ዘፍጥረት 19:15-26
ዘፍጥረት 19:15-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፥ “ተነሣ፤ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ አንተም በከተማዪቱ ሰዎች ኀጢአት እንዳትጠፋ” እያሉ ያስቸኩሉት ነበር። እርሱም በዘገየ ጊዜ እነዚያ መላእክት የእርሱን እጅ፥ የሚስቱንም እጅ፥ የሁለቱን ሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ራርቶላቸዋልና። ወደ ሜዳም በወጡ ጊዜ እንዲህ አሉት፥ “ራስህን አድን፤ ወደ ኋላም አትመልከት፤ አንተንም መከራ እንዳታገኝህ በዚች ሀገር በዳርቻዋና በተራራዋ አትቁም።” ሎጥም አላቸው፥ “ጌቶች ሆይ፥ በጀ በሉኝ፤ እነሆ፥ ባሪያህ በፊትህ ምሕረትን አግኝቼ እንደሆነ፥ ሰውነቴንም ታድናት ዘንድ፥ ቸርነትህን አብዝተህልኝ እንደ ሆነ፥ መከራ አግኝቶኝ እንዳልጠፋ ወደ ተራራ ሸሽቼ ራሴን ማዳን አልችልም። እነሆ፥ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፤ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ራሴን ላድን፤ ሰውነቴም ከዳነች ትንሽ አይደለችም፤” እርሱም አለው፥ “ስለ እርስዋ የነገርኸኝን ያችን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ፥ እንዳልኸው ልመናህን ተቀብዬሃለሁ፤ እንግዲህ ፍጠንና በዚያ ራስህን አድን፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ሴጎር ተባለ። ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች፤ ሎጥም ወደ ሴጎር ገባ። እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞችም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፤ የጨው ሐውልትም ሆነች።
ዘፍጥረት 19:15-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋር አብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት። ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የእርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው። እንዳወጧቸውም፣ መልአኩ፣ “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ፈጥናችሁ ሽሹ፤ መለስ ብላችሁ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ፤ ከረባዳው ስፍራ እንኳ ቆም አትበሉ፤ ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለዚያ ትጠፋላችሁ” አላቸው። ሎጥም እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን፤ እነሆ፤ እኔ ባሪያህ አንዴ በፊትህ ሞገስ አግኝቻለሁ፤ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርኅራኄ አድርገህልኛል፤ እኔ እንደ ሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል። እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ፤ በጣም ትንሽ አይደለችም እንዴ? ወደዚያ ብሸሽ እኮ ሕይወቴ ትተርፋለች።” እርሱም እንዲህ አለው፤ “ይሁን እሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም። አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ አንዳች ማድረግ ስለማልችል ቶሎ ብለህ ወደዚያ ሽሽ።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ። ሎጥ ዞዓር ሲደርስ ፀሓይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰዶምና በገሞራ ላይ ከሰማይ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ የሚያቃጥል ዲንና እሳት አዘነበባቸው። እነዚያንም ከተሞችና ረባዳውን ምድር በሙሉ፣ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፣ የምድሩን ቡቃያ ሳይቀር ገለባበጠው። የሎጥ ሚስት ግን ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች።
ዘፍጥረት 19:15-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፥ ተነሣ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውስድ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፉ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር። እርሱም በዘገያ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ስዎች የእርሱን እጅ የሚስቱን፥ እጅ የሁለቱን የሴትፕች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት። ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኍላ እንዲህ አለው ራስህን አድን ወደ ኍላህ አትይ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ። ሎጥም አላቸው ጌቶቼ ሆይ እንዲህስ አይሁን እነሆ ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል ክፋ እንዳያጋኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት እርስዋም ትንሽ ናት ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ እርስዋ ትንሽ ከተም አይደለችምን? እርሱም አለው፤ የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፤ በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና። ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ። ሎጥ ወደ ዞዓር በገብ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች። እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ እነዚያንም ከተሞች በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። የሎጥም ሚስት ወደ ኍላዋ ተመለከተች የጨው ሐውልት፥ ሆነች።
ዘፍጥረት 19:15-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማግስቱ ጠዋት በማለዳ መላእክቱ ሎጥን “ፍጠን! ከተማይቱ ስትጠፋ አብራችሁ እንዳትጠፉ ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ውጣ” እያሉ አጣደፉት። ሎጥ ግን አመነታ፤ ሆኖም እግዚአብሔር ለእርሱና ለቤተሰቡ ስለ ራራ መላእክቱ ሎጥንና ሚስቱን፥ ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን፥ እጆቻቸውን ይዘው ከከተማዋ እንዲያወጡአቸው አደረገ። ካወጡአቸውም በኋላ ከመላእክቱ አንዱ “ሕይወታችሁን አድኑ! ወደ ኋላ አትመልከቱ! በሸለቆው ውስጥ አትዘግዩ፤ እንዳትሞቱ ወደ ተራራው ሽሹ!” አላቸው። ሎጥ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ፥ እባካችሁ ወደዚያ እንድንወጣ አታደርጉ፤ እኔ አገልጋያችሁ በፊታችሁ ሞገስ ስላገኘሁ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርዳታ አድርጋችሁልኛል፤ ነገር ግን ይህ ጥፋት ደርሶብኝ እሞታለሁ ብዬ ስለምሰጋ ወደዚያ ተራራ መሸሽ አልችልም። እኔ በፍጥነት ሸሽቼ ላመልጥበት የምችል እነሆ አንዲት ትንሽ ከተማ በቅርብ አለች፤ ስለዚህ ሸሽቼ ወደ እርሷ እንድሄድ ፍቀዱልኝ፤ እንደምታዩአት ትንሽ ከተማ ናት፤ ወደ እርስዋ ብሄድ ሕይወቴ ከጥፋት ይድናል።” መልአኩም “እሺ አንተ ባልከው እስማማለሁ፤ ይህችን አንተ የምትላትን ከተማ አላጠፋትም፤ ወደዚያች ከተማ እስከምትደርስ ምንም ማድረግ ስለማልችል ፈጥነህ ወደ እርስዋ ሽሽ!” አለው። ሎጥ ያቺን ከተማ ትንሽ ብሎአት ስለ ነበር ጾዓር ተባለች። ሎጥ ወደ ጾዓር ሲደርስ ገና ፀሐይ መውጣትዋ ነበር፤ እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ከተሞች ላይ እሳትና ዲን ከራሱ (ከእግዚአብሔር ዘንድ) ከሰማይ አዘነበ። በዚህ ዐይነት እነዚያን ከተሞችና ሸለቆዎች፥ እዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፥ በምድሩም ላይ የበቀለውን ነገር ሁሉ ደመሰሰ። የሎጥ ሚስትም ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች።
ዘፍጥረት 19:15-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፦ “ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፥ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ” እያሉ ያስቸኩሉት ነበር። እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት። ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አሉት፦ “ራስህን አድን፥ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።” ሎጥም፥ አላቸው፦ “ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፥ እነሆ ባርያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፥ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፥ እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርሷ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርሷም ትንሽ ናት፥ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርሷ ሸሽቼ ላምልጥ፥ እርሷ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?” እርሱም አለው፦ “የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፥ በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፥ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ጾዓር ተባለ። ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች። እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፥ እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች።