ዕንባቆም 1:12-17
ዕንባቆም 1:12-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ የተቀደስህ አምላኬ ሆይ፥ አንተ ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፣ አቤቱ፥ ለፍርድ ሠርተኸዋል፥ ለተግሣጽም አድርገኸዋል። ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም፣ አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለምን ዝም ትላለህ? ሰዎችንም እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ አለቃም እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ? ሁሉን በመቃጥን ያወጣል፥ በመረቡም ይይዛቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፣ ስለዚህ ደስ እያለው እልል ይላል። እድል ፈንታው በእነርሱ ሰብታለችና፥ መብሉም በዝቶአልና ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል። ስለዚህ መረቡን ይጥላልን? አሕዛብንም ዘወትር ይገድል ዘንድ አይራራምን?
ዕንባቆም 1:12-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከዘላለም ጀምሮ ያለህ አይደለህምን? የእኔ አምላክ፣ የእኔ ቅዱስ እኛ አንሞትም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲፈርዱ ሾመሃቸዋል፤ ዐለት ሆይ፤ ይቀጡ ዘንድ ሥልጣን ሰጠሃቸው። ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤ አንተ በደልን መታገሥ አትችልም፤ ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትታገሣለህ? ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣ ለምን ዝም ትላለህ? አንተ ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣ ገዥ እንደሌላቸውም የባሕር ፍጥረታት አደረግህ። ክፉ ጠላት ሁሉንም በመንጠቆ ያወጣቸዋል፤ በመረቡ ይይዛቸዋል፤ በአሽክላው ውስጥ ይሰበስባቸዋል፤ በዚህም ይደሰታል፤ ሐሤትም ያደርጋል። በእነርሱ ተዝናንቶ ይኖራልና፤ ምግቡም ሠብቷል። ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፤ ለአሽክላውም ያጥናል። ታዲያ መረቡን ባለማቋረጥ መጣል፣ ሕዝቦችንስ ያለ ርኅራኄ መግደል አለበትን?
ዕንባቆም 1:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አቤቱ፥ የተቀደስህ አምላኬ ሆይ፥ አንተ ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፥ አቤቱ፥ ለፍርድ ሠርተኸዋል፥ ለተግሣጽም አድርገኸዋል። ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም፥ አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለምን ዝም ትላለህ? ሰዎችንም እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ አለቃም እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ? ሁሉን በመቃጥን ያወጣል፥ በመረቡም ይይዛቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፥ ስለዚህ ደስ እያለው እልል ይላል። እድል ፈንታው በእነርሱ ሰብታለችና፥ መብሉም በዝቶአልና ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል። ስለዚህ መረቡን ይጥላልን? አሕዛብንም ዘወትር ይገድል ዘንድ አይራራምን?
ዕንባቆም 1:12-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! አንተ ከጥንት ጀምሮ የነበርክ ቅዱስ ነህ፤ አንተ ስለምትጠብቀን አንሞትም፥ እነርሱ ፍርድህን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መድበሃቸዋል፤ አምባችን ሆይ! እኛን እንዲቀጡ ለእነርሱ ሥልጣን ሰጥተሃቸዋል። ዐይኖችህ እጅግ የጠሩ ስለ ሆኑ፥ ክፉ ነገርን መመልከት አይሆንላቸውም፤ አንተም ክፉ ነገር ሲሠራ ማየት አይስማማህም፤ ታዲያ እነዚህን ዐመፀኞችን እንዴት ዝም ብለህ ትመለከታቸዋለህ? ክፉዎችስ ከእነርሱ ይበልጥ ደጋግ የሆኑ ሰዎችን ሊያጠፉ ሲነሡ ስለምን ዝም ትላለህ? ሰዎችን እንደ ባሕር ዓሣዎችና መሪ እንደሌላቸው በደረታቸው እየተሳቡ እንደሚሄዱ ፍጥረቶች የምታደርጋቸው ለምንድን ነው? ዓሣ በመንጠቆ እንደሚያዝ ጠላት ሁሉንም ይይዛቸዋል፤ በመረብም እንደሚጐተት ይጐትታቸዋል፤ በማከማቻው ይሰበስባቸዋል፤ ይህን በማድረጉ በደስታ ይፈነጥዛል። በምግብ ስለሚያበለጽጉትና በቅንጦት እንዲኖር ስለሚያደርጉት ለመረቡ መሥዋዕት ያቀርባል፤ ለማከማቻውም ዕጣን ያጥናል። ታዲያ እርሱ መረቡን እያራገፈና ያለምሕረት ሕዝቦችን እየፈጀ መቀጠል አለበትን?
ዕንባቆም 1:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ አምላኬ፥ ቅዱሴ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፤ ጌታ ሆይ፥ ለፍርድ ወስነሃቸዋል፥ ዓለት ሆይ ለተግሣጽም መሠረትሃቸው። ዐይኖችህ ክፉ እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው፥ ክፉ ሥራም መመልከት አትችልም፤ አታላዮችን ለምን ትመለከታለህ? ክፉዎቹ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆኑትን ሲውጡ ለምን ዝም ትላለህ? ሰዎችን እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ ገዢ እንደሌላቸው የሚሳቡ ፍጥረቶች አደረግሃቸው። ሁሉን በመንጠቆ ያወጣል፥ በመረቡ ይጎትታቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፤ ስለዚህ ደስ ይለዋል፥ ሐሤትም ያደርጋል። ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል። በእነርሱ ድርሻው ሰብቷልና፥ መብሉም በዝቶአልና። ስለዚህ መረቡን ባዶ ከማድረግና አሕዛብን ዘወትር ከመግደል አይቆጠብምን?