ዕብራውያን 12:15-29
ዕብራውያን 12:15-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አስተውሉ፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ የሚያቃልል አይኑር፤ ሕማምን የምታመጣ፥ ብዙዎችንም የምታስታቸውና የምታረክሳቸው መራራ ሥር የምትገኝበትም አይኑር። ለጥቂት መብል ብኵርናውን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ሴሰኛና ርኩስ የሚሆን አይኑር። ከዚያ በኋላ እንኳ በረከትን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባም ተግቶ ምንም ቢፈልጋት ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና። ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም፥ ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም፥ ወደ መለከት ድምፅም፥ ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፥ ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ። የተነጋገራቸውን ሊሰሙት አልተቻላቸውም ነበርና፥ “እንስሳም ያን ተራራ ቢቀርበው በድንጋይ ይወግሩት” ነበር። የታያቸውም እንዲህ ግሩም ነበር፤ ሙሴም እንኳን፥ “እኔ ፈርቻለሁ፥ ደንግጫለሁም” አለ። እናንተ ግን፥ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ፥ በሰማያት ወደ አለችው ኢየሩሳሌም፥ ደስ ብሎአቸው ወደሚኖሩ አእላፍ መላእክትም ደርሳችኋል። ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈ ወደ ማኅበረ በኵርም፥ ሁሉን ወደሚገዛም ወደ እግዚአብሔር፥ ወደ ፍጹማን ጻድቃንም ነፍሳት፥ የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ ተረጨው ደሙ ደርሳችኋል። ለሚናገረው እንቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነርሱ በደብረ ሲና የተገለጠላቸውን እንቢ ስለ አሉት ካልዳኑ፥ ከሰማይ ከመጣው ፊታችንን ብንመልስ እኛማ እንዴታ? ያንጊዜ ቃል ምድርን አናወጣት፤ “አሁንም እኔ ምድርን እንደ ገና አንድ ጊዜ አናውጣታለሁ” ብሎ ተናገረ፤ ምድርን ብቻም አይደለም፤ ሰማይንም ጭምር እንጂ። አንድ ጊዜ ደግሞ ያለውም ፍጡራን ናቸውና፥ የማይናወጠው ይኖር ዘንድ፥ የሚናወጠውን እንደሚያሳልፈው ያሳያል። ስለዚህ የማይናወጥ መንግሥትን ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሀት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ። አምላካችን በእውነት የሚያቃጥል እሳት ነውና።
ዕብራውያን 12:15-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ። ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው፣ ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም መልሶ ሊያገኘው አልቻለም። ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፣ ወደ ጨለማው፣ ወደ ጭጋጉና ወደ ዐውሎ ነፋሱ አልደረሳችሁም፤ ወደ መለከት ድምፅ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምፅ አልመጣችሁም፤ የሰሙትም ሌላ ቃል ተጨምሮ እንዳይናገራቸው ለመኑ። ምክንያቱም “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ፣ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለውን ትእዛዝ መሸከም አልቻሉም። በዚያ ይታይ የነበረውም ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነበርና፣ ሙሴ “በፍርሀት ተንቀጠቀጥሁ” አለ። እናንተ ግን ወደ ጽዮን ተራራ፣ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ መጥታችኋል፤ በደስታ ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈው ወደ በኵራት ማኅበር ቀርባችኋል፤ የሁሉ ዳኛ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹምነትን ወዳገኙት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ፣ እንዲሁም ከአቤል ደም የተሻለ ቃል ወደሚናገረው ወደ ተረጨው ደም ደርሳችኋል። የሚናገረውን እርሱን እንቢ እንዳትሉት ተጠንቀቁ። እነዚያ ከምድር ሆኖ ሲያስጠነቅቃቸው የነበረውን እንቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፣ እኛ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅቀን ከእርሱ ብንርቅ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? በዚያን ጊዜ ድምፁ ያናወጠው ምድርን ነበር፤ አሁን ግን፣ “ምድርን ብቻ ሳይሆን፣ ሰማያትንም አንድ ጊዜ ደግሜ አናውጣለሁ” ብሎ ቃል ገብቷል። አንድ ጊዜ “ደግሜ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይናወጡት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ፣ የሚናወጡት ይኸውም፣ የተፈጠሩት የሚወገዱ መሆናቸውን ነው። ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሰኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤ አምላካችን የሚያጠፋ እሳት ነውና።
ዕብራውያን 12:15-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥ ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና። ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፤ ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ፤ እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት የምትለውን ትእዛዝ ሊታገሡ አልቻሉምና፤ ሙሴም፦ እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል። ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን? በዚያም ጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጠ፥ አሁን ግን፦ አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል። ዳሩ ግን፦ አንድ ጊዜ ደግሜ የሚል ቃል የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት የተፈጠሩ እንደሚሆኑ ይለወጡ ዘንድ ያሳያል። ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።
ዕብራውያን 12:15-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት ተጠንቀቁ፤ እንዲሁም ምንም መራራ ፍሬ የሚያፈራ ሥር በመካከላችሁ እንዳይበቅልና እንዳያስቸግራችሁ ብዙዎችንም እንዳያረክስ ተጠንቀቁ። ሴሰኛ የሆነ ወይም ለአንድ ጊዜ ምግብ ብሎ ብኲርናውን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ነውረኛ የሆነ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላም ዔሳው በረከትን እንደገና ለመቀበል በፈለገ ጊዜ ይህን በረከት እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ እያለቀሰ እንኳ ያንን በረከት ተግቶ ቢፈልግ ሊያገኘው አልቻለም። ለንስሓ ምንም ዕድል አላገኘም። እናንተ በእጅ ወደሚዳሰሰው ወይም ወደሚቃጠለው ወደ ሲና ተራራ አልደረሳችሁም፤ ወደ ጭጋጉ፥ ወደ ጨለማውም፥ ወደ ዐውሎ ነፋሱም፥ የእምቢልታ ድምፅ ወይም የሚነገረው ቃል ወደሚሰማበትም አልደረሳችሁም፤ ያንን ቃል የሰሙ ሰዎች “ከእንግዲህ ወዲህ ሌላ ቃል አይነገረን” በማለት እስከ መለመን ደርሰዋል። “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለው ትእዛዝ ስለ ከበደባቸው ሊሸከሙት አልቻሉም። የታየው ድርጊት እጅግ አስፈሪ ከመሆኑ የተነሣ ሙሴ እንኳ “እኔ ፈራሁ፤ ተንቀጠቀጥኩም” አለ። እናንተ ግን ወደ ጽዮን ተራራ ቀርባችኋል፤ እርስዋ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ የሆነችው ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ናት፤ በደስታ ወደተሰበሰቡት፥ በብዙ ሺህ ወደሚቈጠሩት መላእክት ቀርባችኋል። ስማቸው በሰማይ ወደተጻፈው፥ የቤተ ክርስቲያን የበኲር ልጆች ወደሆኑት ወደ አማኞች ጉባኤ፥ የሁሉ ፈራጅ ወደ ሆነው አምላክና ፍጹምነትን ወዳገኙት የጻድቃን ነፍሳት ቀርባችኋል። የአዲስ ኪዳን ማእከላዊ አስማሚ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገረውና ወደተረጨው ደሙም ቀርባችኋል። ያንን የሚናገረውን አንቀበልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ እግዚአብሔር በሰው አማካይነት ከምድር ሲናገራቸው አንሰማም ያሉት ካላመለጡ፥ ታዲያ እኛ ከሰማይ የሚናገረንን ባንቀበል እንዴት እናመልጣለን! በዚያን ጊዜ ቃሉ ምድርን አናውጦአል፤ አሁን ግን “ምድርን ብቻ ሳይሆን አንድ ጊዜ ደግሜ ሰማይን ጭምር አናውጣለሁ” በማለት ቃል ገብቶአል። ይህ “አንድ ጊዜ ደግሜ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይናወጡ ነገሮች ጸንተው እንዲኖሩ የሚናወጡ ወይም የተፈጠሩ ነገሮች መወገዳቸውን ነው። እንግዲህ እኛ የማትናወጠውን መንግሥት ስለምንወርስ እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታም በአክብሮትና በፍርሃት እናገልግለው። አምላካችን እንደሚያቃጥል እሳት ነው።
ዕብራውያን 12:15-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከመካከላችሁ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት መራራ ሥር በቅሎ እንዳያስጨንቃችሁ፥ ማንም ሴሰኛ እንዳይሆን ወይም ስለ አንድ መብል በኩርነቱን እንደ ሸጠው ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላ እንኳን በረከቱን ለመውረስ ቢፈልግም እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ እያለቀሰ ቢፈልግም እንኳን ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና። ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፥ ወደ ጭጋጉና ወደ ጨለማው፥ ወደ ዐውሎ ነፋሱ ገና አልደረሳችሁም፤ ወደ መለከት ድምፅ፥ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምጽ አልመጣችሁም። ያን ነገር የሰሙት ሁሉ ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው እስኪለምኑ አደረሳቸው፤ ምክንያቱም “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት፤” የምትለውን ትእዛዝ መሸከም አልቻሉም። ሙሴም “እጅግ እፈራለሁ፤ እንቀጠቀጥማለሁ፤” እስኪል ድረስ የሚታየው ነገር እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፤ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል። የሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላይ ሲያስረዳቸው እምቢ ያሉት ካላመለጡ፥ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅቀን ፈቀቅ የምንል እኛ እንዴት እናመልጣለን? ያንጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጧት ነበር፤ አሁን ግን “አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም፤” ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል። ዳሩ ግን “አንድ ጊዜ ደግሜ” የሚል ቃል የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት ፍጡራን ነገሮች እንደሆኑና እንደሚለወጡ ያሳያል። ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።