የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዕንባቆም 1

1
1እግዚአብሔር ለነቢዩ ለዕንባቆም በራእይ የገለጠለት ቃል የሚከተለው ነው፦
ዕንባቆም ስለ ፍትሕ መጓደል የተሰማው ሐዘን
2እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን በመጠየቅና በእኛ ላይ የደረሰውን ዐመፅ በመግለጥ ወደ አንተ ስንጮህ የምታዳምጠንና የምታድነን መቼ ነው? 3ለምን ይህ ሁሉ ግፍ ሲደርስ እንዳይ አደረግኸኝ? አንተስ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም እንዴት ዝም ብለህ ትመለከታለህ? ጥፋትንና ዐመፅን አያለሁ፤ ጠብና ክርክርም ይነሣሉ። 4በዚህ መሠረት ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕም ተዛብቶአል፤ ክፉዎች በደጋግ ሰዎች ላይ ከበባ አድርገዋል፤ ስለዚህ ፍርድ ተጣሟል።
ከእግዚአብሔር የተሰጠ መልስ
5ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “በዙሪያችሁ ያሉትን ሕዝቦች እስቲ ተመልከቱ፤ በምታዩት ሁሉ እጅግ ተደነቁ፤ ማንም ሰው ቢነግራችሁ እንኳ ልታምኑ የማትችሉትን አስደናቂ ነገር በዘመናችሁ እሠራለሁ። #ሐ.ሥ. 13፥41። 6እነሆ እነዚያን ጨካኞችና ችኲሎች ባቢሎናውያንን አስነሣባችኋለሁ፤ እነርሱ የራሳቸው ያልሆነውን ምድር ሁሉ በጦር ኀይል ለመያዝ በየሀገሩ ይዞራሉ። 7እነርሱ አስፈሪና አስደንጋጭ ናቸው፥ የራሳቸውን ክብር ማስጠበቂያ ሕግ ያወጣሉ።
8“ፈረሶቻቸው ከነብር ይበልጥ ፈጣኖች፥ ከማታ ተኲላ ይልቅ አስፈሪዎች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም እየጋለቡ ከሩቅ ይመጣሉ፤ ነጥቀው ለመብላትም እንደ ንስር ይበራሉ።
9“ሠራዊታቸው ሁሉ የዐመፅ ሥራ ለመፈጸም ይገሠግሣሉ፤ ፊታቸው ከወደ ምሥራቅ እንደሚመጣ ነፋስ ያቃጥላል፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ። 10በነገሥታት ላይ ይሳለቃሉ፤ መሪዎቻቸውንም ይንቃሉ፤ በምሽጎቹ ሁሉ ላይ በመሳቅ ዐፈር ቈልለው ይይዙዋቸዋል። 11ከዚህ በኋላ እንደ ነፋስ ጠራርገው ይሄዳሉ፤ እነዚህ ጒልበታቸውን እንደ አምላካቸው የሚቈጥሩ ሰዎች በደለኞች ናቸው።”
ዕንባቆም ስለ ፍትሕ መጓደል ዳግመኛ የተሰማው ሐዘን
12እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! አንተ ከጥንት ጀምሮ የነበርክ ቅዱስ ነህ፤ አንተ ስለምትጠብቀን አንሞትም፥ እነርሱ ፍርድህን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መድበሃቸዋል፤ አምባችን ሆይ! እኛን እንዲቀጡ ለእነርሱ ሥልጣን ሰጥተሃቸዋል። 13ዐይኖችህ እጅግ የጠሩ ስለ ሆኑ፥ ክፉ ነገርን መመልከት አይሆንላቸውም፤ አንተም ክፉ ነገር ሲሠራ ማየት አይስማማህም፤ ታዲያ እነዚህን ዐመፀኞችን እንዴት ዝም ብለህ ትመለከታቸዋለህ? ክፉዎችስ ከእነርሱ ይበልጥ ደጋግ የሆኑ ሰዎችን ሊያጠፉ ሲነሡ ስለምን ዝም ትላለህ?
14ሰዎችን እንደ ባሕር ዓሣዎችና መሪ እንደሌላቸው በደረታቸው እየተሳቡ እንደሚሄዱ ፍጥረቶች የምታደርጋቸው ለምንድን ነው? 15ዓሣ በመንጠቆ እንደሚያዝ ጠላት ሁሉንም ይይዛቸዋል፤ በመረብም እንደሚጐተት ይጐትታቸዋል፤ በማከማቻው ይሰበስባቸዋል፤ ይህን በማድረጉ በደስታ ይፈነጥዛል። 16በምግብ ስለሚያበለጽጉትና በቅንጦት እንዲኖር ስለሚያደርጉት ለመረቡ መሥዋዕት ያቀርባል፤ ለማከማቻውም ዕጣን ያጥናል። #2ነገ. 24፥2።
17ታዲያ እርሱ መረቡን እያራገፈና ያለምሕረት ሕዝቦችን እየፈጀ መቀጠል አለበትን?

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ