ዘፍጥረት 8:1-12
ዘፍጥረት 8:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ፥ አዕዋፍንም ሁሉ፥ የሚንቀሳቀሰውንም ሁሉ ዐሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አመጣ፤ ውኃውም ጐደለ፤ የቀላዩም ምንጮች፥ የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፤ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤ ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እየቀለለ ይሄድ ጀመረ፤ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጐደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች። ውኃውም እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ ይጐድል ነበር፤ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ራሶች ተገለጡ። ከአርባ ቀን በኋላም ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፤ ከምድርም ላይ ውኃዉ ጐድሎ እንደሆነ ያይ ዘንድ ቁራውን ላከው፤ እርሱም ሄደ፤ ነገር ግን ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ አልተመለሰም። ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ጐድሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ በኋላ ላካት። ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም፤ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች፤ ውኃው በምድር ላይ ሁሉ ነበረና፤ እጁን ዘረጋና ተቀበላት፤ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት። ከዚያም በኋላ ደግሞ ሰባት ቀን ቆይቶ፥ ርግብን እንደገና ከመርከብ ላካት። ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ በአፍዋም እነሆ፥ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃው እንደ ጐደለ ዐወቀ። ደግሞ ሰባት ቀን ቆይቶ፥ ርግብን ላካት፤ ዳግመኛም ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
ዘፍጥረት 8:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከርሱ ጋራ የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ ዐሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ። የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ ውሃ መስኮቶች ተዘጉ፤ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ። ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ ዐምሳ ቀን በኋላም ጐደለ። በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች። ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየቀነሰ መጣ፤ በዐሥረኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ። ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣ ቍራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቍራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚያም በኋላ፣ ኖኅ ውሃው ከምድር ገጽ ጐድሎ እንደ ሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤ ነገር ግን ውሃው የምድርን ገጽ ገና እንደ ሸፈነ ስለ ነበር፣ ተመልሳ ኖኅ ወዳለበት መርከብ መጣች፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ተቀበላት፤ ወደ መርከቢቱም አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደ ገና ላካት። እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጕደሉን ዐወቀ። ሰባት ቀንም ቈይቶ ርግቧን እንደ ገና ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
ዘፍጥረት 8:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ኖኅን፤ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዋቱን ሁሉ፤ እንስሳውንም ሁሉ አሰበ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፉስን አሳለፈ፤ ውኂውም ጎደለ የቀላዪም ምንጮች የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፤ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ ውኂውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፤ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኂው ጎደለ። መርከቢቱም በስባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች፤ ላይ ተቀመጠች። ውኂውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበረ፤ በአሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበር በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮች ራሶች ተገለጡ። ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፤ ቁራንም ሰደደው እርሱም ወጣ፤ ውኂው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ቀልሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ ዘንድ ሰደዳት። ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አለገኘችም፤ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች ውኃ በምድር ላይ ሁሉ ስለ ነበረ እጁን ዘረጋና ተቀበላት ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት። ከዚያም በኋላ ደግሞ እስከ ስባት ቀን ቆየ ርግንም እንደ ገና ከመርከብ ሰደደ። ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ። ደግሞ እስከ ሰባት ቀም ቆየ ርግብንም ሰደዳት ዳግመኛም ወደ እርሱ አልስተመለሰችም።
ዘፍጥረት 8:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሶች ሁሉ አሰበ፤ ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም መጒደል ጀመረ። ከምድር በታች ያሉት ጥልቅ ምንጮች፥ በሰማይ ያሉት የውሃ መውረጃ በሮች ሁሉ ተዘጉ፤ ዝናቡም ከሰማይ መውረዱን አቆመ። ውሃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ መጒደል ጀመረ፤ ከመቶ ኀምሳ ቀኖችም በኋላ ውሃው ከምድር ላይ በጣም ጐደለ። በሰባተኛው ወር፥ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቡ “አራራት” ከተባሉት ተራራዎች በአንደኛው ጫፍ ላይ ዐረፈ። ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየጐደለ ሄደ፤ በዐሥረኛው ወር መጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ። ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቡን መስኮት ከፈተ፤ ቊራን ወደ ውጪ ላከው፤ ቊራውም ውሃው ከምድር እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚህ በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጒደሉን ለማወቅ አንዲት ርግብ ላከ። ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለ ነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ ውስጥ አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየም በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት። እርስዋም ወደ ማታ ጊዜ የለመለመ የወይራ ዘይት ዛፍ ቅጠል በአፍዋ ይዛ ወደ ኖኅ ተመለሰች፤ በዚህ ሁኔታ ኖኅ ውሃው ከምድር መጒደሉን ዐወቀ። ደግሞም ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ በዚህን ጊዜ ግን ርግቢቱ ሳትመለስለት ቀረች።
ዘፍጥረት 8:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሶች ሁሉ አሰበ። ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፥ ውኃውም ጎደለ፥ ከምድር በታች ያሉት ታላቅ የውሃ መፍለቂያዎች፥ በሰማይ ያሉት የውሃ መውረጃ በሮች ሁሉ ተዘጉ፤ ዝናቡም ከሰማይ መውረዱን አቆመ። ውሃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር፥ ከወሩም በዓሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች በአንደኛው ጫፍ ላይ ዐረፈች። ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበረ፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ተገለጡ። ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥ ቁራንም ወደ ውጪ ላከው፤ እርሱም ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚህ በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን ለማወቅ አንዲት ርግብ ላከ። ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለ ነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ ውስጥ አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየም በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት። ርግብም ወደ ማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እነሆም፥ በአፍዋ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃው መጉደሉን አወቀ። ደግሞም ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ ዳግመኛም ወደ እርሱ ሳትመለስለት ቀረች።