ዘፍጥረት 18:10-14
ዘፍጥረት 18:10-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም፥ “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ። ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ቆማ ሳለች ይህን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜያቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም ለብቻዋ በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፥ “እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ፈጽሞ ሽምግሎአል።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “ሣራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት? እስከ ዛሬ ገና ነኝን? በእውነትስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅትዋል እነሆ፥ እኔም አርጅቻለሁ ብላለችና። በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች።”
ዘፍጥረት 18:10-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም፣ “ጊዜው ሲደርስ በርግጥ በዚህ ጊዜ በሚቀጥለው ዓመት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። ሣራም በዚህ ጊዜ ከበስተጀርባው ካለው ከድንኳኑ ደጃፍ ሆና ትሰማ ነበር። በዚያ ጊዜ አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜያቸው ገፍቶ ነበር፤ ሣራም ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ዐልፎ ነበር። ሣራ በልቧ፣ “ካረጀሁና ጌታዬም ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል?” ብላ ሣቀች። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች? ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።”
ዘፍጥረት 18:10-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም፥ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኍላው ሳለች ይህንን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፤ ካረጀሁ በኍላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል። እግዚአብሔርም አብርሃምም አለው፤ ካረጀሁ በኍላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለእግዚአሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንድ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታግኝለች።
ዘፍጥረት 18:10-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሦስቱም እንግዶች አንዱ አብርሃምን “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። እርሱም ይህን በሚናገርበት ጊዜ ሣራ በስተኋላው በድንኳኑ ደጃፍ ቆማ ታዳምጥ ነበር፤ አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው መግፋት አርጅተው ነበር፤ የሣራም፥ ልጅ የመውለጃ ዕድሜዋ አልፎ ነበር። ስለዚህ ሣራ “እኔ አሁን እንዲህ ካረጀሁ በኋላ ጌታዬ አብርሃምም ካረጀ በኋላ እንዲህ ያለ ደስታ ሊኖረኝ ይችላልን?” ብላ በማሰብ ሳቀች። እግዚአብሔርም አብርሃምን “ሣራ ‘እንደዚህ ካረጀሁ በኋላ ልጅ መውለድ እችላለሁን’ በማለት ስለምን ሳቀች? ከቶ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? እንደ ነገርኩህ የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው።
ዘፍጥረት 18:10-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም፦ “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፥ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፥ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለጌታ የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፥ ሣራም ልጅን ታገኛለች።”