ዘፍጥረት 37:23-27
ዘፍጥረት 37:23-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደ ደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት ያጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤ ይዘውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር። ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች የግመል ጓዝ አዩ። ነጋዴዎቹ ሽቶ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብፅ የሚወርዱ ነበሩ። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል? ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አናንሣ። ምንም ቢሆንኮ ወንድማችን፣ ሥጋችን ነው” ወንድሞቹም በሐሳቡ ተስማሙ።
ዘፍጥረት 37:23-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲንም ሆነ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱ ቀሚሱን ገፈፋት ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነውም? ኑ ለእስማኤላውያን እንሽጠው እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና
ዘፍጥረት 37:23-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በደረሰ ጊዜ ጌጠኛ የሆነውን እጀ ጠባቡን አወለቁበት፤ ዮሴፍንም ወስደው ውሃ በሌለው ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት። ከዚህ በኋላ ምሳ ለመብላት ተቀመጡ፤ በሚመገቡበትም ጊዜ እስማኤላውያን ነጋዴዎችን በሩቅ አዩ፤ እነርሱም በግመሎቻቸው ቅመማ ቅመም፥ በለሳን፥ ከርቤም ጭነው ከገለዓድ ወደ ግብጽ የሚጓዙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን ገድለን የአሟሟቱን ሁኔታ ብንደብቅ ምን ይጠቅመናል? እርሱ የሥጋ ወንድማችን ስለ ሆነ” በእርሱ ላይ ጒዳት ከምናደርስበት ይልቅ ለእነዚህ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ብንሸጠው ይሻላል፤ ወንድሞቹም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ።
ዘፍጥረት 37:23-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺውን ቀሚሱን ገፈፉት፤ ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ባዶ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዐይኖቻቸውንም በአነሡ ጊዜ እነሆ፥ ይስማኤላውያን ነጋድያን ከገለዓድ ሲመጡ አዩ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ወደ ግብፅ ሀገርም ሊያራግፉ ይሄዱ ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፥ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድን ነው? ኑ፥ ለእነዚህ ይስማኤላውያን እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፤ ወንድማችን ሥጋችን ነውና።” ወንድሞቹም የነገራቸውን ሰሙት።
ዘፍጥረት 37:23-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ሆነ፥ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፥ ወስደውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፥ ጉድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። ምግብ ሊበሉ ተቀመጡ፥ ዓይናቸውንም አንሥተው ሲያዩ፥ እነሆ የእስማኤላውያን ነጋዴዎች ወደ ግብጽ ለመውረድ ከገለዓድ ይመጣሉ፥ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድነው? ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና።” ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት።