ዘፍጥረት 49:22-26
ዘፍጥረት 49:22-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ዮሴፍ የሚያድግ ልጅ ነው፤ ለእኔ በጣም የተወደደ የሚቀናልኝና የሚያድግልኝ ልጅ ነው፤ ወደ እኔ የሚመለስም ጐልማሳ ነው። በምክራቸው የሰደቡት ጌቶች ሆኑበት፤ ቀስተኞችም ወጉት፤ ነገር ግን ቀስቶቻቸው በኀይል ተቀጠቀጡ፤ የእጆቻቸው ክንድ ሥርም በያዕቆብ ኀያል እጅ ዛለ፤ በዚያም በአባትህ አምላክ ዘንድ እስራኤልን አጸናው። “የእኔ አምላክ ረዳህ፤ ከላይ በሰማይ በረከት፥ ሁሉ በሚገኝባት፥ በምድር በረከት፥ በጡትና በማኅፀን በረከት ባረከህ፤ የአባትህና የእናትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ይበልጣሉ፤ ዘለዓለማውያን ከሆኑ ከኮረብቶችም በረከቶች ይልቅ ኀያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ራስ አናት ላይ ይሆናሉ።
ዘፍጥረት 49:22-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣ በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው። ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ። ቀስተኞች በጭካኔ አጠቁት፤ በጥላቻም ነደፉት። ነገር ግን በያዕቆብ ኀያል አምላክ ክንድ፣ እረኛው በሆነው በእስራኤል ዐለት፣ ቀስቱ ጸና፤ ጠንካራ ክንዱም ቀለጠፈ። አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣ በሚባርክህ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ፣ ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል። ከጥንት ተራሮች በረከት፣ ከዘላለም ኰረብቶች ምርቃት ይልቅ፣ የአባትህ በረከት ይበልጣል። ይህ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።
ዘፍጥረት 49:22-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ። ቀስተኞች አስቸገሩት ነደፋትም ተቃወሙትም ነገር ግም ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፤ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ በአባትህ በአምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ በጥልቅ በረከት ከታች በሚሠራጭ በጡትና በማኅፀን በረከት። የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኅያላን ናቸው፤ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮርፍቶች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ።
ዘፍጥረት 49:22-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ዮሴፍ፥ በውሃ ምንጭ አጠገብ ተተክሎ፥ ሐረጎቹ በግድግዳ ላይ እንደሚዘረጉ ፍሬያማ ዛፍ ነው። ቀስተኞቹ በብርቱ ያጠቁታል፤ በቀስታቸውም እየነደፉ ያሳድዱታል። ነገር ግን ብርቱ በሆነ በያዕቆብ አምላክ ኀይል፥ በእስራኤል እረኛና ጠባቂ ብርታት፥ የእርሱ ቀስት ጽኑ ይሆናል፤ ክንዱም ይበረታል። የአባትህ አምላክ ይረዳሃል፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ከላይ ከሰማይ ዝናብን፥ ከምድርም ጥልቀት ውሃን በመስጠት ይባርክሃል፤ ብዙ ከብትና ብዙ ልጆችም ይሰጥሃል። ከጥንት ጀምሮ ጸንተው ከሚኖሩት ተራራዎችና ዘለዓለማውያን ከሆኑት ኮረብታዎችም ከሚገኘው ደስ ከሚያሰኝ በረከት ሁሉ የአባትህ በረከት ይበልጣል። እንግዲህ ይህ ሁሉ በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ ይሁን፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም በዮሴፍ አናት ላይ ይውረድ።
ዘፍጥረት 49:22-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፥ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ። ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፥ ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፥ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥ በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት። የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፥ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረብቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፥ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ።