ኦሪት ዘፍጥረት 49
49
ያዕቆብ ልጆቹን እንደ መረቃቸው
1ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፥ “በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ። 2እናንት የያዕቆብ ልጆች ኑ፥ ተሰብሰቡ፤ ስሙም፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ።
3“ሮቤል እርሱ የበኵር ልጄና ኀይሌ፥ የልጆችም#ዕብ. “የጕብዝናዬ” ይላል። መጀመሪያ ነው፤ ክፉ ሆነ፤ አንገቱንም አደነደነ።#ዕብ. “የክብር አለቃና የኀይል አለቃ” ይላል። ጭንቅ ነገርንም አደረገ። 4እንደ ውኃ የሚዋልል ነው፤ ኀይል የለውም፤#ዕብ. “አለቅነት ለአንተ አይሁን” ይላል። ወደ አባቱ መኝታ ወጥቶአልና፤ ያን ጊዜ የወጣበትን አልጋ አርክሶአልና።
5“ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፤ በጭቅጭቃቸውና በጦራቸው ዐመፅን ፈጸሙአት። 6በምክራቸው ሰውነቴ አትገናኛቸው፤ ዐሳቤም በአመፃቸው አትተባበርም፤ በቍጣቸው ሰውን ገድለዋልና፤ በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቈርጠዋልና። 7ቍጣቸው ርጉም ይሁን፤ ጽኑ ነበርና፤ ኵርፍታቸውም ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፤ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ።
8“ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። 9ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከመሰማሪያህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ ተኛህ፤ አንቀላፋህም፤ እንደ አንበሳም ደቦል የሚቀሰቅስህ የለም። 10መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፤ ምስፍናም ከአብራኩ፥ ለእርሱ የሚጠብቀውን እስኪያገኝ ድረስ፤ የአሕዛብ ተስፋቸው እርሱ ነውና፤ 11አህያይቱን በወይን ግንድ ያስራል፤ የአህያይቱንም ግልገል በወይን ሐረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፤ መጐናጸፊያውንም በዘለላው ደም። 12ዐይኖቹ ከወይን ይልቅ ደስ ያሰኛሉ፤ ጥርሱም ከወተት ይልቅ ነጭ ነው።
13“ዛብሎን ጫማውን አዝቦ ይኖራል፤ እርሱም እንደ መርከቦች ወደብ ይሆናል፤ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ይሰፋል።
14“ይሳኮር መልካም ነገርን ወደደ፤ በተወራራሾቹም መካከል ያርፋል። 15ዕረፍትም መልካም መሆንዋን፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን በአየ ጊዜ ምድርን ያርሳት ዘንድ ትከሻውን ዝቅ አደረገ፤ በሥራም ገበሬ ሆነ።
16“ዳን ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ በወገኑ ይፈርዳል፤ 17ዳን በጎዳና ላይ እንደሚያደባ እባብ ይሆናል፤ በመንገዱም የፈረሱን ሰኰና እንደሚናደፍ እንደ ቀንዳም እባብ ነው፤ ፈረሰኛውም ወደኋላው ይወድቃል። 18እግዚአብሔርም ያድነው ዘንድ ይጠብቃል።#ዕብ. “እግዚአብሔር ሆይ መድኀኒትህን እጠብቃለሁ” ይላል።
19“ጋድን ሽፍቶች ቀሙት፤ እርሱም ፍለጋቸውን ተከታትሎ ቀማቸው።
20“የአሴር እንጀራ ወፍራም ነው፤ እርሱም ለአለቆች ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል።
21“ንፍታሌም በፍሬው ላይ ውበትን የሚሰጥ ሰፊ ዘንባባ ነው።#ዕብ. “የተፈታ ሚዳቋ ነው መልካም ቃልን ይሰጣል” ይላል።
22“ዮሴፍ የሚያድግ ልጅ ነው፤ ለእኔ በጣም የተወደደ የሚቀናልኝና የሚያድግልኝ ልጅ ነው፤ ወደ እኔ የሚመለስም ጐልማሳ ነው።#ዕብ. “ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው ፤ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ ነው ፤ ሐረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ” ይላል። 23በምክራቸው የሰደቡት ጌቶች ሆኑበት፤ ቀስተኞችም ወጉት፤ 24ነገር ግን ቀስቶቻቸው በኀይል ተቀጠቀጡ፤ የእጆቻቸው ክንድ ሥርም በያዕቆብ ኀያል እጅ ዛለ፤ በዚያም በአባትህ አምላክ ዘንድ እስራኤልን አጸናው።
25“የእኔ አምላክ ረዳህ፤ ከላይ በሰማይ በረከት፥ ሁሉ በሚገኝባት፥ በምድር በረከት፥ በጡትና በማኅፀን በረከት ባረከህ፤ 26የአባትህና የእናትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ይበልጣሉ፤ ዘለዓለማውያን ከሆኑ ከኮረብቶችም#ግእዝ “በረከተ መላእክቲሁ ለእግዚአብሔር” ይላል። በረከቶች ይልቅ ኀያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ራስ አናት ላይ ይሆናሉ።
27“ብንያም ነጣቂ ተኵላ ነው፤ በጥዋት ይበላል፤ የማረከውንም ምግቡን በማታ ለሕዝብ ይሰጣል።” 28እነዚህም ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ናቸው፤ አባታቸውም ይህን ነገር ነገራቸው፤ ባረካቸውም፤ እያንዳንዳቸውንም እንደ በረከታቸው ባረካቸው።
የያዕቆብ መሞትና መቀበር
29እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “እኔ ወደ ወገኖች እሰበሰባለሁ፤ በኬጢያዊው በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶች ጋር ቅበሩኝ፤ እርስዋም በከነዓን ምድር በመምሬ ፊት ያለች፥ 30አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት፥ ባለ ድርብ ክፍል ዋሻ ናት። 31አብርሃምንና ሚስቱ ሣራንም በዚያ ቀበሩአቸው፤ ይስሐቅንና ሚስቱ ርብቃንም በዚያ ቀበሩአቸው፤ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት 32እርሻውና በእርስዋ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው።” 33ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋው ላይ ዘርግቶ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተጨመረ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 49: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ