ዘፍጥረት 22:12-18
ዘፍጥረት 22:12-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም፥ “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግበት፤ ለምትውድደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን ዐውቄአለሁ” አለው። አብርሃምም ዐይኖቹን አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ፥ በኋላው እነሆ፥ አንድ በግ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄዶ በጉን ወሰደው፤ በልጁ በይስሐቅ ፈንታም ሠዋው። አብርሃምም ዛሬ በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ፈጽሞ ታየኝ ሲል ያን ቦታ “ራእየ እግዚአብሔር” ብሎ ጠራው። የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፤ እንዲህም አለው፦ “እግዚአብሔር በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ ለምትወድደው ልጅህም ከእኔ አልራራህምና መባረክን እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ፈጽሞ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላት ሀገሮችን ይወርሳሉ፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና።”
ዘፍጥረት 22:12-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና” አለው። አብርሃም ቀና ብሎ ተመለከተ፤ በቍጥቋጦ መካከልም ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተ ኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ አብርሃምን ከሰማይ ዳግመኛ ጠራው፤ እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም (ያህዌ) በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና፣ በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”
ዘፍጥረት 22:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱ፦ እነሆኝ አለ። እርሱም፦ በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምን እግዚአብሔር የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ። አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር አዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፦ በልጁም ፋንታ መሥውዕት አድርጎ ሠዋው። አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል። የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለትኛ ጊዜ ጠራው፦ እንዲህም አለው፦ እንዴህም አለው፦ እግዜአብሔር፦ በራሴማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፦ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምን በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፦ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር እንዳል አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካል፦ ቃሌን ሰምተሃልና።
ዘፍጥረት 22:12-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መልአኩም “ልጁን አትንካ፤ ምንም ዐይነት ጒዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ከመስጠት ስለ አልተቈጠብክ እነሆ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ መሆንህን ተረድቼአለሁ።” አብርሃም ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ ቀንዶቹ በቊጥቋጦ ዛፍ የተያዙ አንድ በግ አየ፤ ሄዶ በጉን አመጣና በልጁ ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው። አብርሃም ያንን ቦታ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ ሰየመው፤ ዛሬም ቢሆን ሰዎች “እግዚአብሔር በተራራው ላይ ያዘጋጃል” ይላሉ። የእግዚአብሔር መልአክ ሁለተኛ ጊዜ አብርሃምን ጠራውና እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ‘ብዙ በረከት እንደምሰጥህ በራሴ ስም እምላለሁ’ ይላል፤ ይህን ስላደረግህና አንድ ልጅህንም ለእኔ ለመስጠት ስላልተቈጠብክ፥ እኔም ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘሮችህም ጠላቶቻቸውን ድል ነሥተው ከተሞቻቸውን ይይዛሉ። ትእዛዜን ስለ ፈጸምክ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”
ዘፍጥረት 22:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም “በልጁ ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ ምንም ዓይነት ጉዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ለመስጠት እንዳልሳሳህ እነሆ አየሁ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ” አለ። አብርሃምም ዓይኑን አንስቶ ሲመለከት፥ ከኋላው እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዛፍ ቊጥቋጦ ተይዞ አየ፥ አብርሃምም ሄዶ በጉን አመጣና፥ በልጁ ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው። ስለዚህም አብርሃም ያንን ቦታ “ጌታ ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ሰየመው፤ ዛሬም ቢሆን ሰዎች “ጌታ በተራራው ላይ ያዘጋጃል” ይላሉ። የጌታ መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥ እንዲህም አለው፦ “ጌታ፥ በራሴ እምላለሁ፥ ይላል፤ ምክንያቱም ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልከኝምና፤ በእውነት መባረክን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት እና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘሮችህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና፥ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ።”