ዘፍጥረት 37:13-28
ዘፍጥረት 37:13-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እስራኤልም ዮሴፍን “እንደምታውቀው ወንድሞችህ መንጎቹን በሴኬም አካባቢ አሰማርተዋል፤ በል ተነሥ፣ ወደ እነርሱ ልላክህ።” አለው። ዮሴፍም “ይሁን ዕሺ” አለው። ያዕቆብም፣ “ሄደህ ወንድሞችህም፣ መንጎቹም ደኅና መሆናቸውን አይተህ ወሬያቸውን አምጣልኝ” አለው፤ ከኬብሮንም ሸለቆ ወደ ሴኬም ላከው። ዮሴፍም ሴኬም በደረሰ ጊዜ፣ ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲባዝን አንድ ሰው አግኝቶት “ምን እየፈለግህ ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮሴፍም፣ “ወንድሞቼን እየፈለግኋቸው ነው፤ መንጎቻቸውን የት እንዳሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው። ሰውየውም፣ “ከዚህ ሄደዋል፤ ደግሞም፣ ‘ወደ ዶታይን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፣ ዶታይን አቅራቢያም አገኛቸው። ወንድሞቹም ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲመጣ በሩቅ አዩት፤ ወደ ነበሩበትም ስፍራ ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ። እነርሱም እንዲህ ተባባሉ፤ “ያ ሕልም ዐላሚ መጣ፤ ኑ እንግደለውና ከጕድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ ‘ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው’ እንላለን፤ እስኪ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን!” ሮቤል ግን ይህን ምክር ሲሰማ ከእጃቸው ሊያድነው ፈለገ፤ እንዲህም አለ፣ “ሕይወቱ በእጃችን አትለፍ፤ የሰው ደም አታፍስሱ፤ እዚህ ምድረ በዳ፣ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ እጃችሁን አታንሡበት።” ሮቤል ይህን ያለው ሕይወቱን ከእጃቸው አትርፎ ወደ አባቱ ሊመልሰው ዐስቦ ነበር። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደ ደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት ያጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤ ይዘውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር። ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች የግመል ጓዝ አዩ። ነጋዴዎቹ ሽቱ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብጽ የሚወርዱ ነበሩ። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል? ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በርሱ ላይ አናንሣ። ምንም ቢሆንኮ ወንድማችን፣ ሥጋችን ነው” ወንድሞቹም በሐሳቡ ተስማሙ። የምድያም ነጋዴዎችም እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሱ፣ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጕድጓድ አውጥተው ለእስማኤላውያን በሃያ ጥሬ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት።
ዘፍጥረት 37:13-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እስራኤልም ዮሴፍን፥ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና” አለው። እርሱም፥ “እሺ” አለው። እርሱም፥ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፤ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። ወደ ኬብሮንም ቆላ ላከው፤ ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም፥ በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውየውም፥ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “ወንድሞችን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ?” አለ። ሰውየውም፥ “ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፤ በዶታይንም አገኛቸው። እነርሱም ወደ እነርሱ ሳይቀርብ ከሩቅ አስቀድመው አዩት፥ ይገድሉትም ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው፥ “ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፤ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ሕልሞቹም ምን እንደሚሆኑ እናያለን።” ሮቤልም ይህን ሰማ፤ ከእጃቸውም አዳነው፤ እንዲህም አለ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ።” ሮቤልም፥ “ደም አታፍስሱ፤ በዚች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፤ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። ሮቤልም እንዲህ ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺውን ቀሚሱን ገፈፉት፤ ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ባዶ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዐይኖቻቸውንም በአነሡ ጊዜ እነሆ፥ ይስማኤላውያን ነጋድያን ከገለዓድ ሲመጡ አዩ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ወደ ግብፅ ሀገርም ሊያራግፉ ይሄዱ ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፥ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድን ነው? ኑ፥ ለእነዚህ ይስማኤላውያን እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፤ ወንድማችን ሥጋችን ነውና።” ወንድሞቹም የነገራቸውን ሰሙት። እነዚያ ይስማኤላውያን ነጋዴዎችም ሲያልፉ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጕድጓድ ጐትተው አወጡት፤ ለይስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።
ዘፍጥረት 37:13-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እስራኤልም ዮሴፍን፦ ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና አለው። እርሱም እነሆኝ አለው። እርሱም፦ ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅን እንደ ሆኑ እይ ወሬአቸውንም አምጣክኝ አለው። እንዲንም ከኬብሮን ቆላ ሰደደው ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም በምድረ በዳ ስቅበዘብዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው ሰውዮውም፦ ምን ትፈልጋለህ? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ወንድሞቼን እፈልጋለሁ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ አለ። ሰውዮውም፦ ከዚህ ተነሥተዋል ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ስምቼአቸዋለሁ አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ በዶታይንም አገኛቸው። እነርሱ በሩቅ ሳለ አዩት ወድ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ያባለ ሕልም ይኸው መጣ። አሁንም ኑ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፋ አውሬም በላው እንላለን ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን። ሮቤልም ይህን ሰማ ከእጃቸውም አዳነው እንዲህም አለ፦ ሕይወቱን አናጥፋ። ሮቤል፦ ደም አታፍስሱ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲንም ሆነ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱ ቀሚሱን ገፈፋት ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነውም? ኑ ለእስማኤላውያን እንሽጠው እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና የምድያም ነጋዶችም አለፈ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።
ዘፍጥረት 37:13-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስራኤልም ዮሴፍን “እነሆ፥ ወንድሞችህ መንጋውን ይዘው ወደ ሴኬም መሰማራታቸውን ታውቃለህ፤ ስለዚህ ወደ እነርሱ ልልክህ እፈልጋለሁ” አለው። ዮሴፍም “እሺ እሄዳለሁ” አለ። አባቱም “በል እንግዲህ ሂድና የወንድሞችህንና የመንጋዎቹን ደኅንነት አይተህ ንገረኝ” አለው። በዚህ ዐይነት እስራኤል ዮሴፍን ከኬብሮን ሸለቆ ላከው። ዮሴፍም ሴኬም ደረሰ። እዚያም በየሜዳው ሲባዝን ሳለ አንድ ሰው አገኘውና “ምን እየፈለግህ ነው?” ብሎ ጠየቀው። ዮሴፍም “ወንድሞቼን እየፈለግሁ ነው፤ መንጋዎቻቸውን ይዘው ወዴት እንደ ተሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው። ሰውየውም “እነርሱ ከዚህ ሄደዋል፤ ‘ወደ ዶታን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቼአቼዋለሁ” አለው። ስለዚህ የወንድሞቹን ዱካ ተከትሎ ሄደና በዶታን አገኛቸው። እነርሱም በሩቅ አዩት፤ ወደ እነርሱም ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ። እርስ በርሳቸውም “እነሆ፥ ያ ሕልም አላሚ መጣ፤ ኑ እንግደለውና ከእነዚህ ጒድጓዶች በአንደኛው ውስጥ እንጣለው፤ ከዚህ በኋላ ‘ክፉ አውሬ በላው’ ብለን ማመኻኘት እንችላለን፤ በዚህ ዐይነት የሕልሙን መጨረሻ እናያለን” አሉ። ሮቤል ይህንን በሰማ ጊዜ ከእጃቸው ለማዳን በመፈለግ “ተዉ፤ አይሆንም፤ ባንገድለው ይሻላል፤ ከምትገድሉት ይልቅ በዚህ በበረሓ ባለው ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት” አላቸው። ሮቤል ይህን ያለው ከእጃቸው አድኖ ወደ አባቱ ሊመልሰው ፈልጎ ነው። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በደረሰ ጊዜ ጌጠኛ የሆነውን እጀ ጠባቡን አወለቁበት፤ ዮሴፍንም ወስደው ውሃ በሌለው ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት። ከዚህ በኋላ ምሳ ለመብላት ተቀመጡ፤ በሚመገቡበትም ጊዜ እስማኤላውያን ነጋዴዎችን በሩቅ አዩ፤ እነርሱም በግመሎቻቸው ቅመማ ቅመም፥ በለሳን፥ ከርቤም ጭነው ከገለዓድ ወደ ግብጽ የሚጓዙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን ገድለን የአሟሟቱን ሁኔታ ብንደብቅ ምን ይጠቅመናል? እርሱ የሥጋ ወንድማችን ስለ ሆነ” በእርሱ ላይ ጒዳት ከምናደርስበት ይልቅ ለእነዚህ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ብንሸጠው ይሻላል፤ ወንድሞቹም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ። የምድያም ነጋዴዎች የሆኑ እስማኤላውያን በዚያ በኩል ያልፉ ነበር፤ ስለዚህ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጒድጓድ ጐትተው በማውጣት ለእነዚህ እስማኤላውያን በሃያ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይዘውት ሄዱ።
ዘፍጥረት 37:13-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እስራኤልም ዮሴፍን፦ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን እየጠበቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እንድልክህ ና” አለው። እርሱም “እነሆኝ” አለው። እርሱም፦ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። በዚህ ዓይነት ከኬብሮን ሸለቆ ላከው፥ ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም በየሜዳው ሲባዝን አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም፦ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ወንድሞቼን እየፈለግሁ ነው፥ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለ። ሰውዮውም፦ “ከዚህ ተነሥተዋል፥ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው። እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ያ ሕልም አላሚ ይኸው መጣ። ኑ፥ እንግደለውና በአንዱ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፥ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።” ሮቤልም ይህን ሲሰማ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ” በማለት ከእጃቸው አዳነው። “ደም አታፍስሱ፥ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጉድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲህም ሆነ፥ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፥ ወስደውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፥ ጉድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። ምግብ ሊበሉ ተቀመጡ፥ ዓይናቸውንም አንሥተው ሲያዩ፥ እነሆ የእስማኤላውያን ነጋዴዎች ወደ ግብጽ ለመውረድ ከገለዓድ ይመጣሉ፥ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድነው? ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና።” ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። የምድያም ነጋዶችም አለፉ፥ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጉድጓድ አወጡት፥ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፥ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት።