ዕብራውያን 10:1-39
ዕብራውያን 10:1-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። ይህስ ባይሆን ከሚሠዉት መሥዋዕት ባረፉ ነበር፥ ለሚሠዉት ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸው ነበርና፥ ባአንድ ጊዜም ያነጻቸው ነበርና። ነገር ግን በዚያው መሥዋዕት በየዓመቱ የኀጢአት መታሰቢያ አድርገው የሚያቀርቡት ነበራቸው። የላምና የፍየል ደም ኀጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልምና። ስለዚህም ወደ ዓለም በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ አለ፥ “መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን አለበስኸኝ እንጂ። በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት በሚቀርበው መሥዋዕት ደስ አላለህም። ያንጊዜ እነሆ፥ በመጽሐፍ ራስ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን አደርግ ዘንድ መጥቻለሁ አልሁ።” በዚህ ላይ “መሥዋዕትንና መባን፥ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም፥ ስለ ኀጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፤ በእርሱም ደስ አላለህም” ብሎ ተናገረ፤ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡ ናቸው። ከዚህ በኋላ፥ “አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን አደርግ ዘንድ እነሆ፥ መጣሁ” አለ፤ ይህ ቃል የኋለኛውን ያቆም ዘንድ የፊተኛውን ያፈርሳል። በፈቃዱም አንድ ጊዜ በተደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋዉ ቍርባን ተቀደስን። ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዘወትር እያገለገለ ይቆም ነበር፤ ፈጽሞ ኀጢአት ማስተስረይ የማይቻላቸውን እነዚያን መሥዋዕቶች ብቻም ይሠዋ ነበር። እርሱ ግን ስለ ኀጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘለዓለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ። እንግዲህ ጠላቶቹ ከእግሩ በታች እስኪወድቁ ድረስ ይጠብቃል። ለሚቀደሱትም ለዘለዓለም የምትሆን አንዲት መሥዋዕትን ሠዋ። መንፈስ ቅዱስም ምስክራችን ነው። “ከእነዚያ ወራቶች በኋላ የምገባላቸው ኪዳን ይህቺ ናት ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልባቸው አኖረዋለሁ፤ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ካለ በኋላ። ከእንግዲህ ወዲህ ኀጢአታቸውንና በደላቸውን ደግሜ አላስብባቸውም” ብሏል። እንዲህም ኀጢአት የሚሰረይ ከሆነ፥ እንግዲህ ወዲህ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አያስፈልግም። እንግዲህ ወንድሞቻችን ሆይ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ወደ መቅደስ ለመግባት ባለሙአልነት አለን። በሥጋው መጋረጃ በኩል የሕይወትንና የጽድቅን መንገድ ፈጽሞ አድሶልናልና። በእግዚአብሔር ቤት ታላቅ ካህን አለን። እንግዲህ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፥ ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ። እንግዲህ የማይናወጠውን የተስፋችንን እምነት እናጽና፤ ተስፋ የሰጠ እርሱ የታመነ ነውና። በፍቅርና በበጎ ምግባርም ከባልንጀሮቻችን ጋር እንፎካከር። ሌሎች ልማድ አድርገው እንደ ያዙት ማኅበራችንን አንተው፤ እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። እውነትን ካወቅናት በኋላ፥ ተጋፍተን ብንበድል ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አይኖርም። ነገር ግን የሚያስፈራ ፍርድ ከሓዲዎችንም የሚበላቸው የቅናት እሳት ይጠብቃቸዋል። ከሙሴ ሕግ የተላለፈ ቢኖር ሁለት፥ ወይም ሦስት ምስክሮች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት ይሞታል። የእግዚአብሔርን ልጅ የከዳ፥ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቈጠረ፥ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? “እኔ እበቀላለሁ፤ እኔም ብድራትን እመልሳለሁ፥” ያለውን እናውቀዋለንና፤ ዳግመኛም “እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል።” በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው። እናንተ የተጠመቃችሁበትንና ብዙ መከራ የታገሣችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ፤ እናንተ ተሰድባችሁ ነበር፤ መከራም አጽንተውባችሁ ነበር፤ ተዘባብተውባችሁም ነበር፤ በዚህም መንገድ እንዲህ ከሆኑት ጋር ተባብራችሁ ነበር። በእስራቴም ጊዜ ከእኔ ጋር በመከራ ተባብራችኋል፤ የገንዘባችሁንም መዘረፍ በደስታ ተቀብላችኋል፤ በሰማያት ለዘለዓለም የሚኖር ከዚህ የሚበልጥና የተሻለ ገንዘብ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና። ትልቁን ዋጋችሁን የምታገኙባትን መታመናችሁን አትጣሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን ተስፋ ታገኙ ዘንድ መታገሥ ያስፈልጋችኋል። “ገና ጥቂት ቀን አለና፤ የሚመጣውም ፈጥኖ ይደርሳል፥ አይዘገይምም። ጻድቅ በእምነት ይድናል፤ ወደኋላ ቢመለስ ግን ልቡናዬ በእርሱ ደስ አይላትም።” እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት አይደለንም።
ዕብራውያን 10:1-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ እውነተኛው አካል አይደለም፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር ያለ ማቋረጥ የሚቀርበው ተደጋጋሚ መሥዋዕት፣ ለአምልኮ የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። ፍጹም ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ፣ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረምን? ደግሞም ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚነጹ፣ በኅሊናቸው ኀጢአተኝነት ባልተሰማቸውም ነበር። ነገር ግን እነዚህ መሥዋዕቶች በየዓመቱ ኀጢአትን የሚያስታውሱ ናቸው፤ ምክንያቱም የኰርማዎችና የፍየሎች ደም ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም። ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሏል፤ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ለኀጢአት በሚቀርብ መሥዋዕት ደስ አልተሰኘህም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አልሁ፤ ‘ስለ እኔ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣ አምላክ ሆይ፤ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ።’ ” ሕጉ ይህ እንዲደረግ ቢያዝም፣ እርሱ ግን በመጀመሪያ፣ “መሥዋዕትንና መባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ ደስም አልተሰኘህበትም” ይላል። ቀጥሎም፣ “እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ፤ ሁለተኛውን ለመመሥረት የመጀመሪያውን ሻረ። በዚህ ፈቃድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል። ካህን ሁሉ በየዕለቱ ቆሞ አገልግሎቱን ያከናውናል፤ ኀጢአትን ማስወገድ ከቶ የማይችሉትን እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር ያቀርባል። ይህኛው ካህን ግን አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል፤ ምክንያቱም በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጓቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል፤ “ከዚያም በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም እጽፈዋለሁ።” ደግሞም፣ “ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣ ከእንግዲህ አላስብም” ይላል። እነዚህ ይቅር ከተባሉ በኋላ ከእንግዲህ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አይኖርም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤ ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው። በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን፣ ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ። እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ። የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤ የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው። የሙሴን ሕግ የናቀ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት ይገደል ነበር። ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ተራ ነገር የቈጠረ፣ የጸጋንም መንፈስ ያክፋፋ እንደ ምን ያለ የባሰ ቅጣት ይገባው ይመስላችኋል? “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና፤ ደግሞም፣ “ጌታ በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል” ይላል። በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው። ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ፣ በመከራ ውስጥ በብርቱ ተጋድሎ ጸንታችሁ የቆማችሁበትን የቀድሞውን ዘመን አስቡ። አንዳንድ ጊዜ በአደባባይ ለስድብና ለስደት ተጋልጣችሁ ነበር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚህ ያለ መከራ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር አብራችሁ መከራን ተቀብላችኋል። እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ። ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ የተስፋ ቃሉን እንድትቀበሉ፣ ጸንታችሁ መቆም ያስፈልጋችኋል፤ ምክንያቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ “የሚመጣው እርሱ ይመጣል፤ አይዘገይም። ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አትሰኝም።” እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም።
ዕብራውያን 10:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን በተዉ አልነበረምን? ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ፦ መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ሰለ ኃጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም። በዚያን ጊዜ፦ እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ይላል። በዚህ ላይ፦ መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ፥ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፥ ቀጥሎ፦ እነሆ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ፥ ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል። የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም። እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ። የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። ነገር ግን ግማሽ በነቀፋና በጭንቅ እንደ መጫወቻ ስለ ሆናችሁ ግማሽም እንዲህ ካሉት ጋር ስለ ተካፈላችሁ፥ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ። የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።
ዕብራውያን 10:1-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕግ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር ምሳሌ (ጥላ) ነበር እንጂ እውነተኛ መልኩ አልነበረም፤ ስለዚህ በየዓመቱ ዘወትር የሚሠዉትን መሥዋዕቶች ይዘው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። ሕጉ ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች በማያዳግም ሁኔታ ከኃጢአት ስለ ነጹና ኃጢአት እንደሌለባቸውም በኅሊናቸው ስለሚታወቃቸው መሥዋዕትን ማቅረብ በተዉ ነበር። እነዚያ መሥዋዕቶች ግን በየዓመቱ ኃጢአትን የሚያስታውሱባቸው ናቸው። የወይፈኖችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም። ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ ሰውነትን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት ስርየት በሚሠዋ መሥዋዕት አልተደሰትክም፤ በዚያን ጊዜ እኔ፥ ‘አምላኬ ሆይ፥ በመጽሐፍ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ’ ” አልኩ። እሱም በመጀመሪያ እነዚያ በሕጉ መሠረት የታወጁ ቢሆኑ እንኳ “መሥዋዕትንና መባን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት ስርየት የሚሠዋውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ በእነርሱም አልተደሰትህም” አለ፤ ቀጥሎም “እነሆ፥ እኔ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ” አለ፤ በዚህ ሁኔታ ሁለተኛውን ዐይነት መሥዋዕት በቦታው ለመተካት የመጀመሪያውን ዐይነት መሥዋዕት ሽሮአል። በዚህም “ፈቃድ” በሚለው ቃል መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አንዴ በማያዳግም ሁኔታ መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ምክንያት ተቀድሰናል። እያንዳንዱ ካህን ኃጢአትን ማስወገድ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ዘወትር እያቀረበ በየቀኑ ቆሞ ያገለግላል። ክርስቶስ ግን ለሁልጊዜ የሚሆነውን አንዱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦአል። ከእንግዲህ ወዲህ ጠላቶቹ በሥልጣኑ ሥር እስኪሆኑ ድረስ ይጠባበቃል፤ ይህም የሆነው እነዚያን የተቀደሱትን በአንዱ መሥዋዕት አማካይነት ለዘለዓለም ፍጹሞች ስለ አደረጋቸው ነው። መንፈስ ቅዱስም በዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ፥ “ከእነዚያ ቀኖች በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሮአቸውም እጽፈዋለሁ።” ቀጥሎም “ኃጢአታቸውንና ክፉ ሥራቸውን ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም” ይላል። ስለዚህ ኃጢአት ሁሉ ከተደመሰሰ በኋላ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! በኢየሱስ ደም አማካይነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት የሚያስችለንን መተማመኛ አግኝተናል፤ የምንገባውም በመጋረጃው፥ ማለትም በሥጋው አማካይነት በከፈተልን በአዲሱና ሕያው በሆነው መንገድ ነው። በእግዚአብሔር ቤት ላይ ሥልጣን ያለው ትልቅ ካህን አለን። ስለዚህ ከክፉ ኅሊና እንድንነጻ ልባችንን ተረጭተን፥ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፥ ቅን ልብና እውነተኛ እምነት ይዘን ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። የተስፋውን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለ ሆነ አሁን አምነን የምንመሰክረውን ተስፋ ሳናወላውል አጥብቀን እንያዝ። በፍቅርና በመልካም ሥራ ነቅተን እንድንኖር አንዱ ሌላውን ያሳስበው፤ ዘወትር እየተገናኘን እርስ በርሳችን እንበረታታ እንጂ አንዳንዶች ማድረግ እንደ ለመዱት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም የጌታ መምጫ ቀን መቃረቡን እያስታወሳችሁ ይህን ነገር በይበልጥ አድርጉ። እውነትን ካወቅን በኋላ ሆን ብለን ኃጢአት ብንሠራ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት የሚቀርብ ምንም መሥዋዕት አይኖረንም። አሁን የሚቀረው ግን ወደ ፊት የሚሆነው አስፈሪ ፍርድና ተቃዋሚዎችን የሚያቃጥል አስፈሪ እሳት ነው። የሙሴን ሕግ የጣሰ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት በሞት ይቀጣል። ታዲያ፥ የእግዚአብሔርን ልጅ የናቀ፥ የተቀደሰበትን የቃል ኪዳን ደም ያረከሰ፥ የጸጋን መንፈስ የሰደበ፥ እንዴት ያለ የባሰ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል! “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ተገቢ ዋጋን እከፍላለሁ” ያለው ማን መሆኑን እናውቃለን፤ እንዲሁም “እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል” ይላል ጌታ። ስለዚህ በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው። ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ ብዙ መከራ ተቀብላችሁ የታገሣችሁባቸውን እነዚያን የቀድሞዎቹን ቀኖች አስታውሱ። አንዳንድ ጊዜ በሰው ፊት ተሰድባችኋል፤ ተንገላታችኋል፤ አንዳንድ ጊዜም ይህ ዐይነት ሥቃይ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር ጓደኞች በመሆናችሁ መከራ ተቀብላችኋል። እናንተ የተሻለና ነዋሪ ሀብት በሰማይ እንዳላችሁ በማወቃችሁ ለእስረኞች ራራችሁላቸው፤ ንብረታችሁም ሲወሰድባችሁ ታግሣችሁ ሁኔታውን በደስታ ተቀበላችሁ። እንግዲህ፥ ታላቅ ሽልማት የምታገኙበትን መተማመኛችሁን አትጣሉት። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ እግዚአብሔር ሊሰጣችሁ ቃል የገባላችሁን ነገር ለማግኘት በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋችኋል። ለዚህም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “ያ የሚመጣው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይመጣል፤ አይዘገይምም፤ የእኔ የሆነ ጻድቁ ሰው ግን በእምነት ሕይወትን ያገኛል፤ ወደ ኋላው ቢያፈገፍግ ግን እኔ በእርሱ አልደሰትም።” እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን ነን እንጂ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት ሰዎች ወገን አይደለንም።
ዕብራውያን 10:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን ጥላ በመሆኑ፥ እውነተኛ አካል አይደለም። በየዓመቱም ዘወትር በሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚቀርቡትን ለፍጽምና ሊያበቃ ከቶ አይችልም። እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን ባቆሙ አልነበረምን? ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት ዓመታዊ የኃጢአት መታሰቢያ ነው ያለው፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ለማስወገድ አይችልም። በዚህ ምክንያት፥ ወደ ዓለም ሲመጣ፥ “መሥዋዕትንና መባን አልወደድክም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠልና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት፥ አንተ ደስ አላለህም። በዚያን ጊዜ፥ ‘እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ! ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፥’ አልኩ፤” ይላል። በዚህ ላይ “መሥዋዕትንና መባን የሚቃጠል መሥዋዕትንም፥ ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፥ በእርሱም ደስ አላለህም፤” ይላል። እነዚህም እንደ ሕጉ የሚቀርቡት ናቸው። ከዚያም “እነሆ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፤” ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካህናትም ሁሉ በየዕለቱ እያገለገለ እነዚያን ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን መሥዋዕቶች ደጋግሞ ለማቅረብ ይቆማል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድ መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፤ አሁን ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ እንዲህ በማለት፦ “ከነዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ “በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ፥ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ፤” እንደዚሁም፥ “ኀጢአታቸውንና ዐመጻቸውንም ደግሜ አላስብም፤” ይላል። የእነዚህም ስርየት ባለበት፥ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የለም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ወደ ቅድስት ለመግባት በኢየሱስ ደም ድፍረት ስላለን፥ በአዲስና በሕያው መንገድ በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል ተከፍቶልን፥ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተንና ሰውነታችንን በንጹህ ውሃ ታጥበን፥ በቅን ልብ በፍጹም እምነት እንቅረብ፤ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና፥ ተስፋ የሚሰጠንን ምስክርነት ያለመናወጥ በጽናት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተሳሰብ፤ አንዳንዶችም ልምድ አድርገው እንደያዙት፥ መሰብሰባችንን አንተው፤ እርስ በርሳችን እንመካከር፤ ይልቁንም የቀኑን መቅረብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርብልንም፤ ነገር ግን የሚያስፈራ የፍርድና ተቃዋሚዎችንም ለመብላት የሚጠብቅ የእሳት ግለት አለ። የሙሴን ሕግ የተላለፈ ሰው “በሁለት እና በሦስት ምስክሮች ምስክርነት” ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፥ የተቀደሰበትን ያንን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ፥ የጸጋውንም መንፈስ ያስቆጣ፥ ቅጣቱ እጅግ የከፋ እንዴት የማይሆን ይመስላችኋል? “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤” ያለውን እናውቃለን፤ ደግሞም “ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል።” በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። ነገር ግን ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁባቸውን እነዚያን የመከራ ቀናት አስታውሱ፤ አንዳንድ ጊዜ በግላጭ ለነቀፋና ለስደት የተዳረጋችሁ ነበራችሁ፤ አንዳንዴም እንዲህ ካሉት ጋር በሚደርስባቸው ነገር ተካፋይ ሆናችሁ ነበር፤ በሰማይ የበለጠና ፍጻሜ የሌለው ሀብት እንዳላችሁ በማወቃችሁ፥ የንብረታችሁን መነጠቅ በደስታ ተቀበላችሁ፤ በእስራት ላይ የነበሩትን የስቃያቸው ተካፋይ ሆናችሁ። ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ ጽናት ያስፈልጋችኋል። ምክንያቱም ገና “በጣም ጥቂት ጊዜ፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል፥ አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ነፍሴ ወደ ኋላም በሚያፈገፍግ በእርሱ ደስ አትሰኝም።” እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ጋር ነን እንጂ፥ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ጋር አይደለንም።