ዘፍጥረት 18:11-15
ዘፍጥረት 18:11-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያ ጊዜ አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜያቸው ገፍቶ ነበር፤ ሣራም ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ዐልፎ ነበር። ሣራ በልቧ፣ “ካረጀሁና ጌታዬም ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል?” ብላ ሣቀች። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች? ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።” ሣራ ስለ ፈራች፣ “ኧረ አልሣቅሁም” ብላ ዋሸች። እርሱ ግን፣ “ሣቅሽ እንጂ” አላት።
ዘፍጥረት 18:11-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ቆማ ሳለች ይህን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜያቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም ለብቻዋ በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፥ “እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ፈጽሞ ሽምግሎአል።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “ሣራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት? እስከ ዛሬ ገና ነኝን? በእውነትስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅትዋል እነሆ፥ እኔም አርጅቻለሁ ብላለችና። በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች።” ሣራም ስለ ፈራች “አልሳቅሁም” ብላ ካደች። እርሱም፥ “አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ” አላት።
ዘፍጥረት 18:11-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፤ ካረጀሁ በኍላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል። እግዚአብሔርም አብርሃምም አለው፤ ካረጀሁ በኍላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለእግዚአሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንድ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታግኝለች። ሣራ፥ ስለ ፈራች፤ አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም፤ አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት።
ዘፍጥረት 18:11-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው መግፋት አርጅተው ነበር፤ የሣራም፥ ልጅ የመውለጃ ዕድሜዋ አልፎ ነበር። ስለዚህ ሣራ “እኔ አሁን እንዲህ ካረጀሁ በኋላ ጌታዬ አብርሃምም ካረጀ በኋላ እንዲህ ያለ ደስታ ሊኖረኝ ይችላልን?” ብላ በማሰብ ሳቀች። እግዚአብሔርም አብርሃምን “ሣራ ‘እንደዚህ ካረጀሁ በኋላ ልጅ መውለድ እችላለሁን’ በማለት ስለምን ሳቀች? ከቶ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? እንደ ነገርኩህ የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። ሣራ እጅግ ፈርታ ስለ ነበር “አልሳቅሁም” ብላ ካደች። እርሱ ግን “በእርግጥ ስቀሻል” አላት።
ዘፍጥረት 18:11-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፥ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለጌታ የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፥ ሣራም ልጅን ታገኛለች።” ሣራም ስለ ፈራች፦ “አልሳቅሁም” ስትል ካደች። እርሱም፦ “አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ” አላት።