የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 37:5-36

ዘፍጥረት 37:5-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዮሴ​ፍም ሕል​ምን አለመ፤ ለወ​ን​ድ​ሞ​ቹም ነገ​ራ​ቸው። እር​ሱም አላ​ቸው፥ “እኔ ያለ​ም​ሁ​ትን ሕልም ስሙ፤ እነሆ፥ እኛ በእ​ርሻ መካ​ከል ነዶ ስና​ስር ነበ​ርና፥ እነሆ፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእ​ና​ን​ተም ነዶ​ዎች በዙ​ርያ ከብ​በው እነሆ፥ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወን​ድ​ሞ​ቹም፥ “በእኛ ላይ ልት​ነ​ግ​ሥ​ብን ይሆን? ወይስ ገዢ ትሆ​ነን ይሆን?” አሉት። እን​ደ​ገ​ናም ስለ ሕል​ሙና ስለ ነገሩ የበ​ለጠ ጠሉት። ደግ​ሞም ሌላ ሕል​ምን አየ፤ ለአ​ባ​ቱና ለወ​ን​ድ​ሞ​ቹም ነገ​ራ​ቸው፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “እነሆ፥ ደግሞ ሌላ ሕልም አለ​ምሁ፤ ሕል​ሙም እን​ዲህ ነው፦ ፀሐ​ይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋ​ክ​ብ​ትም ይሰ​ግ​ዱ​ልኝ ነበር።” አባ​ቱም ገሠ​ጸው፤ እን​ዲ​ህም አለው፥ “ይህ ያለ​ም​ኸው ሕልም ምን​ድን ነው? በውኑ እኔና እና​ትህ፥ ወን​ድ​ሞ​ች​ህም መጥ​ተን በም​ድር ላይ እን​ሰ​ግ​ድ​ልህ ይሆን?” ወን​ድ​ሞ​ቹም ቀኑ​በት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ ይጠ​ብ​ቀው ነበር። ወን​ድ​ሞ​ቹም በሴ​ኬም የአ​ባ​ታ​ቸ​ውን በጎች ይጠ​ብቁ ዘንድ ሄዱ። እስ​ራ​ኤ​ልም ዮሴ​ፍን፥ “ወን​ድ​ሞ​ችህ በሴ​ኬም በጎ​ችን የሚ​ጠ​ብቁ አይ​ደ​ሉ​ምን? ወደ እነ​ርሱ እል​ክህ ዘንድ ና” አለው። እር​ሱም፥ “እሺ” አለው። እር​ሱም፥ “ሄደህ ወን​ድ​ሞ​ች​ህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፤ ወሬ​አ​ቸ​ው​ንም አም​ጣ​ልኝ” አለው። ወደ ኬብ​ሮ​ንም ቆላ ላከው፤ ወደ ሴኬ​ምም መጣ። እነ​ሆም፥ በም​ድረ በዳ ሲቅ​በ​ዘ​በዝ ሳለ አንድ ሰው አገ​ኘው፤ ሰው​የ​ውም፥ “ምን ትፈ​ል​ጋ​ለህ?” ብሎ ጠየ​ቀው። እር​ሱም፥ “ወን​ድ​ሞ​ችን እፈ​ል​ጋ​ለሁ፤ በጎ​ቹን የሚ​ጠ​ብ​ቁ​በት ወዴት እንደ ሆነ እባ​ክህ ንገ​ረኝ?” አለ። ሰው​የ​ውም፥ “ከዚህ ተነ​ሥ​ተ​ዋል፤ ወደ ዶታ​ይን እን​ሂድ ሲሉም ሰም​ቼ​አ​ቸ​ዋ​ለሁ” አለው። ዮሴ​ፍም ወን​ድ​ሞ​ቹን ተከ​ታ​ትሎ ሄደ፤ በዶ​ታ​ይ​ንም አገ​ኛ​ቸው። እነ​ር​ሱም ወደ እነ​ርሱ ሳይ​ቀ​ርብ ከሩቅ አስ​ቀ​ድ​መው አዩት፥ ይገ​ድ​ሉ​ትም ዘንድ በእ​ርሱ ላይ ተማ​ከሩ። አን​ዱም ለአ​ንዱ እን​ዲህ አለው፥ “ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። ኑ፥ እን​ግ​ደ​ለ​ውና በአ​ንድ ጕድ​ጓድ ውስጥ እን​ጣ​ለው፤ ክፉ አው​ሬም በላው እን​ላ​ለን፤ ሕል​ሞ​ቹም ምን እን​ደ​ሚ​ሆኑ እና​ያ​ለን።” ሮቤ​ልም ይህን ሰማ፤ ከእ​ጃ​ቸ​ውም አዳ​ነው፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “ሕይ​ወ​ቱን አና​ጥፋ።” ሮቤ​ልም፥ “ደም አታ​ፍ​ስሱ፤ በዚች ምድረ በዳ ባለ​ችው ጕድ​ጓድ ጣሉት፤ ነገር ግን እጃ​ች​ሁን አት​ጣ​ሉ​በት” አላ​ቸው። ሮቤ​ልም እን​ዲህ ማለቱ ከእ​ጃ​ቸው ሊያ​ድ​ነ​ውና ወደ አባቱ ሊመ​ል​ሰው ነው። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ ዮሴፍ ወደ ወን​ድ​ሞቹ በቀ​ረበ ጊዜ የለ​በ​ሳ​ትን በብዙ ኅብር ያጌ​ጠ​ቺ​ውን ቀሚ​ሱን ገፈ​ፉት፤ ወስ​ደ​ውም ወደ ጕድ​ጓድ ጣሉት፤ ጕድ​ጓ​ዱም ውኃ የሌ​ለ​በት ባዶ ነበረ። እን​ጀ​ራም ሊበሉ ተቀ​መጡ፤ ዐይ​ኖ​ቻ​ቸ​ው​ንም በአ​ነሡ ጊዜ እነሆ፥ ይስ​ማ​ኤ​ላ​ው​ያን ነጋ​ድ​ያን ከገ​ለ​ዓድ ሲመጡ አዩ፤ ግመ​ሎ​ቻ​ቸ​ውም ሽቱና በለ​ሳን፥ ከር​ቤም ተጭ​ነው ነበር። ወደ ግብፅ ሀገ​ርም ሊያ​ራ​ግፉ ይሄዱ ነበር። ይሁ​ዳም ወን​ድ​ሞ​ቹን እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ወን​ድ​ማ​ች​ንን ገድ​ለን ደሙን ብን​ሸ​ሽግ ጥቅ​ማ​ችን ምን​ድን ነው? ኑ፥ ለእ​ነ​ዚህ ይስ​ማ​ኤ​ላ​ው​ያን እን​ሽ​ጠው፤ እጃ​ች​ንን ግን በእ​ርሱ ላይ አን​ጣል፤ ወን​ድ​ማ​ችን ሥጋ​ችን ነውና።” ወን​ድ​ሞ​ቹም የነ​ገ​ራ​ቸ​ውን ሰሙት። እነ​ዚያ ይስ​ማ​ኤ​ላ​ው​ያን ነጋ​ዴ​ዎ​ችም ሲያ​ልፉ ወን​ድ​ሞቹ ዮሴ​ፍን ከጕ​ድ​ጓድ ጐት​ተው አወ​ጡት፤ ለይ​ስ​ማ​ኤ​ላ​ው​ያ​ንም ዮሴ​ፍን በሃያ ብር ሸጡት፤ እነ​ር​ሱም ዮሴ​ፍን ወደ ግብፅ ወሰ​ዱት። ሮቤ​ልም ወደ ጕድ​ጓዱ ተመ​ለሰ፤ እነ​ሆም፥ ዮሴ​ፍን ከጕ​ድ​ጓድ በአ​ጣው ጊዜ ልብ​ሱን ቀደደ። ሮቤ​ልም ወደ ወን​ድ​ሞቹ ተመ​ልሶ፥ “ብላ​ቴ​ናው በጕ​ድ​ጓድ የለም፤ እን​ግ​ዲህ እኔ ወዴት እሄ​ዳ​ለሁ?” አለ። የዮ​ሴ​ፍ​ንም ቀሚስ ወሰዱ፤ የፍ​የ​ልም ጠቦት አር​ደው ቀሚ​ሱን በደም ነከ​ሩት። ብዙ ኅብር ያለ​በ​ትን ቀሚ​ሱ​ንም ላኩ፤ ወደ አባ​ታ​ቸ​ውም አገ​ቡት፤ እን​ዲ​ህም አሉት፥ “ይህን ልብስ አገ​ኘን፤ ይህ የል​ጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እን​ዳ​ል​ሆነ እስኪ እየው?” እር​ሱም ዐውቆ፥ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በል​ቶ​ታል፤ ዮሴ​ፍን ቦጫ​ጭ​ቆ​ታል” አለ። ያዕ​ቆ​ብም ልብ​ሱን ቀደደ፤ በወ​ገ​ቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለ​ቀሰ። ወን​ዶች ልጆ​ቹና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ተሰ​ብ​ስ​በው መጡ። ኀዘ​ኑ​ንም ያስ​ተ​ዉት ዘንድ አባ​ታ​ቸ​ውን ማለ​ዱት። ኀዘ​ኑ​ንም መተ​ውን እንቢ አለ፥ እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ወደ ልጄ ወደ መቃ​ብር እያ​ዘ​ንሁ እወ​ር​ዳ​ለሁ።” አባ​ቱም ስለ እርሱ አለ​ቀሰ። እነ​ዚያ ይስ​ማ​ኤ​ላ​ው​ያን ሰዎች ግን ዮሴ​ፍን በግ​ብፅ ለፈ​ር​ዖን ጃን​ደ​ረባ ለዘ​በ​ኞቹ አለቃ ለጲ​ጥ​ፋራ ሸጡት።

ዘፍጥረት 37:5-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዮሴፍም ሕልም ዐለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የባሰ ጠሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ አድምጡኝ እኛ ሁላችን በዕርሻ ውስጥ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ በድንገት ተነሥታ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች ዙሪያዋን ከብበው ለእኔ ነዶ ሰገዱላት።” ወንድሞቹም፣ “ለካስ በላያችን ለመንገሥ ታስባለህና! ለመሆኑ አንተ እኛን ልትገዛ!” አሉት፤ ስለ ሕልሙና ስለ ተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት። እንደ ገናም ሌላ ሕልም ዐለመ፤ ለወንድሞቹም፣ “እነሆ፤ ሌላ ሕልም ዐለምሁ፤ ፀሓይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ” ብሎ ነገራቸው። ሕልሙን ለአባቱና ለወንድሞቹ በነገራቸው ጊዜ፣ አባቱ “ይህ ያየኸው ሕልም ምንድን ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጐንብሰን በርግጥ ልንሰግድልህ ነው?” ሲል ገሠጸው። ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው። ከዚህም በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን በጎችና ፍየሎች ለማሰማራት ወደ ሴኬም አካባቢ ሄዱ፤ እስራኤልም ዮሴፍን “እንደምታውቀው ወንድሞችህ መንጎቹን በሴኬም አካባቢ አሰማርተዋል፤ በል ተነሥ፣ ወደ እነርሱ ልላክህ።” አለው። ዮሴፍም “ይሁን እሺ” አለው። ያዕቆብም፣ “ሄደህ ወንድሞችህም፣ መንጎቹም ደኅና መሆናቸውን አይተህ ወሬያቸውን አምጣልኝ” አለው፤ ከኬብሮንም ሸለቆ ወደ ሴኬም ላከው። ዮሴፍም ሴኬም በደረሰ ጊዜ፣ ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲባዝን አንድ ሰው አግኝቶት “ምን እየፈለግህ ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮሴፍም፣ “ወንድሞቼን እየፈለግኋቸው ነው፤ መንጎቻቸውን የት እንዳሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው። ሰውየውም፣ “ከዚህ ሄደዋል፤ ደግሞም፣ ‘ወደ ዶታይን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፣ ዶታይን አቅራቢያም አገኛቸው። ወንድሞቹም ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲመጣ በሩቅ አዩት፤ ወደ ነበሩበትም ስፍራ ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ። እነርሱም እንዲህ ተባባሉ፤ “ያ ሕልም ዐላሚ መጣ፤ ኑ እንግደለውና ከጕድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ ‘ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው’ እንላለን፤ እስቲ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን።” ሮቤል ግን ይህን ምክር ሲሰማ ከእጃቸው ሊያድነው ፈለገ፤ እንዲህም አለ፣ “ሕይወቱ በእጃችን አትለፍ፤ የሰው ደም አታፍስሱ፤ እዚህ ምድረ በዳ፣ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ እጃችሁን አታንሡበት።” ሮቤል ይህን ያለው ሕይወቱን ከእጃቸው አትርፎ ወደ አባቱ ሊመልሰው አስቦ ነበር። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደ ደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት ያጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤ ይዘውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር። ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች የግመል ጓዝ አዩ። ነጋዴዎቹ ሽቶ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብፅ የሚወርዱ ነበሩ። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል? ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አናንሣ። ምንም ቢሆንኮ ወንድማችን፣ ሥጋችን ነው” ወንድሞቹም በሐሳቡ ተስማሙ። የምድያም ነጋዴዎችም እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሱ፣ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጕድጓድ አውጥተው ለእስማኤላውያን በሃያ ጥሬ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። ሮቤል ወደ ጕድጓዱ ተመልሶ ሲያይ፣ ዮሴፍን በማጣቱ ልብሱን በሐዘን ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፣ “ብላቴናው ጕድጓድ ውስጥ የለም፤ የት አባቴ ልሂድ?” አለ። ከዚያም የዮሴፍን እጀ ጠባብ ወሰዱ፤ አንድ ፍየልም ዐርደው እጀ ጠባቡን በደሙ ነከሩት። በኅብረ ቀለማት ያጌጠችውን እጀ ጠባብ ወደ አባታቸው ወስደው፣ “ይህን ወድቆ አገኘነው፤ የልጅህ እጀ ጠባብ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው” አሉት። እርሱም ልብሱን ዐውቆት፣ “ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው! ክፉ አውሬ በልቶታል፤ በርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቋል” አለ። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና ባለመቻሉ “በሐዘን እንደ ተኰራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር እወርዳለሁ” አለ። ስለ ልጁም አለቀሰ። በዚህ ጊዜ፣ የምድያም ነጋዴዎች ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወስደው፣ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ ለነበረው ለዘበኞች አለቃ፣ ለጲጥፋራ ሸጡት።

ዘፍጥረት 37:5-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዮሴፍም ሕልምን አለመ ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ገና በብዙ ጠሉት እርሱ አላቸው፦ እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና እነሆም የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ። ወንድሞቹም፦ በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን? አሉት። እንደ ገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ ይልቁን ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ፦ እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ እነሆ ፀሐይን ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብርም ሲሰግዱልኝ አየሁ። ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው አባቱም ገሠጸው እንዲህም አለው፦ ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንስገድልህ ይሆን? ወንድሞቹም ቀኑበት አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቅው ነበር። ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። እስራኤልም ዮሴፍን፦ ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና አለው። እርሱም እነሆኝ አለው። እርሱም፦ ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅን እንደ ሆኑ እይ ወሬአቸውንም አምጣክኝ አለው። እንዲንም ከኬብሮን ቆላ ሰደደው ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም በምድረ በዳ ስቅበዘብዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው ሰውዮውም፦ ምን ትፈልጋለህ? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ወንድሞቼን እፈልጋለሁ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ አለ። ሰውዮውም፦ ከዚህ ተነሥተዋል ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ስምቼአቸዋለሁ አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ በዶታይንም አገኛቸው። እነርሱ በሩቅ ሳለ አዩት ወድ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ያባለ ሕልም ይኸው መጣ። አሁንም ኑ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፋ አውሬም በላው እንላለን ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን። ሮቤልም ይህን ሰማ ከእጃቸውም አዳነው እንዲህም አለ፦ ሕይወቱን አናጥፋ። ሮቤል፦ ደም አታፍስሱ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲንም ሆነ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱ ቀሚሱን ገፈፋት ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነውም? ኑ ለእስማኤላውያን እንሽጠው እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና የምድያም ነጋዶችም አለፈ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። ሮቤልም ወደ ጕድጓድ ተመለሰ፥ እነሆም ዮሴፍ በጕድጓድ የለም ልብሱንም ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ ብላቴናውም የለም እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ? አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበት ቀሚሱንም ላኩ፥ ወደ አባታቸውም አገቡት እንዲህም አሉት፦ ይህንን አገኘነ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው። እርሱም አውቆ፦ የልጄ ቀሚስ ነውም ክፋ አውሬ በልቶታል ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል አለ ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹም ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሠ መጽናናትን እንቢ አለ እንዲህም አለ፦ ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለዺጥፋራ ሸጡት።

ዘፍጥረት 37:5-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አንድ ሌሊት ዮሴፍ ሕልም አየ፤ ሕልሙን ለወንድሞቹ በነገራቸውም ጊዜ ከቀድሞው ይበልጥ ጠሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ፤ እኛ ሁላችን በእርሻ ውስጥ የስንዴ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ ተነሣና ቀጥ ብሎ ቆመ፤ የእናንተ ነዶዎች ዙሪያውን ተሰብስበው ለእኔ ነዶ ሰገዱለት።” ወንድሞቹም “ታዲያ በእኛ ላይ ንጉሥ ሆነህ ልትገዛን ታስባለህን?” ብለው ጠየቁት። ስላየው ሕልምና ስለ ተናገረው ቃል ከበፊቱ ይበልጥ ጠሉት። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ሌላ ሕልም አይቶ ወንድሞቹን “እነሆ፥ ሌላ ሕልም አየሁ፤ በሕልሜም ፀሐይ፥ ጨረቃና ዐሥራ አንድ ከዋክብት ሰገዱልኝ” አላቸው። ይህንኑ ለወንድሞቹ የነገራቸውን ሕልም ለአባቱም በነገረው ጊዜ፥ አባቱ “ይህ ምን ዐይነት ሕልም ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም የምንሰግድልህ ይመስልሃልን?” በማለት ገሠጸው። የዮሴፍ ወንድሞች እጅግ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ እያሰላሰለ ይጠብቀው ነበር። አንድ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን መንጋዎች ይዘው ወደ ሴኬም ተሰማሩ፤ እስራኤልም ዮሴፍን “እነሆ፥ ወንድሞችህ መንጋውን ይዘው ወደ ሴኬም መሰማራታቸውን ታውቃለህ፤ ስለዚህ ወደ እነርሱ ልልክህ እፈልጋለሁ” አለው። ዮሴፍም “እሺ እሄዳለሁ” አለ። አባቱም “በል እንግዲህ ሂድና የወንድሞችህንና የመንጋዎቹን ደኅንነት አይተህ ንገረኝ” አለው። በዚህ ዐይነት እስራኤል ዮሴፍን ከኬብሮን ሸለቆ ላከው። ዮሴፍም ሴኬም ደረሰ። እዚያም በየሜዳው ሲባዝን ሳለ አንድ ሰው አገኘውና “ምን እየፈለግህ ነው?” ብሎ ጠየቀው። ዮሴፍም “ወንድሞቼን እየፈለግሁ ነው፤ መንጋዎቻቸውን ይዘው ወዴት እንደ ተሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው። ሰውየውም “እነርሱ ከዚህ ሄደዋል፤ ‘ወደ ዶታን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቼአቼዋለሁ” አለው። ስለዚህ የወንድሞቹን ዱካ ተከትሎ ሄደና በዶታን አገኛቸው። እነርሱም በሩቅ አዩት፤ ወደ እነርሱም ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ። እርስ በርሳቸውም “እነሆ፥ ያ ሕልም አላሚ መጣ፤ ኑ እንግደለውና ከእነዚህ ጒድጓዶች በአንደኛው ውስጥ እንጣለው፤ ከዚህ በኋላ ‘ክፉ አውሬ በላው’ ብለን ማመኻኘት እንችላለን፤ በዚህ ዐይነት የሕልሙን መጨረሻ እናያለን” አሉ። ሮቤል ይህንን በሰማ ጊዜ ከእጃቸው ለማዳን በመፈለግ “ተዉ፤ አይሆንም፤ ባንገድለው ይሻላል፤ ከምትገድሉት ይልቅ በዚህ በበረሓ ባለው ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት” አላቸው። ሮቤል ይህን ያለው ከእጃቸው አድኖ ወደ አባቱ ሊመልሰው ፈልጎ ነው። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በደረሰ ጊዜ ጌጠኛ የሆነውን እጀ ጠባቡን አወለቁበት፤ ዮሴፍንም ወስደው ውሃ በሌለው ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት። ከዚህ በኋላ ምሳ ለመብላት ተቀመጡ፤ በሚመገቡበትም ጊዜ እስማኤላውያን ነጋዴዎችን በሩቅ አዩ፤ እነርሱም በግመሎቻቸው ቅመማ ቅመም፥ በለሳን፥ ከርቤም ጭነው ከገለዓድ ወደ ግብጽ የሚጓዙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን ገድለን የአሟሟቱን ሁኔታ ብንደብቅ ምን ይጠቅመናል? እርሱ የሥጋ ወንድማችን ስለ ሆነ” በእርሱ ላይ ጒዳት ከምናደርስበት ይልቅ ለእነዚህ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ብንሸጠው ይሻላል፤ ወንድሞቹም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ። የምድያም ነጋዴዎች የሆኑ እስማኤላውያን በዚያ በኩል ያልፉ ነበር፤ ስለዚህ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጒድጓድ ጐትተው በማውጣት ለእነዚህ እስማኤላውያን በሃያ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይዘውት ሄዱ። ሮቤል ወደ ጒድጓድ መጥቶ ዮሴፍ በዚያ አለመኖሩን ባወቀ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ወደ ወንድሞቹም ሄደና “እነሆ፥ ልጁ እዚያ የለም! እንግዲህ እኔ ወዴት ብሄድ ይሻለኛል?” አለ። ከዚህ በኋላ አንድ ፍየል ዐረዱና የዮሴፍን ልብስ በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት። እርሱም የልጁ ልብስ መሆኑን ተረድቶ “በእርግጥ የእርሱ ልብስ ነው! አንድ ክፉ አውሬ ገድሎታል፤ ልጄን ዮሴፍን አውሬ ቦጫጭቆ በልቶታል!” አለ። ከዚህ በኋላ ልብሱን በሐዘን ቀደደ፤ ማቅ በወገቡ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀኖች አለቀሰ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ሊያጽናኑት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱ ግን “ለልጄ እያለቀስሁ ወደ ሙታን ዓለም እወርዳለሁ” በማለት መጽናናትን እምቢ አለ። ስለዚህ ስለ ልጁ ማዘኑን ቀጠለ። በዚያን ጊዜ የምድያም ሰዎች እስማኤላውያን ዮሴፍን በግብጽ አገር ለጶጢፋር ሸጡት፤ ጶጢፋር ከፈርዖን ባለሥልጣኖች አንዱ የሆነ የዘበኞቹ አለቃ ነበር።

ዘፍጥረት 37:5-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እነርሱም እንደገና አብዝተው ጠሉት። እርሱም አላቸው፦ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፥ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበር፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፥ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወንድሞቹም፦ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም፦ “እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፥ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።” ሲል ነገራቸው። ለአባቱና ለወንድሞቹም በነገራቸው ጊዜ፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” በማለት አባቱ ገሠጸው። ወንድሞቹም ቀኑበት፥ አባቱ ግን ነገሩን ጠብቆ አኖረው። ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። እስራኤልም ዮሴፍን፦ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን እየጠበቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እንድልክህ ና” አለው። እርሱም “እነሆኝ” አለው። እርሱም፦ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። በዚህ ዓይነት ከኬብሮን ሸለቆ ላከው፥ ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም በየሜዳው ሲባዝን አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም፦ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ወንድሞቼን እየፈለግሁ ነው፥ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለ። ሰውዮውም፦ “ከዚህ ተነሥተዋል፥ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው። እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ያ ሕልም አላሚ ይኸው መጣ። ኑ፥ እንግደለውና በአንዱ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፥ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።” ሮቤልም ይህን ሲሰማ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ” በማለት ከእጃቸው አዳነው። “ደም አታፍስሱ፥ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጉድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲህም ሆነ፥ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፥ ወስደውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፥ ጉድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። ምግብ ሊበሉ ተቀመጡ፥ ዓይናቸውንም አንሥተው ሲያዩ፥ እነሆ የእስማኤላውያን ነጋዴዎች ወደ ግብጽ ለመውረድ ከገለዓድ ይመጣሉ፥ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድነው? ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና።” ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። የምድያም ነጋዶችም አለፉ፥ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጉድጓድ አወጡት፥ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፥ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት። ሮቤል ወደ ጉድጓዱ በተመለሰ ጊዜ፥ እነሆ ዮሴፍ በጉድጓድ የለም፥ ልብሱንም ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ “ብላቴናው የለም፤ እኔስ ወዴት ልሂደው?” አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት። እርሱም ለይቶ ስላወቀው፦ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል” አለ። ያዕቆብ ልብሱንም ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፥ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ፦ “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ።” አባቱም እንደዚህ ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብጽ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጶጥፋራ ሸጡት።