እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ፥ አዕዋፍንም ሁሉ፥ የሚንቀሳቀሰውንም ሁሉ ዐሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አመጣ፤ ውኃውም ጐደለ፤ የቀላዩም ምንጮች፥ የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፤ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤ ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እየቀለለ ይሄድ ጀመረ፤ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጐደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች። ውኃውም እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ ይጐድል ነበር፤ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ራሶች ተገለጡ። ከአርባ ቀን በኋላም ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፤ ከምድርም ላይ ውኃዉ ጐድሎ እንደሆነ ያይ ዘንድ ቁራውን ላከው፤ እርሱም ሄደ፤ ነገር ግን ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ አልተመለሰም። ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ጐድሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ በኋላ ላካት። ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም፤ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች፤ ውኃው በምድር ላይ ሁሉ ነበረና፤ እጁን ዘረጋና ተቀበላት፤ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት። ከዚያም በኋላ ደግሞ ሰባት ቀን ቆይቶ፥ ርግብን እንደገና ከመርከብ ላካት። ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ በአፍዋም እነሆ፥ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃው እንደ ጐደለ ዐወቀ። ደግሞ ሰባት ቀን ቆይቶ፥ ርግብን ላካት፤ ዳግመኛም ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
ኦሪት ዘፍጥረት 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 8:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች