ዘፍጥረት 22:9-14
ዘፍጥረት 22:9-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር ወዳለውም ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያዉን ሠራ፤ ዕንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያዉ በዕንጨቱ ላይ በልቡ አስተኛው። አብርሃምም እጁን ዘረጋ፤ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና፥ “አብርሃም! አብርሃም” አለው፤ እርሱም፥ “እነሆኝ” አለ። እርሱም፥ “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግበት፤ ለምትውድደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን ዐውቄአለሁ” አለው። አብርሃምም ዐይኖቹን አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ፥ በኋላው እነሆ፥ አንድ በግ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄዶ በጉን ወሰደው፤ በልጁ በይስሐቅ ፈንታም ሠዋው። አብርሃምም ዛሬ በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ፈጽሞ ታየኝ ሲል ያን ቦታ “ራእየ እግዚአብሔር” ብሎ ጠራው።
ዘፍጥረት 22:9-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ አመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው። ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ። የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም፤ አብርሃም፤” ብሎ ጠራው፤ አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና” አለው። አብርሃም ቀና ብሎ ተመለከተ፤ በቍጥቋጦ መካከልም ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተ ኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል።
ዘፍጥረት 22:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሰዊያውን ሰራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሰዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው። አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና፦ አብርሃም አብርሃም አለው፤ እርሱ፦ እነሆኝ አለ። እርሱም፦ በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምን እግዚአብሔር የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ። አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር አዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፦ በልጁም ፋንታ መሥውዕት አድርጎ ሠዋው። አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል።
ዘፍጥረት 22:9-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም መሠዊያ ሠርቶ እንጨቱን በላዩ ላይ ረበረበው፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ ከእንጨቱ በላይ በመሠዊያው ላይ አጋደመው። ልጁን ለማረድ ቢላዋ አንሥቶ እጁን ዘረጋ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ “አብርሃም! አብርሃም!” ብሎ ጠራው። አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁኝ!” አለ። መልአኩም “ልጁን አትንካ፤ ምንም ዐይነት ጒዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ከመስጠት ስለ አልተቈጠብክ እነሆ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ መሆንህን ተረድቼአለሁ።” አብርሃም ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ ቀንዶቹ በቊጥቋጦ ዛፍ የተያዙ አንድ በግ አየ፤ ሄዶ በጉን አመጣና በልጁ ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው። አብርሃም ያንን ቦታ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ ሰየመው፤ ዛሬም ቢሆን ሰዎች “እግዚአብሔር በተራራው ላይ ያዘጋጃል” ይላሉ።
ዘፍጥረት 22:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም መሠዊያ ሠራና እንጨቱን በላዩ ላይ ረበረበው፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ላይ፥ ከእንጨቱ በላይ አጋደመው። እጁንም ዘርግቶ፥ ልጁን ለማረድ አብርሃም ቢላዋ አነሣ። ነገር ግን የጌታ መልአክ “አብርሃም! አብርሃም!” ሲል ከሰማይ ተጣራ። አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁኝ!” አለ። እርሱም “በልጁ ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ ምንም ዓይነት ጉዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ለመስጠት እንዳልሳሳህ እነሆ አየሁ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ” አለ። አብርሃምም ዓይኑን አንስቶ ሲመለከት፥ ከኋላው እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዛፍ ቊጥቋጦ ተይዞ አየ፥ አብርሃምም ሄዶ በጉን አመጣና፥ በልጁ ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው። ስለዚህም አብርሃም ያንን ቦታ “ጌታ ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ሰየመው፤ ዛሬም ቢሆን ሰዎች “ጌታ በተራራው ላይ ያዘጋጃል” ይላሉ።