ዕብራውያን 12:1-17
ዕብራውያን 12:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ፥ የኀጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ። የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ፥ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኀጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን እስኪ ዐስቡት። ገና አልጸናችሁምና ደማችሁን ለማፍሰስ እስክትደርሱ ኀጢአትን ተጋደሉኣት፥ አሸንፉኣትም፤ ተስፋችሁን የምታገኙባትን ትምህርትም ውደዷት። እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፥ “ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም። እግዚአብሔር የሚወደውን ይገሥጻልና፥ የሚወደደውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል” ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል። ቅጣታችሁን ታገሡ፤ ልጆቹ እንደ መሆናችሁ ይወዳችኋልና፤ አባቱ የማይቈጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና፥ ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። በሥጋ የወለዱን አባቶቻችን የሚቀጡን፥ እኛም የምንፈራቸው ከሆነ፥ እንግዲያ ይልቁን ለመንፈስ አባታችን ልንታዘዝና ልንገዛ በሕይወትም ልንኖር እንዴት ይገባን ይሆን? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡናል፤ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ በጊዜው ያሳዝናል እንጂ ደስ አያሰኝም፤ በኋላ ግን ለተቀጡ ሰላምን ያፈራል፤ ጽድቅንም ያሰጣቸዋል። ስለዚህም የላሉትን እጆች፥ የሰለሉትንም ጕልበቶች አቅኑ። አንካሳነታችሁ እንዲድንና እንዳትሰነካከሉ ለእግሮቻችሁ የቀና መንገድን አድርጉ። ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም ሩጡ፤ ቅድስናችሁንም አትተዉ፤ ያለ እርሱ ግን እግዚአብሔርን የሚያየው የለም። አስተውሉ፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ የሚያቃልል አይኑር፤ ሕማምን የምታመጣ፥ ብዙዎችንም የምታስታቸውና የምታረክሳቸው መራራ ሥር የምትገኝበትም አይኑር። ለጥቂት መብል ብኵርናውን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ሴሰኛና ርኩስ የሚሆን አይኑር። ከዚያ በኋላ እንኳ በረከትን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባም ተግቶ ምንም ቢፈልጋት ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና።
ዕብራውያን 12:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል። እንግዲህ ዝላችሁ ተስፋ እንዳትቈርጡ፣ ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን እርሱን አስቡ። ከኀጢአት ጋር ስትታገሉ ገና ደማችሁን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም። ልጆች እንደ መሆናችሁ እንዲህ በማለት የተናገራችሁን ማበረታቻ ቃልም ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ፤ የጌታን ቅጣት አታቃልል፤ በሚገሥጽህም ጊዜ ተስፋ አትቍረጥ፤ ምክንያቱም ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።” እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይዟችኋልና የተግሣጽን ምክር ታገሡ፤ ለመሆኑ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ልጆች ሁሉ በሚቀጡበት ቅጣት ተካፋይ ካልሆናችሁ፣ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በላይ፣ እኛ ሁላችን የሚቀጡን ምድራዊ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር። ታዲያ ለመናፍስት አባት እንዴት አብልጠን በመገዛት በሕይወት አንኖርም? አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል። ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ። ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።” ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም። ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ። ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው፣ ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም መልሶ ሊያገኘው አልቻለም።
ዕብራውያን 12:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ። ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤ እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፦ ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል። ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል። ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ፤ ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ። ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና። የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥ ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና።
ዕብራውያን 12:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ስላሉን እኛ እንደ ሸክም የሆነብንን ነገር ሁሉ በእኛ ላይ የተጣበቀብንን ኃጢአት አስወግደን በፊታችንም ያለውን የሩጫ እሽቅድድም በትዕግሥት በመጽናት እንሩጥ። የምንሮጠውም የእምነታችን መሥራችና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን በመመልከት ነው፤ እርሱ በፊቱ በተደቀነው ደስታ ምክንያት በመስቀል ላይ የመሞትን ውርደት ከምንም ሳይቈጥር የመስቀልን መከራና ሞት ታገሠ፤ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝም ተቀመጠ። እንግዲህ ሳትሰለቹና ተስፋ ሳትቈርጡ ይህን ሁሉ የኃጢአተኞችን ተቃውሞ የታገሠውን ኢየሱስን ተመልከቱ። እናንተ ከኃጢአት ጋር በመታገል ገና ደም እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም። እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ አድርጎ እንዲህ ሲል የመከራችሁን ረስታችኋል፤ “ልጄ ሆይ! የጌታን ተግሣጽ አታቃል፤ በቀጣህም ጊዜ ተስፋ አትቊረጥ፤ ጌታ የሚወደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጁ አድርጎ የሚያየውንም ይቀጣል።” እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ስለሚቈጥራችሁ ቅጣትን ታገሡ፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ልጆች የሆኑ ሁሉ የሚቀበሉትን ቅጣት እናንተም ካልተቀበላችሁ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በቀር እኛ ሁላችን የሚቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ፥ በሕይወት ለመኖር ለመንፈሳዊ አባታችን በይበልጥ መታዘዝ እንዴት አይገባንም! እነርሱ መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ቀጥተውናል፤ እርሱ ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይመስልም፤ በኋላ ግን ለተለማመዱት ሰዎች ሰላም የሞላበትን የጽድቅ ፍሬ ያስገኝላቸዋል። ስለዚህ የዛሉትን እጆቻችሁንና የደከሙትን ጒልበቶቻችሁን አበርቱ። አንካሳ የሆነው እንዲፈወስ እንጂ ከቦታው ወጥቶ እንዳይናጋ ለእግራችሁ የቀና መንገድ አድርጉ። ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት ስለማይችል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ፤ በቅድስናም ለመኖር ትጉ፤ ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት ተጠንቀቁ፤ እንዲሁም ምንም መራራ ፍሬ የሚያፈራ ሥር በመካከላችሁ እንዳይበቅልና እንዳያስቸግራችሁ ብዙዎችንም እንዳያረክስ ተጠንቀቁ። ሴሰኛ የሆነ ወይም ለአንድ ጊዜ ምግብ ብሎ ብኲርናውን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ነውረኛ የሆነ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላም ዔሳው በረከትን እንደገና ለመቀበል በፈለገ ጊዜ ይህን በረከት እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ እያለቀሰ እንኳ ያንን በረከት ተግቶ ቢፈልግ ሊያገኘው አልቻለም። ለንስሓ ምንም ዕድል አላገኘም።
ዕብራውያን 12:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ እነደዚህ ዓይነት ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ማንኛውንም ሸክምና የተጣበቅንበትን ኅጢአት ሁሉ አራግፈን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። የእምነታችንንም ራስና ፍጽምና የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፥ ውርደቱንም ንቆ፥ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ እንዴት እንደተቋቋመ አስቡ። ከኃጢአት ጋር በምታደርጉት ተጋድሎ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤ እንደ ልጆችም እንዲህ በማለት የተነገራችሁን ምክር ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ! የጌታን ተግሣጽ አታቅልል፤ በሚገሥጽህም ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ፤ ጌታ የሚወደውን ይገሥጻልና፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ሁሉ ይቀጣል።” እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፥ የተግሣጽን ቅጣት ታገሡ፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ሁሉም ተካፋይ ከሆኑበት ቅጣት ውጭ ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በተጨማሪ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ እንዴት በላቀ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር አይገባንም? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበር፤ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ለጊዜው ቅጣት ሁሉ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰላማዊ የጽድቅን ፍሬ ያፈራላቸዋል። ስለዚህ የላሉትን እጆቻችሁን የሰለሉትንም ጉልበቶቻችሁን አቅኑ። አንካሳውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይሰበር፥ ለእግራችሁ ቀና መንገድ አበጁ። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጣሩ፤ ያለ ቅድስናም ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና ለመቀደስም ፈልጉ። ከመካከላችሁ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት መራራ ሥር በቅሎ እንዳያስጨንቃችሁ፥ ማንም ሴሰኛ እንዳይሆን ወይም ስለ አንድ መብል በኩርነቱን እንደ ሸጠው ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላ እንኳን በረከቱን ለመውረስ ቢፈልግም እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ እያለቀሰ ቢፈልግም እንኳን ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና።