሥርዓትና ምድራዊ መቅደስ ነበራት። ድንኳን ተዘጋጅቶ ነበር፥ በእርስዋም ውስጥ ቅድስት በምትባለው መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበር። ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፤ በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበር፤ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት፥ በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ። በላይዋም ማስተስሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበር፤ ስለ እነዚህም በዝርዝር የመናገሪያው ሰዓት አሁን አይደለም። ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ እያለ ካህናት የአምልኮ አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ደጋግመው ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፤ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ በዚህ መንገድ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ እያለች ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ሲሆን፥ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም የማያደርጉ፥ ነገር ግን ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶች የሚውሉ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ስለ ሆኑ፥ እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ ናቸው።